ልጃቸው ከመወለዷ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተጋቡት አሜሪካውያን

ከንቲባ ፒት ቡደጀጅ (መሀከል) ሜሪና ጋቤን ሲያጋቡ

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Pete Buttigieg

የአሜሪካ የሳውዝ ቤንድ ከንቲባ የሆኑትና በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት ለመውለድ 45 ደቂቃ ብቻ የቀራቸውን ጥንዶች አጋቡ።

ፒቲ ቡደጀጅ በኢንዲያና ግዛት የሳውዝ ቤንድ ከንቲባ ናቸው። ማለዳ 2፡15 ወደ ሥራ ለመግባት እየተጣደፉ በነበሩበት ሰዓት ሜሪና ጋቤ የተሰኙ ጥንዶች ድንገት አስቆሟቸውና እንዲያጋቧቸው ጠየቁ።

ሜሪ ድርስ ነፍሰጡር ናት። 3 ሰዓት ላይ ለመውለድ የሐኪም ቀጠሮ ይዛ እየተጠበቀች ያለች።

ጥንዶቹ ጋብቻቸውን ያሰቡበት አይመስልም፤ ቀለበት እንኳ አላዘጋጁም። ለከንቲባው ግን ይህ ከጥያቄ የሚገባ አልነበረም።

የፅህፈት ቤት ሰራተኞቻቸውን እማኝ እንዲሆኑ አድርገው አነስተኛ ሪባን እንደቀለበት አጥልቀው አጣመሯቸው።

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Pete Buttigieg

ከዚህ በኋላ ሜሪ ባሏን በጎኗ፣ በጣቷ ቀለበቷን አድርጋ ወደ ሆስፒታል በማምራት ሴት ልጅ በሰላም ተገላግላለች።

ከንቲባው "የስልጣን ዘመኔ ሲያበቃ የምናፍቀው እንዲህ አይነት ቅፅበቶችን ነው" ብለው የፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ከአዲሷ ጨቅላ ፎቶ ጋር ለጥፈዋል። አዲሷ ልጅንም የከተማችን አዲሷ ነዋሪ ሆና ተመዝግባለች ሲሉ ገልፀዋል።

አክለውም "አዲስ ተጋቢዎቹንና ጨቅላዋን ወደዚህ ግሩም አለም በመምጣትሽ እንኳን ደስ አለሽ፤ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።

የ37 ዓመቱ ወጣት ከንቲባ ፒት ቡደጀጅ ዲሞክራቶችን በመወከል ለ2020 የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን እያሟሟቁ ነው።

የዕጩዎች ምርጫን ካሸነፉ የመጀመሪያው ራሳቸውን በይፋ የገለጡ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ዕጩ ይሆናሉ ማለት ነው።