የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት፡ «ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለ በረከት አናግረውናል»

አቶ በረከት ስምዖን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጥረት ኮርፖሬት የሃብት ብክነት የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሣ የተያዙት ከወራት በፊት ቢሆንም በአማራ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይፋ ክስ የተመሠረተባቸው ግን ሚያዝያ 14፣ 2011 ዓ. ም. ነው።

በተለይ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሠ ካሣ በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ወዲህ ስለግለሰቦቹ ብዙ ተብሏል። በተለይ አቶ በረከት ስላለፈው እና አሁን ስላሉበት ሁኔታ ምን ያስቡ ይሆን? ባለቤታቸው ወ/ሮ አሲ ፈንቴ ይናገራሉ።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት እንዴት እንደተያዙ ሊያስታውሱን ይችላሉ?

ወ/ሮ አሲ፦በረከትና አቶ ታደሰ በአንድ ቀን ነው የተያዙት። ጥር 15 ቀን ከጥዋቱ በግምት 12፡30 አካባቢ ነበር። በር ሲንኳኳ አልሰማሁም፤ ልጄን ትምህርት ቤት ለመውሰድ እየተዘጋጀሁ ነበር። ሊይዙት እንደመጡ ስሰማ እውነት አልመሰለኝም ነበር። እነሱ [አዴፓ] እሱን ለመያዝ ያሰቡበት ጊዜና በትክክልም የያዙበት ጊዜ በጣም ክፍተት ነበረው። ባላሰበውና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ነው መጥተው የወሰዱት።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት ሊያዙ እንደሚችሉ መረጃ ነበራቸው ማለት ነው?

ወ/ሮ አሲ፦ እንግዲህ ከዚያ በፊት በሚድያ እነሱ [አቶ በረከትና አቶ ታደሰ] ሳያውቁ ከአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ መታገዳቸው ተሰማ። ከዚያ በፊት ግን የሚመለከታቸው የፓርቲው ሰዎች ተሰብስበው ሲገመግሙ ጉዳዩ የማያስጠይቃቸው መሆኑን አስረግጠው ነበር፤ በፖለቲካ ውሳኔ ደረጃ ማለት ነው። ቢሆንም እነ በረከት ባልተገኙበት ከማዕከላዊ ኮሚቴ መወገዳቸው ተሰማ። ይህ ማንም ያልጠበቀው ነበር። በረከትም አልጠበቀውም ነበር። ምክንያቱም በግምገማው ላይ በረከት ቦርድ ሊቀመንበር [የጥረት ኮርፖሬት] እንጂ 'ኦፕሬሽናል' ሥራዎች ላይ አይሰማራም ብለው ነበር። አልፎም እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የቦርድ አባላት ፊርማ ያረፈበት ሥራ ስለሆነ የአሠራር ድክመት እንጂ በከባድ ሙስና አያስወነጅልም ተብሎ ነበር። ይህንን ተከትሎ በረከት በሚድያ ነገሩን አብራርቶ መግለጫ ሰጥቷል። ያው በተለያየ ጊዜ ሊከሱ እንደሚችሉ 'ኢንፎርማሊ' እንሰማ ነበር። የመክሰስ ያለመክሰስ መብቱ ያለው በነሱ እጅ ነው። መቼ ነው የሚለውን ግን ያው አናውቅም ነበር። እና ድንገተኛ ነበር።

ቢቢሲ፦ የተያዙት ቦሌ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው። ወደ ባሕርዳር የተወሰዱት እንዴት ነበር?

