እንግሊዝ ቦይንግን ከበረራ ካገዱት ሃገራት ተቀላቀለች

ለጊዜው የሲልክኤር 6 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደዋል Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ለጊዜው የሲልክኤር 6 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደዋል

የእንግሊዝ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለጥንቃቄ ከበረራ አገደ።

ይህን እንዲወስኑ ያደረጋቸውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላንን መከስከስ ተከትሎ፤ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው የቦይንግ አውሮፕላን በመሆኑና የ157 ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ ነው።

አውሮፕላኑን ከበረራ በማገድ እንግሊዝ ማሌዥያን፣ ሲንጋፖርን፣ ቻይናንና አውስትራሊያን ተቀላቅላለች። የሃገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ላልተወሰነ ጊዜ እገዳው እንደሚቀጥል አሳውቋዋል።

ትዊ የተሰኘው አየር መንገድና የኖርዌይ አየር መንገድ ሁለቱም የቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን ተጠቃሚዎች ናቸው።

"የእንግሊዝ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ነገሮችን ከቅርብ ሲቆጣጠር የነበረ ሲሆን ለጊዜው ከመረጃ ሳጥኑ በቂ መረጃ ባለመገኘቱ ለጥንቃቄ ሲባል አውሮፕላኖቹን ከማብረርም ሆነ በእንግሊዝ ከባቢ አየር እንዳይበሩ አግደናል" የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።

የትዊ አየር መንገድ መግለጫ ያሏቸውን የቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላኖች እንዳገዱ ይነግራል።

"ከእረፍት የሚመለሱ ተሳፋሪዎች በሙሉ በሌላ አውሮፕላን እንዲመለሱ አድርገናል" ያለው ሲቪል አቪየሽኑ ወደ እረፍት ለሚሄዱ ተሳፋሪዎቻቸውም ይህንኑ እንዳመቻቹ አሳውቀዋል።

የኖርዌይ አየር መንገድም የዚህን አውሮፕላን በረራዎች በሙሉ ማገዱንና በተሳፋሪዎች ዘንድ ለተፈጠረው ችግር በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ሞዴል በ 6 ወር ጊዜ ውስጥ ሁለቴ የመከስከስ አደጋ ቢያጋጥበውም የአሜሪካ የፌደራል አየር መንገድ አስተዳደር ግን አውሮፕላኑ ለመብረር ብቁ ነው ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

Image copyright JONATHAN DRUION

ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ኬንያ በመብረር ላይ የነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ካኮበኮበ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ 157 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

አደጋው በጥቅምት ወር ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት የቀጠፈው የላየን ኤር 737 ማክስ 8 ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።

አንዳንድ አየርመንገዶች የአውሮፕላኑን ሞዴል ፕሌኖቻቸውን ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዳይበሩ አስጠንቅቀዋል።

ነገር ግን ሰኞ ማምሻ ላይ የአሜሪካው ፌደራል አየርመንገድ አስተዳደር መስሪያ ቤት አውሮፕላኑ ለበብረር ብቁ ነው፤ ምንም የደህንነት ስጋት የለበትም ብሏል።

ቻይና፥ ኢንዶኔዥያና ኢትዮጵያ ሰኞ ዕለት ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላኖቻቸውን እንዳይበሩ አዘዋል። የአርጀንቲናው ኤሮላይነስ፥ የሜክሲኮው ኤሮሜክስኮ እና የብራዚል ጎል አየር ምንገዶችም በተመሳሳይ ሞዴል ፕሌኖች የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጠዋል።

ማክሰኞ የሲንጋፖር ሲቪል አቬሽን ባለስልጣናት "ሁሉንም የተለያዩ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ሞዴሎች ወደ ሲንጋፖር እና ከሲንጋፖር ወደ ሌላ ቦታ እንዳይበሩ በጊዜያዊነት ከልክለናል" ብለዋል።

እገዳው ከምሸት 3 ሰአት ጀምሮ ይተገበራል።

ቦይንግ ሞዴሉ ለመብረር አስተማማኝ ነው ካለ በኋላ ሌሎች አየርመንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ 8 ማብረርን ቀጥለዋል።

ከአደጋው በኋላ የቦይንግ አለማቀፍ የገበያ ድርሻ 12.9 በመቶ መውረዱ ተሰምቷል።

ስለአደጋው እስካሁን የምናውቀው

• 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከጠዋቱ 2፡38 ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ተነሳ።

• ከ6 ደቂቃ በኋላ ከአብራሪዎቹ ጋር ይደረግ የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ቢሾፍቱ አካባቢ አውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ አጋጠመው።

• የአውሮፕላኑ አብራሪ ችግር ስላጋጠመው ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ጠይቆ እንዲመለስ ተነግሮት እንደነበር ታውቋል።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

• ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከአራት ወራት በፊት የተገዛ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህ አይነት ስድስት አውሮፕላኖች አሉት።

• አውሮፕላኑ እሁድ ጠዋት ከጆሃንስበርግ በረራው ሲመለስ ምንም አይነት የበረራ ችግርን የሚመለከት መረጃ እንዳልነበርና ከሶስት ሰዓት በላይም መሬት ላይ ቆይቶ እንደነበር ተገልጿል።

• ዋና አብራሪው ያሬድ ሙልጌታ ከ 8 ሺህ ሰዓት በላያ ያበረረ ፓይለት ሲሆን ረዳት አብራሪው አህመድ ኑር ሞሃመድ ደግሞ 2 መቶ ሰዓት ያበረረ ፓይለት እንደሆነ ታውቋል።