የይለፍ ቃልዎ 123456 ወይስ 'ሊቨርፑል'?

ብዙዎች የይለፍ ቃላቸው ከሚያደጉት "ሊቨርፑል" ይገኝበታል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የይለፍ ቃልዎ ወይም 'ፓስወርድዎ' ምንድን ነው? እንገምት እስኪ. . .

123456 ይሆን? ወይስ 123456789?

ምናልባትም እርስዎን ጨምሮ ሚሊዮኖች የይለፍ ቃላቸው 123456 እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል።

የእንግሊዝ የመረጃ ደህንነት ተቋም በሠራው ጥናት መሰረት 123456 የበርካቶች የይለፍ ቃል ሲሆን፣ 123456789 እንዲሁም 1111111 'ፓስወርዳቸው' ያደረጉትንም "ቤቱ ይቁጠራቸው" ተብሏል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በርካቶች እጅግ ሚስጥራዊ መሆን ለሚገባቸው መረጃዎቻቸው የይለፍ ቃል የሚያደርጉት በቀላሉ ሊገመት የሚችል ቁጥር ወይም ቃል ነው።

ማንም ሊገምተው የሚችል የይለፍ ቃል መጠቀም በቀላሉ ለኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (ሀከርስ) ያጋልጣል።

በጥናቱ ይፋ እንደተደረገው መረጃቸው ከተመዘበረባቸው ግለሰቦች አብዛኞቹ የይለፍ ቃላቸው 123456 ሲሆን፣ ወደ 23 ሚሊየን ሰዎች የይለፍ ቃላቸው 123456 ነው።

የእንግሊዝ የመረጃ ደህንነት ተቋም፤ ሰዎች በቀላሉ ማስታወስ የሚችሉት ነገር ግን ሌላ ሰው ሊገምተው የማይችል የይለፍ ቃል በመጠቀም መረጃቸውን መጠበቅ አለባቸው ብሏል።

ብዙዎች አሽሊ፣ ማይክል፣ ዳንኤል፣ የሚሉ ስሞችን 'ፓስወርዳቸው' ከማድረጋቸው ባሻገር 'ሊቨርፑል' እና 'ቸልሲ' የይለፍ ቃላቸው የሚያደርጉም አሉ። የሙዚቃ ባንድ መጠሪያ እንዲሁም የራሳቸውን ስም የይለፍ ቃላቸው የሚያደርጉም ጥቂት አይደሉም።

የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች በተበራከቱበት በዚህ ዘመን የይለፍ ቃልን ማጠንከር አንዱ ራስን የመከላከያ መንገድ ነው ተብሏል።

ታዲያስ የይለፍ ቃልዎን ለመቀየር አላሰቡም?