የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡ በእርግጥ ስልጠናው ከአደጋው ጋር ይያያዛል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት Image copyright JONATHAN DRUION

ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ግዙፍ አየር መንገዶች ብቻ ያላቸው እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላን ነው። ነገር ግን አውሮፕላኑ ባጋጠመው አንዳች ውሉ ያልታወቀ እክል ሁለት አሰቃቂ አደጋዎች ከገጠሙት በኋላ ለጊዜውም ቢሆን ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።

ባለፈው ጥቅምት ወር የኢንዶኔዢያ ላየን አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ አውሮፕላን ለበረራ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ቁልቁል ወደ ባህር በመከስከሱ የ189 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ከዚህ አደጋ አምስት ወራት በኋላም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ መከተሉ የዓለም አቪየሽን ኢንዱስትሪን ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ ደረጃ ንጦታል።

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

ከአደጋው በኋላ ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ ተወስዶ የነበረው የአውሮፕላኑ የበረራ መረጃ ማስቀመጫ የያዛቸው መረጃዎች በተገቢው ሁኔታ መገልበጣቸውን፣ ምርመራውን እያካሄደ ያለው ቢኢኤ ለጊዜው ያገኘውን መረጃ ለኢትዯጵያ አደጋ ምርመራ ቢሮ እንዳስረከበም ተዘግቧል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያውና በኢንዶኔዢያው የአውሮፕላን አደጋዎች መካከል "ግልጽ መመሳሰል" እንዳለ ጠቁመዋል።

የአውሮፕላኖቹ ስሪት፣ ለበረራ ከተነሱ ከደቂቃዎች በኋላ አደጋው መድረሱ፣ የአወዳደቃቸው ሁኔታና ገጥሟቸዋል የተባለው ሁለንተናዊ ችግር በእጅጉ መመሳሰል ሲታይ ለአሰቃቂዎቹ አደጋዎች መከሰት የአብራሪዎቹ ችግር ሳይሆን አዲሱ አውሮፕላን ምርትና ስሪቱ አንዳች ቴክኒካዊ እክል ሳያጋጥመው እንዳልቀረ ፍንጭ ሰጥቷል።

በቦይንግ 737 ማክስ ፈቃድ ላይ ምርመራ ሊደረግ ነው

በተለይም የአሜሪካ የአቪየሽንት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት (FAA) የቦይንግ ምርቶችን ደረጃና ጥራት በመቆጣጠርና በማጽደቅ ሂደት ላይ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለቦይንግ አሳልፎ መስጠቱ ዓለምን አስደንግጧል። ባጋጠመኝ የፋይናንስ አቅም መመናመን የአውሮፕላኑ አምራች ራሱ የአዳዲስ አውሮፕላኖችን ብቃት በከፊል እንዲያረጋግጥ አድርጊያለሁ ሲል አምኗል፥ ባለሥልጣኑ ባሳለፍነው ሳምንት ለሲያትል ታይምስ የምርመራ ዘገባ በሰጠው ቃል።

ለዚህም ነው ይህ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ያላቸው ሃገራት በአውሮፕላኑ ላይ ያለው ችግር ተጣርቶ መፍትሄን እስኪያገኝ ድረስ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ያደረጉት። የአውሮፕላኑ አምራች የሆነችው አሜሪካም ለአውሮፕላኑ አገልግሎት ላይ መዋል የተሰጠውን ፍቃድ በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ አዛለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገኛኛ ብዙኃን የኢትዮጵያው አየር መንገድ አብራሪ ይህን አውሮፕላን ለማብረር የሚያስፈልግን ተጨማሪ ስልጠና እንዳልወሰደ በመጥቀስ ያቀረቡት ዘገባ ከተለያዩ ወገኖች ቁጣንና ተቃውሞን አስከትሏል።

ሁለቱን የአውሮፕላን አደጋዎች የሚያመሳስላቸው ነገር አለ

ዘገባው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለአየር መንገዱ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ አደጋው የደረሰበት አብራሪ ለዚህ አውሮፕላን ያስፈልጋል የተባለ በምስለ በረራ (ሲሙሌተር) የሚደረግ ልምምድ አላደረገም ሲል አስፍሯል። ይህን ልምምድ ለማድረግ ፕሮግራም የተያዘለትም በዚህ ወር መጨረሻ ነበር ይላል ዘገባው።

