ከሸዋ ሮቢት እስከ ሃርቡ ከፀጥታ ኃይሎች ውጭ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከለከለ

ብርጋዴል ጄኔራል ሰኢድ ትኩየ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media

ከሸዋ ሮቢት እስከ ሃርቡ ከተማ ድረስ ባለው ዋናው መንገድ ግራ እና ቀኝ 5 ኪሎ ሜትር ድረስ ከፀጥታ አስከባሪ ኃይላት ውጭ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከለከለ።

ይህ የተነገረው በሰሜን ሽዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመፍታት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ልዩ ኃይል እና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል የተውጣጣ ጥምር የፀጥታ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ መሆኑን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የ11ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ሰኢድ ትኩየ በትናንትናው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ፣ በሁለቱም ዞኖች በሚገኙ እና የፀጥታ ስጋት ባለባቸው 10 ወረዳዎች ከሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርጎ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

አክለውም ‹‹ችግሩ ከተከሰተ በኋላ የተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች በመግባታቸው በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም አሁንም ድረስ ግን ሕዝቡ ስጋቶች አሉበት›› ብለዋል።

ጥምር የፀጥታ ኃይሉ የፀጥታ ዕቅድ አውጥቶ የሕዝቡን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ፣ ተጎጅዎችን ለማቋቋም፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር እና አጥፊዎችን በመለየት ለሕግ ማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በመግለጫው ላይ እንዳስታወቀው በሁለቱም ዞኖች ለፀጥታ ስጋት ይሆናሉ ያላቸውን 12 የሚደርሱ ቦታዎች ለይቷል፡፡ በነዚህ ቦታዎች ላይም ጊዜያዊ እና ቋሚ ፍተሻ ይደረጋል ሲል ተናግሯል።

በመጨረሻም ከክልል እና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ውጭ በየትኛውም አካባቢ በግልም ሆነ በቡድን የሚደረግ ፍተሻ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል።

የተከሰተው ምን ነበር?

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዌ ሃረዋ ወረዳ በታጠቁ ኃይሎችና በአካባቢው ነዋሪ መካከል ለመጀመሪያ ግጭት የተቀስቅሰው መጋቢት 26 2010 ዓ.ም ነበር።

ግጭቱ በተፈጠረበት እለት ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል የሠላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ፣ ቢያንስ የሁለት የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።

ምክትል ኃላፊው በወቅቱ ግጭቱን በማድረስ የወነጀሉት "አካባቢውን ለማተራመስ አጀንዳ የያዘ፣ በዋናነት ከኦነግ አባላት ጋር ትስስር ያለው ኃይል" ያሉትን ነው።

ይህንን ተከትሎም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) "የራስን ጥፋት ለመደበቅ የኦነግን ስም ማጠልሸት ከተጠያቂነት አያስመልጥም፤ አሁንም ቢሆን ሰላማዊ ትግል ላይ ነው ያለነው፤ የአማራ ልዩ ኃይሉ ተግባር የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርን በማፍረስ ወደ ሌላ ዞን ለመቀላቀል የሚደረግ የድንበር ማስፋፋት ነው ብለን እናምናለን" ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ መግለጫ አውጥቷል።

ለተፈጠረው ችግር መጠየቅ ያለበትም ቡድኑን የሚቆጣጠረው የክልሉ መንግሥት እንጂ ኦነግ አለመሆኑንም በመግለጫው ጠቅሷል።

ይህ በከሚሴ የተጀመረው ግጭት ወደ አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴና በዙሪያቸው ባሉ አካባቢዎች ተሸጋግሮ የበርካታ ንፁኀን ሕይወት አልፏል፤ ንብረትም ወድሟል።

በወቅቱ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በግጭቱ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸውንና የዘረፋ ድርጊትም ተከስቶ እንደነበር ተናግረው ክስተቱ ከክልሉ ልዩ ኃይል አቅም በላይ በመሆኑ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እንዲገባ መደረጉንም አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት መግለጫ የሰጡ ሲሆን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የግጭቱን ምክንያት እና ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችን በተመለከተ በማጣራት ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ከዚህ በኋላ ነው በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜ/ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ "በክልሉ የጸጥታ መዋቅር የሚመራው የጸጥታ ኃይል ነው በዋናነት ችግር ያደረሰው" ሲሉ የተናገሩት።

የአማራ ክልል የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ምክትል ኅላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ በበኩላቸው "ልዩ ኃይሉም ሆነ የጸጥታ መዋቅሩ ተልዕኮውን በሚገባ የሚያውቅና የአማራ ክልል ህዝብን ደህንነት የሚጠብቅ እንጂ መልሶ የአማራን ህዝብ የሚጎዳበት ምክንያት የለውም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ገደቤ እንዲህ አይነቱ ሃሳብ በጣም የተሳሳተና የአማራን ህዝብ መብትም ታሳቢ ያላደረገ ነው በማለት "እዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀስ ኃይል መኖሩ ይታወቃል ማስረጃዎችም አሉን። የተፈጸመው ጥቃትም በአማራው ህዝብ ላይ እና በንጹሃን ላይ ነው። ይህን የፈጸመው ልዩ ኃይል ነው ማለት ምን ማለት ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የአማራና የኦሮሞ ክልል የፀጥታ አካላት በሁለቱ ክልሎች የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት አብረው ለመስራት በባህር ዳር ከተማ በተሰበሰቡበት ወቅት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።