"ከእንቅልፌ ስነሳ የፊቴ አንዱ ክፍል ከሌላኛው በላይ ተልቆ ነበር"

'ደርማል ፊለር' ከንፈርና ጉንጭ ለማሳደግ የሚጠቀሙበት ብዙዎች ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Rachael Knappier

ሰዎች ራሳቸውን ለማስዋብ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

ባለንበት ዘመን 'ውብ' የሚባለውን ሰው መስፈርት ለማሟላት የሚደረገው ጥረት መስመር ስቶ ሕይወት እየቀጠፈ ነው።

ከንፈር፣ ዳሌ፣ መቀመጫና ሌላም የሰውነት አካላቸውን 'አይነ ግቡ' ለማድረግ ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ የሞቱ በርካቶች ናቸው።

ነገሩ ያሳሳበው የእንግሊዝ መንግሥት ከሚቀጥለው ወር አንስቶ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ሊጀምር መሆኑን ይፋ አድርጓል። የሀገሪቱ መንግሥት ሰውነት ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ተጸእኖም ሊያስከትል እንደሚል ዜጎቼን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ ብሏል።

'ፊቴ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ነበር'

ለዚህ ጽሁፍ ስንል ግሬግ የሚል ስም የሰጠነው ግለሰብ፤ የተሸበሸበ ፊቱን ሞልቶ ለማስተካከል ቆዳ ስር የሚጨመር 'ደርማል ፊለር' አዘውትሮ ይጠቀም እንደነበረ ይናገራል።

ከንፈርና ጉንጭ ለማሳደግ 'ደርማል ፊለር' የሚጠቀሙ ብዙዎች ናቸው።

ግሬግ ከ 'ደርማል ፊለር' በተጨማሪ 'ቦቶክስ' ማለትም ሰዎች ፊታቸው ውስጥ የሚጨምሩት ምርት ገዝቶ ይጠቀም ነበር።

እነዚህን ምርቶች ፊቱ ላይ በተደጋጋሚ ከመጠቀሙ የተነሳ ፊቱ ከጥቅም ውጪ ሆኖ እንደነበረ ይናገራል።

ራስን በራስ በስሪንጅ በመውጋት የሚወሰዱ ኬሚካሎች ኢንፌክሽን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በጣም ከከፋ አይን ሊያጠፉም ይችላሉ።

'በጣም ያማል'

ግሬግ አንድ ቀን ከእንቅልፉ ሲነሳ አንዱ የፊቱ ክፍል ከሌላው በልጦ አገኘው። ኬሚካሉ ኢንፌክሽን ፈጥሮበት ነበር።

"ከእንቅልፌ ስነሳ የፊቴ አንዱ ክፍል ከሌላኛው በላይ ተልቆ ነበር። በጣም ያማል። እርዱኝ ብዬ ለመጠየቅ እንኳን አሳፍሮኝ ነበር"

ግሬግ 'እኔን ያየ ይቀጣ' ሲል ይመክራል።

የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ባለሙያዋ ኑጌት እንደሚሉት ብዙዎች የሚጠቀሟቸው ኬሚካሎች በህክምና ባለሙያ ያልታዘዙ ናቸው።

'ሴቭ ፌስ' የተባለው የህክምና ባለሙያዎች መዝጋቢ ተቋም እንደ አውሮፓውያኑ ከ2017 እስከ 2018፤ 934 ፍቃድ የሌላቸው ግለሰቦች በዘርፉ ተሰማርተው አግኝቻለሁ ብሏል።