"እናቱ ስታየኝ 'ልጄ ያሬድ ይመጣል' እያለች ታለቅስ ነበር"- በናይሮቢ የካፒቴኑ ጸጉር አስተካካይ

ካፕቴን ያሬድ ጌታቸ Image copyright Hassan Katende/Facebook

ያሬድ ተክሌ ነው የምባለው። የምኖረው ናይሮቢ ነው።

ካፒቴን ያሬድ እኔ ጋ ነበር የሚስተካከለው። የረዥም ጊዜ ደንበኛዬ ነበር። በተለይ እረፍት ሲሆን፣ ለክሪስማስ እዚህ ኬንያ ሲመጣ እዚህ እኔ ጋ ነበር ጸጉሩን የሚስተካከለው።

እኔ ሰው ከሞተ በኋላ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ሲባል ብዙም ደስ አይለኝም። ግን እውነቴን ነው የምልህ ያሬድ በጣም የተለየ ልጅ ነበር።

ሥነ ሥርዓት ያለው፣ ሰውን የሚያከብር፣ ሁሉንም እኩል የሚያይ። እኔን ራሱ ያሬድ ብሎ ጠርቶኝ እኮ አያውቅም። ሞክሼ ነበር የሚለኝ... (እንባ ተናነቀው )

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

አንተ ጸጉር ቤት ከቤተሰቦቹ ጋ ነበር የሚመጣው?

አዎ! ሁልጊዜም ከቤተሰቡ ጋ ነው። አንድ ወንድሙ ኢሲያ ትምህርት የሚማር ነበር። ደግሞ ብታይ ከእናት ከአባቱ ጋ ያላቸው ነገር ልዩ ነው። ፍቅራቸው።

አባቱም ዶ/ር ጌታቸው ደንበኛዬ ነው። አብረው ነበር የሚመጡት። ያሬድ ግን በብዛት ከእናቱ ጋ ነበር የሚመጣው። እናቱ አምጥታው ነው ተስተከካክሎ ሲጨርስ የምትወስደው። ሂሳብ ራሱ « እሰኪ ዛሬ እኔ ልጋብዝህ እያለች እሷ ነበር የምትከፍልለት በብዛት» በጣም የሚያስቀና ቤተሰብ ነው። እሷ ሥራ ስላላት ቅዳሜ ወይ እሑድ ነበር እዚህ የሚመጡት።

የካፕቴን ያሬድ ሃይማኖታዊ የሀዘን ስርአት ያለ አስከሬን ተፈፀመ

Image copyright Yared Tekle
አጭር የምስል መግለጫ ብዙ ጊዜ ፀጉሩን ለመስተካከል የሚመጣው ከወላጆቹ ጋር እንደነበር አስተካካዩ ያሬድ ተክሌ ይናገራል

ከእናቱ ጋ ስታያቸው በቃ ያስቀናሉ። መኪና እንኳ እንዲነዳ ብዙም ደስ አይላትም፤ ስለምትሳሳለት። "እዚህ [ናይሮቢ] መንገዱ ጥሩ አይደለም፣ ጠባብ ነው በቃ እኔ አደርስሀለሁ" ትለው ነበር። በቃ ምን ልበልህ፣ እሱምኮ አንዳንዴ መኪና ይዞባት ይመጣል፤ ግን በቃ እናቱ ብዙም ደስ አይላትም።

ሁልጊዜም አብሯት እንዲሆን ነው የምትፈልገው።

ከካፒቴን ያሬድ ጋ በምን ቋንቋ ነበር የምትግባቡት?

እኔ በኪስዋሂሊ ነበር የማዋራው። እሱ ግን አማርኛ መልመድ ስለሚፈልግ በአማርኛ ማውራትን ይመርጣል። እኔ ሳውቀው ብዙም አልነበረም አማርኛ፤ ምክንያቱም እዚህ ኬንያ ተወልዶ ስላደገ በደንብ አይችልም ነበር። ከጊዜ በኋላ ነው አማርኛ ራሱ መሞከር የቻለው።

መጨረሻ ላይ ጎበዝ እየሆነ ነበር። ለመቻል ጉጉት ነበረው። ሁለተኛ ደግሞ ከዌስትላንድ እዚህ [ሀበሻ ሬስቶራንት] ድረስ የሚመጣው ለኢትዯጵያ ፍቅር ስላለው እንጂ ሰፈሩ'ኮ የሕንዶችም የኬንያም ብዙ ጸጉር ቤት አለ። እናቱ ደግሞ አማርኛ አይችሉም። ግን አንዳንድ ነገር ይገባቸዋል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

ምን ምን ያወራህ ነበር? ምን ትዝ ይልሃል?

በኢትዮጵያዊነቱ ደስተኛ ነው። ሁሌም ስሜቱ ደስተኛ ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ በመግባቱ በሥራው፣ ደስተኛ ነበር። ደቡብ አፍሪካም ሊሄድ ይፈልግ ነበር።

ኬንያም መማር ያስብ ነበር። ግን በኋላ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲያገኝ በጣም ደስተኛ ነበር። ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ እድል እንዳለ ነበር የሚነግረኝ።

የሞቱን ዜና እንዴት ነው የሰማው?

እኔ እስከመጨረሻው ድረስ አውሮፕላን መከስከሱንና ሰዎች መሞታቸውን እንጂ ያሬድ ይኖርበታል ብዬ በጭራሽ አላሰብኩም።

እና እዚሁ ጸጉር ቤት ውስጥ ሥራ ላይ እያለሁ « አብራሪው ግማሽ ኬንያ ነው አሉ...» ሲባል ደነገጥኩ። አንድ እሱን ነው የማውቀው እና ያሬድዬ ነው በቃ ብዬ ክው አልኩ።

ከዚያ በኋላ ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ስረጋጋ ቤተሰቦቹ ጋ ደወልኩ። ከዚያ በነገታው ሰኞ ጠዋት ዌስትላንድ ሄጄ እናቱ ጋ ለቅሶ ደረስኩ።

በጣም ነው እናቱ የምታሳዝነው። ልጇ የመጣ ያህል ነው ስታየኝ ያለቀሰችው። አቅፋኝ በቃ አለቀሰች። የኔና የሱን ቅርበት ስለምታቅ በጣም አለቀሰች።

"ልጄ ያሬድ እኮ አለ፤ ይመጣል" ትለኝ ነበር። ሞቱንም እንኳ ለመቀበል ተቸግራለች። (እንባ ይተናነቀዋል)

እንግዲህ እግዚአብሔር የፈቀደውን ነው የሚያደርገው፤ ለቤተሰቦቹ መጽናናት ይስጠልን ከማለት ውጭ ምን ማድረግ ይቻላል?