ኢትዮጵያ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት አዙሪት እንዴት ትውጣ?

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያላት መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የሁለት ወር ከስድስት ቀን ፍላጎትን የሚሸፍን እንደሆነና ይህም ለመድሃኒትና ለነዳጅ የሚውል እንደሆነ ከጥቂት ቀናት በፊት ተዘግቧል።

አገሪቱ የሁለት ወር ተኩል ብቻ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ነው ያላት ማለት ምን ማለት ነው? ለኢኮኖሚ ኤክስፐርቱ ዶ/ር አሰፋ አድማሴ ያነሳነው ጥያቄ ነበር።

አገሪቱ በመደበኛ ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ከሶስት ወር የሚበልጥ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ኖሯት አያውቅም።

"ያለው መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለሁለት ወር ብቻ የሚሆነው ማለት ያለውን አሟጠን እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም" በማለት በተጠቀሰው ሁለት ወር እና ጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ከውጭ በሚላክ ገንዘብ፣ በእርዳታ ፣ በብድርና በወጪ ንግድም የሚመጣ የውጭ ምንዛሬ ይኖራል ይላሉ።

ከውጭ እቃዎችን ለማስገባት የሚውል መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አስፈላጊ ቢሆንም አገሪቱ ለሁለት ወራትና ጥቂት ቀናት የሚሆን ነው ያላት ማለት የሚያሸብር ነገር እንዳልሆነ ያስረግጣሉ።

በርግጥም ክምችቱ ትንሽ ነው ስጋትም ያሳድራል ነገር ግን በዚሁ አበቃ ማለት አይደለም ይላሉ።

አገራት ምን ያህል ክምችት እንዲኖራቸው ይመከራል?

ምንም እንኳ በተፃፈ ህግ ባይሆንም እንደ አሰራር የአለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አገራ ከሶስት እስከ ስድስት ወር መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲኖራቸው ይመክራል።

ያነጋገርናቸው ሌላው የኢኮኖሚ ኤክስፐርት ዶ/ር እዮብ ተስፋዬ የሶስት ወር ክምችት በቂ ሊባል የሚችል ሲሆን ብዙ ጊዜ ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉት መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ከሶስት ወር በታች ሲሆን እንደሆነ ይገልፃሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የሶስት ወር ክምችት መያዝ ጥሩ እንደሆነ ቢመከርም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሶስት ወር ያነሰ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ይዞ መገኘትን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተላመደው እንጂ እንግዳው አለመሆኑን ነው።

በአስቸጋሪ፤ በመደበኛ ሁኔታም እውነታው ይህው ነው።

ለሶስት ወር የተባለውም መሻሻል እንጂ ሁልጊዜ ሶስት ወር ሆኖ መቅረትም ግን የለበትም።

የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ "በደርግ መውደቂያ፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የአስር ቀን ነበር" የሚሉት ዶ/ር እዮብ የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት የመጠባበቂያ ክምችቱ የሶስት ሳምንት ብቻ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

እናም የዛሬው ክምችት ከዚያ እያለ እያለ ያደገ ነው።

ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በጣም ውስን በመሆኑ ፣ ከውጭ ከሚላክ ገንዘብ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም የተሻሻለው በቅርብ በመሆኑና አሁንም ብዙው በጥቁር ገበያ የሚተላለፍ በመሆኑ ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የተሻሻለው ገና በቅርቡ በመሆኑ የመጠባበቂያ ክምችቱ ሊያድግ እንዳልቻለም ያስረዳሉ።

ነገር ግን የአሁኑን የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አነስተኛ መሆንን የተለየ የሚያደርገው የውጭ እዳ ጫና የበረታበት ጊዜ ላይ መሆኑ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ስለዚህም በዚህ የእዳ ጫና ምክንያት መጠባበቂያው ሳይነካ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች የሚቀርብ የውጭ ምንዛሬም ከፍተኛ እጥረት አለ። ይህ ከዚህ ቀደምም ሞልቶም አያውቅም።

መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አገልግሎ ምንድን ነው?

