አቶ ተወልደ አየር መንገዶች ሁሉ ለጊዜው ቦይንግ 737-8 ማክስን እንዳይጠቀሙ ጠየቁ

ተወልደ ገ/ማርያም Image copyright Getty Images

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም አስተማማኝነታችው እስኪረጋገጥ አየር መንገዶች ሁሉ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖችን ለጊዜው መጠቀም እንዲያቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ተወልደ ይህን ያሉት ዛሬ ጠዋት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ያመራ የነበረው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው ቢሾፍቱ አቅራቢያ ኢጄሬ በተባለ ቦታ ነው።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

የአደጋው መንስኤ ገና መጣራት ያለበት ቢሆንም አውሮፕላኑን ግን ለጊዜው ከአገልግሎት ውጭ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ አቶ ተወልደ።

በምክንያትነት የሚያስቀምጡት እሁድ ያጋጠመው አደጋ ከአምስት ወራት በፊት በላየን አየር መንገዱ ተመሳሳይ አውሮፕላን ቦይንግ 737-8 ማክስ በኢንዶኔዥያ ጃካርታ ካጋጠመው አደጋ ጋር መመሳሰሉን ነው።

ሁለቱም አውሮፕላኖች በተነሱ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው የተከሰከሱት።

የአሜሪካው የፌደራል አቪየሽን ባለስልጣን ምንም እንኳ በአሜሪካ ሴናተሮችና የሰራተኛ ማህበራት ግፊት ቢኖርም ቦይንግ 737-8 ማክስን አገልግሎት እንዳይሰጥ የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው አስታውቋል።