ሰማይ ላይ ወልዳ አሥመራ የምትታረሰው ኢትዮጵያዊት

ጀነቲ ሁሴን በሆስፒታል ውስጥ በሕክምና እና በኢትዮጵያ ኢምባሲ ባልደረቦች ተከብባ Image copyright Ethiopian Embassy- Eritrea

ጀነቲ ሁሴን መሐመድ ትባላለች፤ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። ኑሮዋን የመሠረተችው ደግሞ ባሕር ማዶ፤ ሳዑዲ።

ቅዳሜ ዕለት ታዲያ በቤተሰቦቿ ተከ'ባ ለመውለድ፣ በሀገሯ እና በወገኖቿ መካከልም ለመታረስ በማሰብ፣ ከሳውዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ጓዟን ሸካክፋ አውሮፕላን ተሳፈረች።

አውሮፕላኑ የኤርትራ አየር ክልል ውስጥ እንደገባ ግን ያላሰበችው ነገር ገጠማት፤ ምጥ ፈትሮ ያዛት። ዕለቱ ቅዳሜ፣ ሰዓቱም ከማለዳው 1 ሰዓት ከሩብ ነበር።

"ከሳውዲ ስነሳ ደህና ነበርኩ" የምትለው ጀነቲ አውሮፕላን ላይ እወልዳለሁ ብላ እንዳላሰበች ለቢቢሲ ተናግራለች።

አውሮፕላን ላይ ከመውጣቷ በፊት ክትትል አድርጋ እንደነበር ስንጠይቃትም ከበረራ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጁምዓ [ዓርብ] ሆስፒታል ሄዳ ዶክተሮች በቅርብ አትወልጂም እንዳሏት ታስታውሳለች። በነገታው ምጧ ይፋፋማል ብሎ ያሰበም ኾነ ያለመ ማን ነበር?

አንዳንድ ጥያቄዎች ለ"108ኛው" ፓርቲ

ኢትዮጵያዊያን ቶሎ አያረጁም?

ጌዲዮ በዐቢይ ጉብኝት ማግስት

አውሮፕላኑ ከሳዑዲ ተነስቶ ቅድሚያ ጅዳ ሲያርፍ "የሆነ የመርገጥ ስሜትና ፈሳሽ ውሃ ሲፈሰኝ ተሰምቶኛል" ትላለች ጀነቲ፤ ሁኔታው የድንጋጤ ወይም የሌላ ህመም ነው ብላ በማሰብ ለማንም አልተነፈሰችም።

"በቅርብ እወልዳለሁ ብዬ ስላላሰብኩ ዝም አልኩ"

እነዚህን ምልክቶቿን ከራሷ ውጪ ለሌላ ሰው ያላዋየችው ጀነቲ አውሮፕላኑ ተነስቶ በረራ ሲጀምርም በዝምታዋ ፀናች።

ነገር ግን "ጢያራው ከተነሳ 10 ወይ 20 ደቂቃ በኋላ ጓደኞቼን አሞኛል፤ አስተናጋጆቹን ንገሯቸው አልኳቸው። አስተናጋጆቹም መጥተው ሽርት ውሃ መፍሰስ ምናምን ከሆነ ምጥ ነው ብለው ወደ ሆነ ቦታ ወሰዱኝ" ትላለች።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረው ቦታ ጥበት ለምጥ እንዳስቸገራት የምትናገረው ጀኒት ሊያስተኟት ሲሉ ሽርት ውኃዋ መፍሰሱን ታስታውሳለች። አስተናጋጆቹ በሁኔታው ተደናግጠው ባለሙያ ከተሳፋሪዎቹ መካከል እንዳለ ቢጠይቁም ባለመገኘቱ እራሳቸው እንደረዷት ትዝ ይላታል።

ይህ ሁሉ ሲሆን የነ ጀነቲ አውሮፕላን በአስመራ አየር ክልል እየበረረ እንጂ መሬት አልረገጠም።

መንታ በሰማይ ላይ

ብዙ ሰዎች ጀነቲ ልጆቿን የተገላገለችው በኤርትራ አስመራ እንደሆነ ነው የገባቸው። እውነታው ትንሽ ይለያል።

"የመጀመሪያዋ ልጄ አውሮፕላኑ ከማረፉ በፊት የተወለደች ሲሆን ሁለተኛዋ ግን አውሮፕላኑ አርፎ ሞተሩን ለማብረድ እየተንደረደረ ነበር የተወለደችው" በማለት መንታ ልጆች የታቀፈችበትን የሰማይ ላይ ድራማ በስሱ ታስታውሳለች።

Image copyright Ethiopian Embassy- Eritrea

'ስም አወጣሽላቸው?' ብለን ስንጠይቃት ነገሩን እንዳላሰበችበት በሚያሳብቅ አግራሞት፣ "...ወላሂ ማን እንደምላቸው ገና እያሰብኩበት ነው" ብላለች።

ጀኒት መንታ ስትወልድ የመጀመሪያዋ ነው። ከዚህ በፊት አንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆች አሏት። አሁን ምድር ላይ የተወለዱ ሦስት ልጆቿን ጨምራ በሰማይ ከተወለዱት ሁለቱ ጋር የአምስት ልጆች እናት ሆናለች።

ቅዳሜ ዕለት ልጆቿን አውሮፕላን ላይ በሰላም ከተገላገለች በኋላ በቀጥታ የተወሰደችው በአስመራ ከተማ ትልቅ ወደሚባለው ኦሮታ ሪፈራል ሆስፒታል ነው።

የሆስፒታሉ የሕፃናት ሐኪም ዶ/ር ዘሚካኤል ዕቁበም ጀኒት በአውሮፕላን ውስጥ በሰላም መውለዷን አረጋግጠው እነርሱ በፍጥነት በስፍራው በመድረስ ድህረ የወሊድ ህክምና እንደሰጧት ገልፀዋል።

ጀኒት ቅዳሜ፣ መጋቢት 14፣ ብትወልድም እስከዛሬ ድረስ ወደ ሀገሯ ያልተሸኘችው የሁለተኛዋ መንታ ጨቅላ የደም ማነስ ሁኔታ ስለነበራት ነው ብለዋል። አሁን የደምዋ መጠንና አመጋገቧም እየተስተካከለ መጥቷል ያሉት ዶ/ር ዘሚካኤል ጨቅላዋ ሙሉ ጤንነቷ ከተመለሰ በኋላ ሁሉም ወደቤታቸው እንደሚሄዱ አረጋግጠዋል።

በአስመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ የኤምባሲው ሁለተኛ ፀሐፊ የሆኑት አቶ ዘሪሁን መገርሳ ነግረውናል።

ለመሆኑ በተርሚናል አምጦ፣ በሰው አገር ሰማይ ወልዶ፣ በአሥመራ ታርሶ...የልጆቹ ዜግነት ከወዴት ነው?

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