ይህን ተከትሎ በተለይ ከኢትዮጵያዊያን በኩል ዘገባው ቦይንግን ለማዳን የተረደረገ ሴራ በሚል ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል።

በተለይም ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ይህንን ዘገባ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ካጋራ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ አንባቢዎች ዘገባውን ክፉኛ ተችተዋል። ዘገባውን መሠረታዊ ቴክኒካል ችግርን ገሸሽ አድርጎ በአብራሪዎች ለማላከክ ቦይንግን ለማዳን የተደረገ ነውር አድርገው የቆጠሩት ጠቂት አይደሉም።

Image copyright ETHIOPIAN AIRLINES
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ወልደማሪያም በአደጋው ስፍራ

የምስለ በረራ ስልጠናና አደጋውን ምን አገናኛቸው?

የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ በቦይንግ 737 ላይ በቂ ልምድ ያላቸው ካፒቴኖች ማክስ ኤይት የተባለውን ዘመነኛ አውሮፕላን ለማብረር የተወሰነ ልምምድ ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቅሳል። ነገር ግን ቦይንግም ይሁን ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች የምስለ በረራ ስልጠና ማክስ-8ን ለማብረር እንደ ግዴታ አላስቀመጡም።

ብዙዎቹ የአሜሪካ የዚህ አውሮፕላን አብራሪዎችም ቢሆኑ ከ737 አውሮፕላን ወደ ማክስ 8 አብራሪነት የተሸጋገሩት የአንድ ሰዓት ስልጠና በአይፓድ በመውሰድ ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ስለምን የምስለ በረራ ስልጠና ጉዳይ ጎልቶ እንዲሰማ ተፈለገ የሚለው ለብዙዎች ግራ ሆኗል።

በርካታ የተለያዩ በቦይንግ ኩባንያ የተሠሩ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘገባውን "የተሳሳተ እና የተዛባ" መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

"እናቱ ስታየኝ 'ልጄ ያሬድ ይመጣል' እያለች ታለቅስ ነበር"- በናይሮቢ የካፒቴኑ ጸጉር አስተካካይ

ጨምሮም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አብራሪዎች አውሮፕላን አምራቹ ባወጠው እና በአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተቀባይነት ባለው መንገድ ተገቢውን ስልጠና መውሰዳቸውን አረጋግጧል።

በአቪዬሽን ጉዳዮች ላይ ዘጋቢ የሆነው ቃለየሱስ በቀለ "የአሜሪካ አብዛኞቹ 737 ማክስ አውሮፕላን ያላቸው አየር መንገዶች የምስለ በረራ መለማመጃ የላቸውም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ለስልጠናው የሚያገለግለው ይህ ዘመናዊ መሣሪያ ባለቤት ነው" ይላል።

ምስለ በረራ (ሲሙሌተር) እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጣ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህን ሞዴል ማሰልጠኛዎች ቀደም ብሎ የመግዛት ባህል እንዳለው ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

ቃለየሱስ እንደሚለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማክስ ኤይትን በምስለ በረራ መለማመጃ ከጥር ወር ወዲህ ማሰልጠን የጀመረ ሲሆን አብራሪዎቹም በየስድስት ወሩ ልምምድ ያደርጋሉ፤ ይህን ልምምድ ተከትሎም ፈተና ይወስዳሉ። ይህ ለኢትዯጵያ አየር መንገድ አዲስ ነገር አይደለም

በተጨማሪም ከ737 800 ኤን ጂ (ኔክስት ጄኔሬሽን) ከተባለው አውሮፕላን ወደ ማክስ 8 አውሮፕላን ሲኬድ ልዩነታቸው የተወሰነ ስለሆነ አብራሪዎች ልዩነቱን እንዲወስዱ ቦይንግ እንደሚመክር የሚናገረው ቃለእየሱስ፤ "ይህንን ስልጠና ደግሞ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን አብራሪ ወስዷል" ሲል ይናገራል።

