"ቱሪስቶችን እሳቱ ወዳለበት ቦታ አንወስድም" የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አስጎብኚዎች

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት በቱሪስት ፍሰቱ ለይ ተጸዕኖ እንዳልፈጠረ አስጎብኚዎች ገለጹ። "እስካሁን ያለው የቱሪስት ፍሰት ጥሩ ነው" ሲል በማስጎብኘት ስራ የተሰማራው ሸጋው አንዳርጋቸው ገልጿል።

"በስራችን ላይ ብዙም ተጸዕኖ አልፈጠረም" የሚለው አወቀ ነጋሽ በበኩሉ ጎብኚዎችን እሳቱ ወዳለበት ቦታ ግን አንወስድም ብሏል። አፈሩ መበላቱንና ለድንኳን መትከያነት አመቺ አለመሆኑን ደግሞ በምክንያትነት ያስቀምጣል።

ሸጋው በበኩሉ በእሳቱ የተቃጠለውን አካባቢ ማየት ጎብኚዎችን እና አስጎብኚዎችን በመንፈስ የሚጎዳ ከመሆን ባለፈ የሃገር ገጽታን ስለሚጎዳ እንደማያስጎበኙት ይናገራል። እሳቱ የተነሳበትን አካባቢ ባለማስጎብኘታቸው ጎብኚዎች የፓርኩን አጠቃላይ ገጽታ እንዳይመለከቱ እንቅፋት ፈጥሯል።

እሳቱ በተደጋጋሚ መነሳቱ በዘላቂነት ከሚፈጥረው ችግር ባለፈ ከዩኔስኮ ዓለም ቅርስነት እንዲወጣ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አወቀ ነጋሽ ገልጿል።

እሳት በየጊዜው በፓርኩ እንደሚነሳ ያስታወቁት የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው የአሁኑ እሳት ከሌሎቹ ጊዜዎች በስፋቱ ከፍተኛ ቢሆንም በጎብኚዎች ፍሰት ላይ ተጽዕኖ አለመፍጠሩን አስታውቀዋል።

በዋናነት የቱሪስት መስህብ የሆነው የፓርኩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ብርቅዬ የዱር እንስሳቱ መሆናቸውን አቶ አበባው ገልጸው በዚህ በኩል ጉዳት አለመድረሱ የማስጎብኘት ሥራው ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል።

ሚያዝያ ወር የጎብኚዎች ቁጥር እየቀነሰ የሚመጣበት ሲሆን የዘንድሮውም በተለመደው ሁኔታ በመሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።ዘንድሮ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።

ለአንድ ዓመት የተያዘውን ዕቅድ ከወዲሁ ማሳካት የተቻለ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 26600 ሰዎች ፓርኩን ጎብኝተዋል። እሳቱን ለማጥፋት ጥሩ ሥራ መሰራቱን የሚገልጹት አስጎብኚዎች ለቀጣይ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።