ወ/ሮ አሲ፦ መጀመሪያ ፖሊሶቹ ሲመጡ የፌዴራል ናቸው ብሎ ነው ያሰበው። ግን መጥሪያው የታዘዘው በአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። ይሄንን እሱ አልተቀበለውም፤ ምክንያቱም የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ስለነበር። ተከሶበታል የተባለው ነጥብም ትክክል አይደለም ብሎ ተከራከረ። ወደቤቱ መመለስ አልቻለም፤ ምግብም አልበላም፤ መድሃኒትም አልወሰደም ነበር። ለሁለት ሰዓት ያህል ተከራከረ። እኔ ከጎኑ ስለነበርኩ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየደወልኩ እርዳታ ለማግኘት ሞከርኩ። ማናቸውም ለማናገር ፍላጎትም ዝግጁነቱም አልነበራቸውም። የ13 ዓመት ልጃችን ይህ ሁሉ ሲሆን እዚያው ነበረች። መጨረሻ ላይ እነዚህ የታዘዙ ፖሊሶች ስለሆኑ መፍትሄ አይመጣም፤ እንደውም እዚያው ሄጄ እራሴን ነፃ አወጣለሁ ብሎ ወሰነ። ከዚያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አውሮፕላን ከታደሰ ጋር ወደ ባህርዳር ተወሰዱ ማለት ነው። ከዚያ ባህርዳር ዘጠነኛ ፖሊስ ጣብያ ሄዱ። በቀጣዮቹ ቀናት በተደራጁ ወጣቶች እንዲሰደቡና እንዲዘለፉ ሆነ።

ቢቢሲ፦ አሁን እንዴት ባለ ሁኔታ ነው እየተመላለሳችሁ እየጠየቃችኋቸው ያላችሁት?

ወ/ሮ አሲ፦ በሚካሄደው የፍርድ ሂደት ላይ መቅረት አልፈልግም። ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ቤተሰብ የላቸውም። ሁሉም ቤተሰብ አዲስ አበባ ነው የሚኖረው። በዚያ ላይ የእነሱን ውንጀላ እንጂ ሌላ ውሳኔ የማይጠብቅ የተደራጀ ቡድን አዳራሹን ሞልቶ ነው የሚውለው። የተከሰሱበትም 'ኬዝ' የፖለቲካ እንጂ እውነት እንደሌለው ስለምናውቅ በዚህ ሁኔታ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ስንል ሁሌም መገኘት አለብን። ፍርዱን እየተከታተልን ለሚድያም ማሳወቅ አለብን። በዚያ ላይ እነዚህ ሰዎች ጠበቃ የላቸውም። ጠበቃ የሚሆን ሰው ላይ እርምጃ እንወስዳለን የሚል መልዕክት 'ሶሻል ሚድያ' ላይ ስለተሠራጨ ጠበቃ ማግኘት አልቻልንም። ሁለት ጠበቆች መጥተው ነበር ሁኔታውን ለማጣራት፤ ነገር ግን ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው ጥለው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።

ቢቢሲ፦ በማረሚያ ቤት የእነ አቶ በረከት አያይዝስ እንዴት ነው?

ወ/ሮ አሲ፦ እሥር ቤቱ እውነት ለመናገር አዲስ ነው። ሌላ እሥር ቤት ባላውቅም ሰዎች እንደሚናገሩት የተሻለ ነው። ከባህርዳር ወጣ ያለ ነው። ለብቻቸው ገለል አድርገው ነው ያስቀመጧቸው። ለዚህ እናመሰግናለን። ይህ ማለት ግን ችግር የለም ማለት አይደለም። ቀደም ሲል ቤተሰብ ረዘም ያለ ጊዜ ተሰጥቶት ይጠይቅ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተሰልፈን ጠብቀን ነው የምንጠይቃቸው። በዚያ ላይ የተሰጠን አጭር ጊዜ ሳያልቅ በቃችሁ እንባላለን። ይብዛም ይነስም በስልክ እንገናኝ ነበር፤ አሁን ግን ያን ማድረግ አልቻልንም። አዲስ አበባ ላይ ጠበቆችን አማክረን ያሉንን መልዕክት በአግባቡ ማስተላለፍ አልቻልንም። በዚህ በኩል ቤተሰብ እየተንገላታ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መጻሕፍት ይገቡላቸዋል ግን የሚጽፉት በኮምፒውተር ሳይሆን በእስክሪቢቶ ነው።

ቢቢሲ፦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከአቶ በረከት ጋር ብዙ ጊዜ የምታወሩት ስለምንድነው?

