በሰሜን ተራሮች ፓርክ በሄሊኮፕተር ውሃ እየተረጨ ነው

የእሳት ማጥፊያ ሂሊኮፕተር

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በድጋሚ የተከሰተውን እሳት ለማጥፋት ከደቡብ አፍሪካ የመጣችው ሄሊኮፕተር ትላንት ሥራ ጀምራለች።

ሄሊኮፕተሯ በደቡብ አፍሪካ የተመዘገበች ሲሆን ንብረትነቷ የኬንያ መሆኑን በሰሜን ተራሮች ፓርክ የህብረተሰብ እና የቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

ዛሬ ማለዳ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ አባተ ለቢቢሲ እንደገለፁት በትናንትናው እለት ከኬኒያ የመጣችው እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር አምስት ጊዜ በመመላለስ ርጭት አካሂዳለች።

9 አባላት ያሉት የእስራኤላውያን የእሳት አደጋ ሰራተኞች ቡድንም በትናንትናው እለት በስፍራው የደረሰ ሲሆን ከሄሊኮፕተር አብራሪው ጋር እሳቱን በተሻለ መልኩ እንዴት ማጥፋት ይቻላል የሚለውን ይመካከራሉ ብለዋል።

ሰሞኑን በድጋሚ የተቀሰቀሰውን እሳት ለማጥፋት በተደረገው ሥራ፣ ጓሳ ሳር ያለበትን የላይኛውን ክፍል በህብረተሰቡ ርብርብ ጠፍቷል ያሉት ኃላፊው ገደላማው የፓርኩ ክፍል አስቸጋሪ በመሆኑ ከትላንት ጀምሮ በሄሊኮፕተር የማጥፋት ሥራው ተጀምሯል ብለዋል።

ሄሊኮፕተሯ ውሃ የምትቀዳው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ከሚገኘው አፈራ ወንዝ ነው ያሉት አቶ ታደሰ፣ ነዳጅ ለመሙላት ደግሞ ጎንደር እንደምትመላለስ አስረድተዋል። በየበረራው መካከል የሚደረገው የቴክኒክ ፍተሻ እንዳለ ሆኖ በቀን ከስምንት እስከ አስር ጊዜ የውሃ ርጭት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ያለውን ሂደት ያስረዳሉ።

በዛሬው ዕለት የእሳቱ መጠን በከፍተኛ መጠን መቀነሱን የተናገሩት አቶ ታደሰ፤ እስራኤላውያን የእሳት አደጋ ሰራተኞች ዛሬ ጠዋት ቅኝት አከናውነው እሳቱ ቀላል መሆኑን እንደተናገሩ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ገዛኸኝ ከሆነ ባለሙያዎቹ እሳቱን በተሻለ ሁኔታ እንዴት መቆጣጠር ይቻላል የሚለው ላይ የሚሰሩ ሲሆን ከዚህ በኋላም በፓርኮች ተመሳሳይ የእሳት አደጋ እንዳይደርስ መከላከል የሚቻልበት መንገድ ላይ ይሰራሉ ብለዋል።

መንግሥት በሰሜን ተራሮች የተከሰተው የእሳት አደጋ ሰዎች እንደለኮሱት አምኗል ያሉት አቶ ገዛኸኝ አባተ እነማን ናቸው የሚለው በምርመራ ላይ ያለ ነው ብለዋል።

እሳቱ በፓርኩ ላይ ያደረሰው ጉዳት እስካሁን ያልታወቀ መሆኑን የገለፁት ቃል አቀባዩ "እስካሁን ድረስ ከብርቅዬ እንስሳቶቻችን መካከል አንድም እንዳልሞተ ነው የምናምነው" ሲሉ ተናግረዋል።