በዓለም አቀፍ ገበያ ባልተጠበቀ መልኩ የነገሮች ዋጋ ሲንር ፤ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ሳይታሰብ ቢጨምር ወይም በአገራት መካከል በተፈጠረ ግጭት የእቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር የሚፈጠር ችግርን ለመቋቋም የሚውል ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ለኢንቨስተሮች መተማመኛም ነው።

ኢንቨስተሮች መዋእለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ የሚያዩት የመጀመሪያ ነገር የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምን ያህል ነው? እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ አያያዙ ምን ይመስላል? የሚለውን እንደሆነ ዶ/ር እዮብ ይናገራሉ።

የውጭ ምንዛሬ ዋጋን በማስተካከል እረገድም ምን ይደረግ? የሚለውን አቅጣጫ ጠቋሚም ነው። ለምሳሌ የዶላር ዋጋ ከፍ ሲል ገበያውን ለማስተካከል ይረዳል።

ከውጭ ምንዛሬ እጥረት አዙሪት እንዴት ይወጣ?

አገሪቱን ለዓመታት እየተሽከረከረችበት ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመታደግ የወጪ ንግድ ላይ በርትቶ ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ አለ ብለው እንደማያምኑ ዶ/ር አሰፋ ይናገራሉ።

መንግሥትም ብዙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ያለው ለዚሁ ሲባል ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ከዚህ አንፃር የአገሪቱ የወጪ ንግድ ያለበት ሁኔታ መፍትሄ ለመሆን ተስፋ የሚጣልበት ነው ወይ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ ፤ የወጪ ንግድን እንደ ዋነኛ ዘርፍ ያለመቁጠር አዝማሚያም እየተፈጠረ ነው።

ጥቂት የማይባሉ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩት ፈልገውት ሳይሆን ይልቁንም ለማስመጣት ስራቸው እንዲረዳቸው ብለው ነው።

በአገሪቱ ሳይፈታ እየተሽከረከረ ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የዘላቂ ስትራቴጂ አስፈላጊነትን አፅንኦት የሚሰጡት ዶ/ር እዮብ ፤ ለወጪ ንግድ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ሊቀጥል ቢገባም የአቅጣጫ ለውጥ ያስፈልጋል ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ዋጋ መውረድ ከቡና ብዙ ማግኘት አልቻልንም የዚህ ዓመት አፈፃፀሙ ጥሩ አይደለም እያሉ ማለፍ ሳይሆን ይህ ባይሳካ ያንን እያሉ አማራጮችን ማስቀመጥ እንሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

እንደ ግብርና ፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ማእድን ሚኒስቴር ያሉ የተለያዩ መስሪያቤቶች በተናጥል የወጪ ንግድን እናበረታታለን ይላሉ።

ነገር ግን ይህ የተበታተነ አሰራርን ሰብስቦ አገሪቱ የተቀናጀ የወጪ ንግድ ስትራቴጂ እንዲኖራት ማድረግ ግድ ነው ይላሉ ዶ/ር እዮብ።

እንደ እሳቸው አስተያየት ከውጭ ከሚላክ ገንዘብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትና ለመጠቀምም የሚያዋጣ አካሄድ መከተል አስፈላጊ ነው ይላሉ። ምክንያቱም ብዙዎች ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ጥቁር ገበያው ነውና።

ቱሪዝም ትኩረት ይደረግበት የሚሉት ሌላ ዘርፍ ሲሆን "ተስፋ የተጣለበት ኢንዱስትሪ ፓርክስ እንደተባለለት ነው ወይ ብሎ መመርመር የሚያስፈልግም ይመስለኛል"ሲሉ ያክላሉ።

መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ተመንን ገበያው እንዲወስን ማድረግን ቀጣይ አቅጣጫ አድርጎ ያስቀመጠ መሆኑን በተመለከተም በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታትም የሚሳካ እንደማይመስላቸው ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።