ወ/ሮ አሲ፦ በርካታ ጉዳዮች እናነሳለን። ስለቤተሰን እናወራለን። ብዙ ጊዜያችንን የምናጠፋው ግን ስለ ፍርድ ሂደቱ በማውራት ነው። ጠበቃ ስለሌላቸው ከጠበቆች የተሰጠንን ምክር እናደርሳለን፤ ጥያቄም ካለን ይዘን እንመለሳለን። ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካም እናወራለን። እርግጥ ቴሌቪዥን ገብቶላቸዋል።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት ከመታሠራቸው በፊት ከሀገር መውጣት ይፈልጋሉ ወይ ተብለው እንደማይፈልጉ ገልፀው ነበር። አሁን ላይ የተለየ ሃሳብ ይኖራቸው ይሆን?

ወ/ሮ አሲ፦ እኔ እስከማውቀው ድረስ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ከኢትዮጵያ የመውጣት ፍላጎት የለኝም ነው የሚለው። ወደፊት ምን ይሆናል? አይታወቅም። ሰው ስለሆነ አስገዳጅ ነገሮች ይፈጠሩ ይሆናል። ብዙ ወዳጅ ዘመድ ይገፋፋው እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ከኢትዮጵያ ውጣ እያለ። ግን አንድም ቀን ከሀገር የመውጣት ፍላጎት እንዳለው ሲናገር ሰምቼው አላውቅም። ቤተሰቤ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚል ፍራቻ ነበረው እንጂ እሱ ለሞትም የተዘጋጀ ሰው ነው።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት ዛሬ ላይ የሚቆጫቸው ነገር ይኖር ይሆን? ባደርገው ወይም ባላደርገው ኖሮ የሚሉት?

ወ/ሮ አሲ፦ የሚቆጨው ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል። በዚህ ደረጃ የማውቀው ነገር የለም። በዚሁ ሁኔታ ነገሩ መደምደሙ ግን ያሳዛነዋል። እነዚህ ያሰሩትን ሰዎች ከማንም በላይ ያምናቸው ነበረ። ሥልጣንም አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። እኔ ይበቃኛል፤ እኛ መውጣት አለብን፤ እናንተ ተረከቡ ብሎ አስተላልፏል። ይቆጨዋል ብዬ የምገምተው ነገር፤ የእነርሱ ዓይነት 'ቫልዩ' ያለው ትክክለኛ ተተኪ አለመፈጠሩ ያሳዝነዋል ብዬ እገምታለሁ። እዚህ ላይ ጉድለት እንዳለ ሲናገር እሰማዋለሁ። ከመታሠሩ ጋር በተያያዘ የሚቆጨው የማውቀው ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት የተከሰሱበት ሂደት ፖለቲካዊ ተፅዕኖ አለው ብለው ያስባሉ?

ወ/ሮ አሲ፦ አዎ፤ በደንብ! ለምን? ብለህ ብትጠይቀኝ፤ አንደኛ በርካታ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና ይጠረጠራሉ። ነገር ግን ብዙ ጊዜ አይጠየቁም። ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረው የሠሩ ሰዎች ሳይያዙ እነሱ ብቻ ተነጥለው የተያዙበት ሁኔታ በግምገማ መታየት ነበረበት። ሁለተኛ ነገር ደግሞ በረከትም ሆነ አቶ ታደሰ በሙስና አይታወቁም። እንደውም ይጠየፋሉ ተብሎ ነው የሚነገርላቸው። እንዲሁም መጽሐፉ ላይ የሙስና እና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ሰዎች ስም እየጠቀሰ አጋልጧል። አቶ ታደሰም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ኑሯቸውን በዝቅተኛ ደረጃ፤ በድህነት የሚመሩ ሰዎች ናቸው። በሱም ስም ሆነ በዘመድ አዝማድ አንድም ንብረት የለውም። መሬት እንኳን የሌላቸው፤ ቤት የሌላቸው፤ መኪና ወይም ሌላ ንብረት ያላፈሩ፤ መንግሥት በሚሠጣቸው ገቢ የሚኖሩ ናቸው። ከድርጅቱም በቃኝ ብሎ የተገለለው ሙስና በመንሠራፋቱ ምክንያት ነው። ቤት ድረስ 'ያላንተ አይሆንልንም' እያሉ የሚመጡ እንደነበሩ አውቃለሁ። ዛሬ ደርሶ ሙሰኛ ነው ተብሎ ሲወቀስ ፖለቲካ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ቢቢሲ፦ ምንም እንኳ ክሳቸው እየታየ ያለው በአማራ ክልል ሥር ቢሆንም፤ የአቶ በረከት ክስ የፌዴራል መንግሥት እጅ አለበት ብለው ያስቡ ይሆን?

