የጌዲዮ ተፈናቃዮች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል

በመጠለያዎቹ ውስጥ በርካታ ነብሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ይገኛሉ
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በአሳሳቢ የምግብ እጥረት ውስጥ ይገኛሉ አለ።
በመጋቢት ወር የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በአንድ መጠለያ ስፍራ ብቻ በሚገኙ ሕፃናት ላይ ያየውን የምግብ እጥረት "ድንገተኛ ከሚባለው ወለል በላይ ያለፈ" ነው ብሎታል።
አክሎም ቡድኑ በምግብ እጥረት እጅጉን የተጎዱ ነብሰ ጡር እናቶችንም መመልከቱን አትቷል።
"የመጠለያ ጣቢያዎቹ እጅጉን የተጨናነቁ መሆናቸውን በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ላይ መገኘት እንዲሁም ተፈናቃዮቹ ወረርሽኝ ሊከሰት በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ መኖራቸውን ተመልክተናል። ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ቀያቸውን እንዲለቁ መሆኑ ጤናቸው አስጊ በሆነበት ሁኔታ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።" ብለዋል በስፍራው ያሉት የድንበር የለሽ ሐኪሞች ማህበር የመስክ ባለሙያና አስተባባሪ ማርከስ ቦይኒንግ።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር የተፈናቃዮቹን የሚያገኙትን ምግብ ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።
የመፈናቀሉ መንስዔ ምንድን ነው?
ለአሁኑ ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት የሆነው መፈናቀል የጀመረው፤ ባለፈው ዓመት በጉጂ እና በጌዲዮ ተወላጆች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ፤ በሁለቱም ማህበረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት ሰዎች መሞታቸው፣ ቤቶች መቃጠላቸው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀዬያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ተዘግቦ ነበር።
ይህን ተከትሎም ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዱ። ብዙ የጌዲዮ ተወላጆችም ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው ጌዲዮ ዞን ወደሚገኙ አካባቢዎች ገብተው መጠለል ጀመሩ።
ከጉጂዎች በኩልም የተፈናቀሉ እንዳሉም ይነገራል።