የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከቃጠሎው በኋላ

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ አጋጥሞት ያውቃል። እንዲህ እንዳሁኑ ያለ ሲገጥመው ግን የመጀመሪያው ነው። እሳቱ ከአንድ ሺህ ሔክታር በላይ የሆነውን የፓርኩን ክፍል አውድሟል።

ፓርኩ 43 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን አንዱ ቀበሌ ላይ ብቻ ቃጠሎው እንደደረሰ የአካባቢው ኃላፊዎች ይናገራሉ። ይህ በአለም የቅርስ መዝገብ ስሙ የሰፈረ፣ የእነ ዋሊያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ መኖሪያ ብሔራዊ ፓርክ እየተቃጠለ ነውን የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን እሳቱን ለማጥፋት የአቅማቸውን ሲያደርጉ ነበር።

በመጨረሻም ከኬኒያ በተገኘ የእሳት ማጥፊያ ሂሊኮፕተርና፣ ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች ድጋፍ እሳቱ መጥፋቱ ተነግሯል።

የአሁኑ እሳት በምን ተለየ?

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ላቀው መብራት በተደጋጋሚ በፓርኩ ውስጥ እሳት ሲነሳ በማጥፋቱ ሥራ ላይ ተሳትፈዋል። የአሁኑ "ገደል ውስጥ ነው" ሲል ልዩነቱን ያስረዳሉ። ቀደም ሲል የሚነሱ እሳቶችን በአፈርና በውሃ ማጥፋት በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደ ነው። ይኼኛው ግን የአካባቢው ነዋሪዎች በቀላሉ ከሚደርሱበት ቦታ አልነበረም ሲነድ የነበረው። "አብዛኛው ሰው ገደላማው የፓርኩ ክፍል የመግባት ልምድ የለውም" የሚሉት አቶ ላቀው ሜዳማውን ክፍል መቆጣጠር መቻላቸውን ግን ይገልጻሉ።

አቶ ደሴ ብርሃን ደግሞ ሌላም ምክንያት ያነሳሉ፤ የስልክ ኔትዎርክ አለመኖርን። "እሳቱ በጀመረባቸው ሁለት ቀናት የስልክ ኔትዎርክ አለመኖሩ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል" ይላሉ። ከዚህ ቀደም በፓርኩ እሳት ሲነሳ ሰዎች ስልክ ደውለው ህብረተሰቡን በማስተባበር የማጥፋቱ ሥራ ይከናወናል።

"እሳቱ ለሶስት ቀናት ከፍተኛ ነበር" የሚሉት ደግሞ የፓርኩ ህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሠ ይግዛው ናቸው። እሳቱ የተነሳበት አካባቢ ከፍታ ያለው በመሆኑ እና ንፋሱም ከፍተኛ መሆኑ በፍጥነት እንዲስፋፋ እና ወደ ገደላማው አካባቢ እንዲዛመት ምክኒያት ነበር ብለዋል።

በእንስሳቱ ላይ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ?

እንደኃላፊው ከሆነ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው የፓርኩ ክፍል በእሳቱ ምክንያት ተቃጥሏል።

ከ90 በመቶ በላይ በእሳቱ ጉዳት የደረሰበት ክፍል ደግሞ ጓሳ የተባለው የሳር ዓይነት ነው። አነስተኛ መጠን ያለው የፓርኩ ደንም ከጉዳት አላመለጠም። በፓርኩ እሳት ለማጥፋት የተሰበሰቡ ሰዎች በአደጋው የፓርኩ መለያ የሆኑት እንደጭላዳ ዝንጀሮ እና ዋሊያ ያሉት የዱር እንስሳት አለመሞታቸውን በእፎይታ ያነሳሉ።

ይህ ግን ለሁሉም እፎይታን የሚሰጥ አይደለም።

ስጋት ካለባቸው መካከል የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደርቤ ለቅሲዮስ አንዱ ናቸው። "በተዘዋዋሪም ቢሆን በእንስሳቱ ላይ ጉዳት ደርሷል" ይላሉ። በእሳቱ ምክንያት የጓሳ ሳር እና አይጦች መቃጠላቸው ተረጋግጧል። እነዚህ ደግሞ በዋነኝነት የቀይ ቀበሮ እና የዋሊያ ምግቦች ናቸው። ለዚህም ነው አቶ ደርቤ እንስሳቱ በተዘዋዋሪም ቢሆን በእሳቱ ተጎድተዋል የሚሉት።

እንስሳቱ ወደሌላኛው የፓርኩ ክፍል እንዲሸሹም ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

እሳቱስ በጎ ጎን አለው?

በእንስሳቱ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ብቻ መታየት የለበትም የሚሉ ግን አሉ። እነዚህ ወገኖች እሳት መኖሩ ጥቅምም አለው ሲሉ ይከራከራሉ።

"እሳት በራሱ አንድ የአስተዳደር (ማኔጅመንት) ዘዴ ነው" ይላሉ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ግርማ ቲመር።

የፓርኩ ሳር በእሳት ቢቃጠል ለብዝሃ ህይወቱ ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደሆነ በመግለጽ። ይህንን ሲያስረዱም "ሣሩ በየጊዜው እየተቃጠለ አዲስ ሣር እንዲበቅል ቢደረግ በምግብ የበለጸገ እና ምርታማ ሣር ለእንስሳቱ ይኖራል" ይላሉ።

ይህ ግን የሚሆነው በቁጥጥር ስር መዋል የሚችል፤ በብዝሃ ህይወቱ እና በእንስሳት ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ በጥናት ሲረጋገጥ መሆኑን ያስረዳሉ።

የአሁኑም እሳት አስቸጋሪ የሆነው ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ነው ይላሉ አቶ ግርማ።

የአካባቢው ህብረተሰብ ይህንን ዕውቀት ያውቀዋል። ደረቁ ሳር ተቃጥሎ ለከብቶቻቸው አዲስ እና የበለጸገ ሳር ለማግኘት ሲሉ ያስጀመሩት ቃጠሎ ለዚህ አደጋ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውንም ያስቀምጣሉ።

በዚህ ረገድ ፓርኩም ሆነ ባለስልጣኑ በተቀናጀ፤ ከቁጥጥር ውጭ ባልሆነ እና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ሳሩን በየጊዜው ቢያቃጥሉ ለዱር እንስሳቱም ሆነ ለብዝሃ ህይወቱ ከፍ ያለ ጥቅም ያስገኛል ሲሉ ሃሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

የውጭ ሃገር ባለሙያዎቹ ምን አከናወኑ?