ወ/ሮ አሲ፦ እንግዲህ የፌዴራል መንግሥት 'በእኛ በኩል አንፈልጋቸውም' ሲል መግለጫ ሰጥቷል። እንዲህ አለም አላለም እነዚህ ሰዎች በግፍ ታሥረዋል። ሰብዓዊ መብታቸው እየተረገጠ ነው፤ በፍትህ እየተዳኙ አይደለም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህንን በተመለከተ ለፌዴራል መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ብንጽፍም ምላሽ የሚሠጥ አልተገኘም። የሚሰጠን መልስ በፍርድ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ላይ ጣልቃ አንገባም የሚል ነው። ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩም አናግረውናል። ከመታሠራቸው ጋርም አያይዞ ያለብንን እክል ነግረናቸዋል። ሊተባበሩን የማይፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ነግረናቸው ችግሩ እንዲፈታ ትዕዛዝ ሰጥተውልናል። በፍትህ ጉዳይ መግባት እንደማይችሉ ነገር ግን ፍትህ በአፋጣኝ ይሰጥ ዘንድ እንደሚያናግሯቸው ነግረውናል። ለዚህ እናመሰግናለን። ግን በጣም ዘግይቷል፤ አሁንም እየዘገየ ነው ያለው።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት ባህርዳር ሲገቡ በርካታ ሕዝብ ወጥቶ መያዛቸው ትክክል ነው ሲል ነበር፤ ቀደም ብሎም ደብረማርቆስ ላይ እሳቸው አሉበት የተባለ ሆቴል ጥቃት ደርሶበታል። አቶ በረከት ምንም ዓይነት ጥፋት ከሌለባቸው፤ እንዲህ ያለ መረር ያለ ተቃውሞ እንዴት ሊያጋጥማቸው ቻለ?

ወ/ሮ አሲ፦ በተለይም በረከት ከመታሠሩ በፊት ከፍተኛ ዘመቻ ተደርጎበታል። ፀረ-አማራ ነው፤ ለትግራይ የሚያደላ ነው የሚሉና መሰል ዘመቻዎች ሲደረጉበት ነበር። የዋሁ ሕዝብ እውነት ሊመስለው ይችላል። ለእነዚህ ዘመቻዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በረከት መልስ አይሰጥም ነበር። ትኩረትም አይሰጣቸውም። ማሕበራዊ ሚድያ ላይም አይሳተፍም። ቀላል የማይባል ስም ማጥፋት የተደረገበትም ወጣቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ ነበር። የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። እንደውም እንደተደረገበት ዘመቻ ቢሆን ኖር በሕይወት የሚቆይም አልነበረም።

ቢቢሲ፦ አቶ በረከት የተመሠረተባቸው ክስ ውድቅ ሆኖ በነፃ ይሰናበታሉ ብላችሁ ታስባላችሁ?

ወ/ሮ አሲ፦ አሁን ትልቁ ፈተና ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው ያሠሩበት ምክንያት ውሃ የማይቋጥር መሆኑ ነው። በጥላቻ እና በመንጋ ግፊት የተመራ መሆኑ ነው፤ የለውጥ ሆይሆይታ ያመጣው ግፊት ነው። ሁለቱም [አቶ በረከትና አቶ ታደሰ] አማራ አይደሉም ተብሎ ይታሰባል። ሁለቱም ለብሔረሰቦች መብት ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፤ የአማራ ብሔር ተወላጅ እንደመሆናቸው ግን ለአማራ ሕዝብ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው። አሁን ክሱ ውድቅ ሆኖ በነፃ ቢለቀቁ ከመጀመሪያውስ ለምን ታሠሩ? የሚል ነገር ሊመጣባቸው ይችላልና ይሄ ነው ትልቁ ፈተና። በእኔ ግምት የክልሉ መሪዎች ከፍትህ በላይ ይህ የሚያስጨንቃቸው ይመስለኛል።