አልሲሲ እስከ 2030 ግብጽን ሊመሩ ይችላሉ

አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የግብፅ ፓርላማ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ማሻሻያያ አፀደቀ። በተሻሻለው ሕገ-መንግሥት መሠረት አልሲሲ እስከ 2030 ድረስ በመንበራቸው ላይ ሊቆዩ ይችላሉ።

አልሲሲ የሁለተኛ የምርጫ ዘመን ስልጣናቸው የሚያበቃው በ2022 ነው። አሁን በተሻሻለው ሕገ-መንግሥት መሰረት በሰላሳ ቀናት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ይጠይቃል። ይህ ደግሞ አራት ዓመት የነበረውን የስልጣን ዘመናቸውን ወደ ስድስት ዓመት ከፍ በማድረግ ለአንድ የስልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ እድል ይሰጣቸዋል።

የፓርላማው ውሳኔ የአልሲሲ የሥልጣን ዘመን ዘለግ ባለ ዓመታት መለጠጡ ብቻ ሳይሆን ዳኞችና አቃቤ ሕጉን የመሾም ልዩ ሥልጣንንም ሰጥቷቸዋል። ከአል-ሲሲ ባሻገር ለመከላከያ ሠራዊትም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ይሰጣል።

አልሲሲ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2013 በመፈንቅለ መንግሥት መሀሙድ ሙርሲን አስወግደው ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተቃውሞ ድምጾችን ሁሉ በመደምሰስ ድጋሚ ምርጫን 97 በመቶ ድጋፍ አግኝቼ አሸንፊያለሁ ብለው ካወጁ ጥቂት ዓመታት ተቆጥሯዋል።

የግብፅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሞላው በአልሲሲ ደጋፊዎች ሲሆን ሁል ጊዜም የአልሲሲን ቃል በማስፈፀም በተቃዋሚዎች ይከሰሳል።

ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አስተያየቱን የሰጠ አንድ የሕዝብ እንደራሴ እንዳለው "አልሲሲ ወሳኝ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የደህንነት እርምጃዎችን የወሰዱ ናቸው እናም የስልጣን ዘመናቸው ሊራዘምላቸውና የጀመሩትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊቀጥሉ ይገባል" ብሏል።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባሉ ኻሊድ ግን "እብደት ነው፤ ትልቅ የስልጣን ጥመኝነት" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የመረጃ መረብ ፍሰትን የሚከታተለው ተቋም የግብፅ መንግሥት ይህ ሕገ-መንግሥት እንዳይሻሻል የሚወተውቱና ፊርማ የሚያሰባስቡ 34 ሺህ ድረ ገፆችን ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ዘግቷል ሲል ይፋ አድርጓል። እነዚህ ወገኖች 250 ሺህ ፊርማ አሰባስበው ነበር።

በ2014 በሕዝበ ውሳኔ ጸድቆ የነበረው የግብጽ ሕገ መንግሥት 'አንቀጽ-140' ተመራጩ ርዕሰ ብሔር ከሁለት የአራት ዓመት የአገዛዝ ምዕራፍ በላይ በሥልጣን እንዳይቆይ ያስገድዳል።

ነገር ግን አሁን በፀደቀው ማሻሻያ ርዕሰ ብሔሩ ስድስት አመት በሥልጣን እንዲቆይ ያስችለዋል።