ከ40 በላይ ኢትዮጵያውያን ባህር ላይ መሞታቸው ተሰማ

ሰደተኞች Image copyright IOM

በያዝነው ወር ከጅቡቲ ወደ የመን ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጥማ ከ40 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተሰማ።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ትግራይ ክልል ውስጥ ከምትገኘው አጽቢ ወንበርታ ወረዳ ጉዞ የጀመሩ መሆናቸውም ታውቋል።

የወረዳዋ ነዋሪዎች የሆኑ ወደ አርባ የሚጠጉ የሟች ቤተሰቦችም ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ መርዶ ተረድተዋል።

ከእነዚህም መካከል ወንድሙን ያጣው ካልአዩ ገብረዮሃንስ አንዱ ነው። ወንድሙ ንጉስ ገብረዮሃንስ በጉዞው ወቅት የት እንደደረሰ በስልክ ይነግራቸው እንደነበር የሚገልፀው ካልአዩ፤ ነገር ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ እንዳቆመ ይናገራል።

እሱ እንደሚለው ከዚህ በፊት ወንድሙ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዞ ስምንት ወራት ቆይቶ ነበር። በሳዑዲ የመኖሪያም ሆነ የሥራ ፍቃድ ስላልነበረው በሳዑዲ ባለሥልጣናት ተይዞ ወደ ሃገር ቤት እንዲመለስ ተደርጎ ነበር።

‘ቤቴን ከ28 ስደተኞች ጋር እጋራለሁ’

የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን ሰቆቃ በየመን

ከሳዑዲ ከተመለስ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየው ለሦስት ቀናት ብቻ ሲሆን ተመልሶም ባለፈው መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ ጉዞ መጀመሩን ወንድሙ ያስረዳል።

ከትግራይ ክልል አጽቢ ወንበርታ ኮሚኬሽን ቢሮ ባልደረቦች የተገኘው መረጋ እንሚያመላክተው ወደ 60 የሚጠጉ ወጣቶች ከሳምንታት በፊት በእግራቸው በአፍራ ክልል አድርገው ወደ ጅቡቲ የተጓዙ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ለመግባትም በየመን በኩል ለማቋረጥ ሞክረዋል።

አቶ ብርሃኔ ትኩ የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፤ መጋቢት 28/2011 ዓ.ም. ላይ ወጣቶቹ ሲጓዙበት የነበረው ጀልባ ችግር ስላጋጠመው ባህር ውስጥ መስጠሙን ተናግረዋል።

አቶ ትኩ አደጋው መድረሱን ወላጆች ከአደጋው ከተረፉ እና ከአንድ ደላላ መስማታቸውን ያስረዳሉ።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም በደረሰው አደጋ የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። ክልሉ በሃዘን መግለጫው 40 የሚሆኑ ወጣቶች በአደጋው ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቅሷል።

የቤት ሰራተኞችን ለመላክ ከኩዌት ጋር ድርድር እንደሚያስፈልግ ኢትዮጵያ አስታወቀች

ኢትዮጵያዊያን በህጋዊ መንገድ ለሥራ መሄድ የሚችሉባቸው ሃገራት የትኞቹ ናቸው?

ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው ወደ የመን የሚሄዱ ጀልባዎች በተደጋጋሚ አደጋ የሚያጋጥማቸው ሲሆን ባለፈው የካቲት ወር ላይም ከጅቡቲ የተነሳ ጀልባ በመገልበጡ 47 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

በወርሃ ሰኔ ባጋጠመ ሌላ አደጋም ከሶማሊያ ባህር ዳርቻ ተነስቶ በመሄድ ላይ የነበረ ጀልባ ተገልብጦ 46 ኢትዮጵያውያን አልቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ እንዳስታወቀው በየወሩ 7000 ስደተኞች በዚሁ ተመሳሳይ መንገድ ባህር ለማቋረጥ ይሞክራሉ።