ስለምንጓዝበት የአውሮፕላን አይነት እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ነገር ግን ከቦይንግ 737 ማክስ ቀደም ያለውን ስሪት ያበሩ የነበሩ አብራሪዎች በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል ያለው ልዩነት ጉልህ የሚባል ባለመሆኑ በምስለ በረራም ባይሆን በቀላል ስልጠና ክፍተቱን ማሟላት ይችላሉ።

"ይህንን የሚለው ደግሞ እራሱ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ነው። ቦይንግ ይህን ባይል ኖሮማ ልምምዱን ያላደረጉ ሁሉ ማክስን ማብረር አይችሉም ነበር" ይላል ቃለየሱስ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ባወጣው መግለጫ ላይ በኢንዶኔዥያው አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ አስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ መመሪያዎች አብራሪዎቹ እንዲያውቁ መደረጉን አመልክቶ የመመሪያው ይዘት ሙሉ በሙሉ በስልጠና ማኑዋል፣ በኦፕሬሽን ዝርዝር መመሪያዎች እና በዕለት ተዕለት ሥራዎች ዝርዝር መመሪያዎች እንዲካተት አድረጌአለሁ ብሏል።

የምስለ በረራ መለማመጃውን በተመለከተም አየር መንገዱ እንደሚለው "የቦይንግ 737 ማክስ ምስለ በረራ አሁን አከራካሪ የሆነውንና ለተከሰተው አደጋም ዋና ምክንያት ይሆናል ተብሎ የሚገመተውን የአውሮፕላኑ ሥርዓት መቆጣጠሪያ (MCAS) ላይ አለ የተባለውን ቴክኒካዊ ችግር ለማሳየት ታስቦ የተሠራ አይደለም" ይላል። ይህም ማለት የምስለ በረራ ስልጠና መውሰድና የቴክኒክ ችግሩ አራምባና ቆቦ ናቸው።

"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የአውሮፕላኑ ደህንነት ጥያቄ ላይ በመውደቁ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ፈተና ውስጥ ገብቷል። ድርጅቱ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ቢያሳውቅም ሁለት ሳምንት ለሚደርስ ጊዜ ጉዳዩ ከእራሱ ላይ ሊወርድ አልቻለም።

ስለአደጋው ምክንያት የተሟላና ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በፈረንሳይ የተጀመረው ምርመራ መጠናቀቅ የሚኖርበት ሲሆን ይህም ከስድስት ወራት በላይ ጊዜን እንደሚጠይቅ ባለሙያዎች አሳውቀዋል። ይህ ውጤት ሳይገለጽ የአደጋ መላምት ማስቀመጥ የአቪየሽን ሥነምግባር አይፈቅድም።

ያም ሆኖ ኩባንያዎች ህልውናቸውን ላለማጣት በእጅ አዙር የሚዲያ ጦርነት መክፈታቸው የሚጠበቅ ነው።

ቃለየሱስ እንደሚለው የእራስን ስምና ዝናን ለመታደግ ሲባል "እውነት የሚመስሉ ወይም የተወሰነ እውነት ያላቸው ግን ደግሞ ብዥታን የሚፈጥሩ መረጃዎች በቀጣይነትም መውጣታቸው አይቀርም።

ዋናው ነገር መሆን ያለበት ግን የተጣሰ ነገር አለ ወይ የሚለው ነው? በዚህም የቦይንግን የአሰራር መመሪያን ከጣሱ ቦይንግ ራሱ ዝም አይልም" ይላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋውንና ሠራተኞቹን በተመለከተ የሚወጡት የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳሳዘኑት ገልጾ፤ "ምርመራው የዓለም አቀፍ የአደጋ ምርመራ ሥነ ሥርዓትና ሕጎች መከተል ስላለበት ውጤቱን በትዕግስት እየተጠባበቀ" መሆኑን ጠቅሶ የመገናኛ ብዙኃን ስለአደጋው መንስዔ በግምት ላይ የተመሠረቱ ምክንያቶች በመስጠት የተሳሳተ መረጃ እንዳያቀርቡ ጠይቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