የካቢኔው ሽግሽግ ምን ያመላክታል?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ለማ መገርሳ፣ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ

የፎቶው ባለመብት, Social Media

በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በካቢኔያቸው ላይ ያደረጉትን ሹም ሽር ፓርላማው አፅድቋል።

በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ኢንጂነር አይሻ መሀመድን በመተካት የመከላከያ ሚኒስትር፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)ን በመተካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።

ከመከላከያ ሚኒስትርነት የተነሱት ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ አቶ ጃንጥራር ዐብይን ተክተው በቀድሞው ቦታቸው ማለትም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትርነት ተመድበዋል።

ምክር ቤቱም ሹመታቸውን በአንድ ተቃውሞ፣ በአምስት ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ከዚህም በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአቶ ለማ መገርሳ ምትክ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾመዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ የዛሬውን ጨምሮ ሦስተኛ ሹም ሽር ወይም የካቢኔ ሽግሽግ አድርገዋል።

የዛሬው ሹም ሽር ይፋ ከተደረገ በኋላ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አዲሶቹ ተሿሚዎች በተሰጣቸው ቦታ በአግባቡ ለማገልገል ሙያዊ ብቃት አላቸው? ከሹመታቸው ጀርባ ያለው ፖለቲካዊ አንድምታስ ምንድን ነው? የሚሉት ይገኙበታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግና ፌደራሊዝም መምህር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የካቢኔ ሽግሽግ መደረጉ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የሚጠቁመው አለ ይላሉ።

"ፖለቲካዊ ትርጉሙ አለመረጋጋት መኖሩን የሚያሳይ ነው። ኢህአዴግ ግንባር እንዲሁም የተለያዩ የብሔር ተኮር ፖለቲካ ድርጅት ስብስብ በመሆኑ የነሱን ይሁንታ የማግኘት ነገር በጣም ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን የሚወስኑት ወይም ደግሞ ለሳቸው የሚረዷቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች በራሳቸው መንገድ መሾም የማይችሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ወጣ ገባነቱ እየታየ ያለው በዚህ ምክንያት ነው" ይላሉ።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍስሐ፣ የአዲሶቹ ሚንስትሮች ሹመት ከሙያዊ ብቃት ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታው ያመዝናል ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ትልቅ እንዲሁም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዲፕሎማሲ እውቀት የሚያስፈልገው እንዲሁም የሀገር ደህንነትንም ጥያቄ የያዘ ቦታ ነው። የአሁኑን ተሿሚ በማየም "ለቦታው ይመጥናሉ ብዬ አላስብም። በአቅም ሳይሆን በፖለቲካዊ ኃይል አሰላለፍ ነው" ይላሉ።

በተቃራኒው የመከላከያ ሚኒስትሩ የኤታማዦር ሹም ስላለው፤ የሚመራው ያው አካል በመሆኑ እንደ ትልቅ ቦታ ባይቆጥሩትም "በኢትዮጵያ የማይናቅ ቦታ ነው" ይላሉ።

ዶ/ር ሲሳይና ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስትሯ ኢ/ር አይሻ በሙያቸው ስለመሾማቸው ይስማማሉ።

አቶ ገዱ በውጪ ጉዳይ እንዲሁም በዲፕሎማሲ ዘርፍ ልምድ እንደሌላቸውም ይናገራሉ። በመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ ጉዳይ ዶ/ር ሲሳይ ከረዳት ፕሮፌሰር መኮንን የተለየ ሀሳብ አላቸው።

"ቀደም ሲል በፀጥታ ቦታዎች ላይ በኃላፊነት እንዲሁም በባለሙያነት እንደመሥራታቸውና የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን የመከላከያ ሚኒስትሩን በብቃት ይይዛሉ ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

በሚንስትሮች ሹም ሹር ወቅት በተደጋጋሚ የሚሰነዘረው ትችት አንድ ሚንስትር የተሾመበትን ዘርፍ አውቆና ተደርቶ መሥራት ሳይጀምር ወደሌላ መሥሪያ ቤት ሲዘዋወር በሥራው ላይ ተጽዕኖ የማሳደሩ ነገር ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደረገው ሽግሽግ ዛሬ ከሕዝብ እንደራሴዎች ጥያቄም ተነስቶበታል።

"ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሚኒስትር አንድ ተርም መቆየት አለበት። ሹመቱ ጎርፍ ሆነ" አንድ የፓርላማ አባል የሰጡት አስተያየት ነበር።

ምሁራኑም ስለሽግሽጉ ጉዳይ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ዶ/ር ሲሳይ እንደሚናገሩት አንድ ተሿሚ ሥራውን ለመምራት ተዘጋጅቶ ሳለ፣ ከተሰጠው ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቢሸጋሸግ እንደገና አዲሱን ሹመት ለመልመድ ጊዜ ያስፈልገዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደረግ ሽግሽግ መቼ እነሳ ይሆን? የሚል ጥያቄ በማጫር አለመረጋጋት ይፈጥራልም ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን አመራሮች ሳይገመገሙና የተወሰነ ጊዜ ሳይቆዩ በተደጋጋሚ እንዲለዋወጡ መደረጋቸው "በአገሪቱ ትልቅ አለመረጋጋት እንዳለ ያሳያል" ይላሉ።

ሀሳባቸውን የሚጋሩት ዶ/ር ሲሳይም በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የካቢኔ ሽግሽግ መደረጉ "አለመረጋጋት መኖሩን ያሳያል" ይላሉ።