ደቡብ ክልል አዲስ ለተፈናቀሉ 54 ሺህ ጌድዮዎች የፌደራል መንግሥትን ድጋፍ ጠየቀ

የጌድዮ ተፈናቃዮች Image copyright MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

የደቡብ ክልል በወሰን ግጭት ከኦሮሚያ ክልል አዲስ ለተፈናቀሉ 54 ሺህ ስምንት መቶ 64 ጌድዮዎች እርዳታ እንዲልክለት የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንን የጠየቀው መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ እንደሆነ የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙት ሃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እነዚህ አዲስ ተፈናቃዮች በገደብ፣ ዲላ አቅራቢያ ጫጩ በሚባል እንዲሁም ጎቲቲ በተሰኘ ሌላ አካባቢ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

እነዚህ ተፈናቃዮች የተፈናቀሉበት ጊዜን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ደበበ "እኛ በዚህ ቀን ለማለት ይቸግረናል። ግን ደብዳቤው እንደደረሰን ወዲያው እርዳታ ልከናል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

ይህ የተላከው እርዳታ ለወዲያው ማስታገሻ ሲሆን ወደ ቦታው ሁኔታውን ለማጣራት ባልደረቦቻቸው መላካቸውንና በቀጣይ አስፈላጊው እርዳታ እንደሚላክ ጠቁመዋል።

በጌድዮ ዞን ገደብ ወረዳ አንድ ተራዶ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰብ ከመንግስት የሚገኘው እርዳታ እያነሰ ተቋርጧል የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ደበበ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት 208 ሺህ የሚሆኑ የጌድዮ ቋሚ ተፈናቃዮች ሲኖሩ እነዚህ ተፈናቃዮች ቀደም ሲል 860 ሺህ ከነበሩት የጌድዮ ተፈናቃዮች ብዙዎቹን ወደ ቀያቸው መመለስ ሲቻል በተለያየ ምክንያት ሳይመለሱ የቀሩ ናቸው።

ያልጠገገው የሀዋሳ ቁስል

በላፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብዙዎች በግጭት ምክንያት መፈናቀላቸው የሚታወቅ ነው።በተመሳሳይ መልኩ የተፈናቀሉ ጌድዮች ቁጥር ግን ከሌሎች በማይወዳደር መልኩ እጅግ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው።ነገር ግን ምንም እነኳ ቁጥራቸው ከፍተኛ፤ ያሉበት ሁኔታም አስከፊ ቢሆንም መንግስት የጌደዮ ተፈናቃዎችን ችላ ብሏቸዋል የሚል ጮኸት ከመቼው በላይ እየተሳማ ነው።

በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የጌድዮ ተፈናቃዮችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችም በማህበራዊ ሚዲያ ብዙዎች እየተጋሯቸው ነው።