እሳት፣ ተፈጥሮ ራሱን እንዲያድስ የሚያግዝ ዘዴ ነው ሲሉ እሳቱን ለመከላከል ከእስራኤል የመጡት ባለሙያዎችም ያስረዳሉ።

ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ከእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከል ከመጡት ዘጠኝ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ኤሪያል ናቸው።

"በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እስካላደረሰ ድረስ" እሳት ጠቀሜታም አለው ሲሉ ይገልጻሉ።

እንደባለሙያው ከሆነ እሳቱን ለመቆጣጠር በተከናወነው ሥራ ውስጥ ቡድኑ የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል። "በቀረቡት የእሳት አደጋ መከላከያ መሣሪዎች እንዴት መስራት አንደሚቻል አሳይተናል" ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ የተመዘገበችው እና ባለቤትነትዋ የኬንያ የሆነችው የእሳት መከላከያ ሄሊኮፕተርም በሙሉ አቅሟ እንድትሠራ የእስራኤላውያኑ ድጋፍ ትልቅ ነበር።

ሄሊኮፕተሯ ቀደም ሲል እሳት ለማጥፋት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ውሃ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በማምጣት ወደ አደጋው ቦታ ለመድረስ 30 ደቂቃ ይፈጅባት ነበር።

ውሃ በቦቴ አደጋው በደረሰበት አቅራቢያ በማስመጣት የሄሊኮፕተሯን ምልልስ ከአስር ደቂቃ በታች ከማድረግ ባለፈ ነዳጅ ለመቆጠብም ባለሙያዎቹ አግዘዋል።

"ሁለት ባለሙያዎቻችን እሳቱ ያለበት ጉድጓድ ውስጥ በመግባት ሄሊኮፕተሯ ውሃ በትክክለኛው ቦታ እንድትደፋ አድርገናል" ሲሉ አሪየል ያስረዳሉ።

እሳቱ ጠፍቷል ለማለት ለምን አስቸገረ?

ይህ ሁሉ ሥራ ተከናውኖ ግን እሳቱ ጠፍቷል ለማለት ብዙዎች ሲቸገሩ ተስተውሏል።

'እሳቱ ጠፍቷል' የሚለውን መረጃ ለመስጠት መገናኛ ብዙሃን፤ ትልቁን ዜና ለመካፈል ደግሞ ህብረተሰቡ በጉጉት ሲጠብቅ ቆይቷል።

በተለይ ደግሞ ከማክሰኞ ጀምሮ እሳቱ ጠፋ የሚል መረጃ ለማግኘት በጉጉት የሚጠብቁት መገናኛ ብዙሃን የሚፈልጉትን አላገኙም።

"እሳቱ ጉዳት በማያደርስበት በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነስ ባለፈ በቁጥጥር ስር መዋል በሚችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል" ሲሉ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ገልጸዋል።

ይህ አገላለጽ የዋና አስተዳዳሪው ብቻ አይደለም፤ የሌሎችም ስለፓርኩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጭምር እንጂ።

ለዚህ ደግሞ ምክንያት የሆነው ከማክሰኞ ጀምሮ በፓርኩ ውስጥ የእሳት ነበልባል ባይታይም በጣም አነስተኛ የሚባል ጭስ መኖሩ ነው።

ይህ ደግሞ የመሬት ውስጥ (ሰርፌስ ፋየር) የሚባለው ዓይነት እሳት በመሆኑ ነው። ይህ ዓይነቱ እሳት በጊዜ ሂደት ሊጠፋ ወይም ደግሞ በነበልባል መልክ በመነሳት ድጋሚ አካባቢውን ሊያቃጥል የሚችል ነው።

ይህ ዓይነቱ እሳቱ በገደላማው የፓርኩ ክፍል በመከሰቱ አለ እንዳይባል የሚታይ ነበልባል አለመኖሩ ጠፍቷል እንዳይባል ደግሞ ጭስ እየታየ በመሆኑ በግልጽ ስለጉዳዩ ለመናገር አዳጋች አድርጎታል።

ይህንን ለመወሰን ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፤ ባለሙያዎችም ሆኑ የፓርኩ ኃላፊዎች እሳቱ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል እንዳይሉ ያደረጋቸው።

እንደኤሪያል ከሆነ እዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ላለመግባት ዋነኛው መፍትሔ የዓለም ቅርስ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የእሳት መከላከል ቡድን ማቋቋም ነው።

እንደባለሙያው ከሆነ "የእሳት መከላከል ቡድን መቋቋም አደጋ ቢፈጠር እንኳን ስጋት ከማስከተሉ በፊት በፍጥነት ለመከላከል ያስችላል።"

ለእነአቶ ላቀውም የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለአካባቢው ስነምህዳር መጠበቅ የሚረዳቸው ፓርክ ተመሳሳይ ችግር አንዳይከሰትበት ቀድሞ መሥራቱ ለነገ የማይባል ነው ።