የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ከሥልጣን ወረዱ

የፕሬዝዳንቱን ከስልጣን መውረድ ዜና ተከትሎ አልጄሪያውያን ደስታቸውን ሲገልጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለበርካታ ሳምንታት ከተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ስልጣን መልቀቃቸውን በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በኩል ይፋ አድርገዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ቡተፍሊካ ተቃውሞ ቢበረታባቸውም ለአምስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ያላቸውን እቅድ ይፋ አድርገው ነበር። ፕሬዝዳንቱ የዛሬ ስድስት አመት ካጋጠማቸው ስትሮክ በኋላ ለሕዝብ የሚታዩት አልፎ አልፎ ነበር።

የፕሬዝዳንቱን ከስልጣን የመውረድ ዜና ተከትሎ በአልጄሪያ ዋና ከተማ፣ አልጀርስ መንገዶች በመኪና ጥሩምባ ጩኸት ደምቀዋል።

በርካታ በደስታ የሰከሩ አልጄሪያውያን የሀገራቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ ሲዘምሩ ታይተዋል።

አንድ ግለሰብ ለሮይተርስ እንዳለው "ይህ የፈጣሪ ፍቃድ ነው። መቶ በመቶ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንደሚኖር እተማመናለሁ። ይህ በጣም ወሳኝ ነው። የከዚህ ቀደም የስርዓቱ አገልጋዮች የነበሩትን በአጠቃላይ ከስልጣን ማውረድ አለብን፤ ያ ነው ፈታኙ ነገር"

የተቃውሞ መሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ከስልጣን የመልቀቅ ዜና ከመሰማቱ በፊት ቡተፍሊካ የሚያደርጉት ማንኛውም ውሳኔ ለውጥ አያመጣም በተቃውሟችን እንገፋበታለን ሲል ተደምጠው ነበር።

የመውረዳቸው ዜና ከተሰማ በኋላ ውሳኔው ወዲያውኑ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጧል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

በአልጀሪያ ህገ መንግስት መሰረት ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ፕሬዝዳንቱን የሚተኳቸው የሴኔቱ አፈጉባኤ ይሆናሉ።

የ82 ዓመቱ አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ ለስልጣን መወዳደራቸውን በመቃወም ነበር ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ የሰነበተው።

የተቃውሞ ሰልፉ ሲደረግ ፕሬዝዳንቱ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ህክምና እየተከታተሉ ነበር።

በወቅቱ የተቃውሞ ሰልፉን የጠሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አቀንቃኞች ሰልፉን የ20 ሚሊየኖች ጉዞ የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን አልጄሪያውያንም መንገዶችን እነዲያጥለቀልቁ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተቃውሞ ሰልፉ ላእ የተሳተፉት አብዛኞቹ ወጠዓቶች ሲሆኑ አዲስ መንግስት ተመስርቶ ማየት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።