የጡት ካንሰር የያዛት የጡት ካንሰር ሀኪም

ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮርዳን

የፎቶው ባለመብት, Alex Kilbee

የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮርዳን

ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮርዳን ትባላለች። የጡት ካንሰር የቀዶ ጥገና ሀኪም ነበረች። የጡት ካንሰር ይዟት ሥራዋን ለማቆም እስከተገደደችበት ጊዜ ድረስ በሙያዋ ብዙ ሴቶችን አገልግላለች።

ስለ ህመሟ ስትናገር፦

"እንደ አብዛኞቹ ሴቶች ጡቴን አልተመረመርኩም ነበር። የጡት ካንሰር ሀኪም ስለሆንኩ የጡት ካንሰር ይይዘኛል ብዬ አስቤ አላውቅም"

ህክምና ስትማር ቢያንስ ለ20 ዓመት የጡት ካንሰር ሀኪም እሆናለሁ ብላ ነበር። ነገር ግን በሙያዋ መሥራት የቻለችው ሁለት ዓመት ብቻ ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ጡቷ ላይ ቀዶ ጥገና ተደርጎ ነበር። ባለፈው ወር ካንሰር ዳግም አገርሽቶባታል።

ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮርዳን

የፎቶው ባለመብት, John Godwin

የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር ሊዝ ኦሪዮርዳን

"ከሀኪምነት ወደ ታማሚነት ልሸጋገር ነው?"

የጡት ካንሰር እንዳለባት ከማወቋ በፊት ጡቷ ላይ አንዳች ምልክት ታይቷት ነበር። ጡት በሚመረመርበት ኤክስሬይ 'ማሞግራም' ስትታይ ጡቷ ላይ ችግር እንደሌለ ተነገራት።

ቢሆንም ምልክቱን በድጋሚ ስታይ እናቷ ካንሰር እንድትመረመር አደረጓት። በምርመራውም ካንሰር እንዳለባትም ታወቀ።

የጡት ካንሰር ሀኪም በመሆኗ ምን እንደሚያስፈልጋት ለማወቅ አማካሪ አላስፈለጋትም። "ከሀኪምነት ወደ ታማሚነት ልሸጋገር ነው?" ብላ ትካዜ ቢገባትም፤ ኬሞቴራፒ እንደሚያስፈልጋት እንዲሁም ምን ያህል ጊዜ በሕይወት መቆየት እንደምትችል ታውቃለች።

ዶ/ር ሊዝ አሁን 43 ዓመቷ ነው። ብዙ ዶክተሮች ህክምና በሚሰጡበት በሽታ አንደማይያዙ ትናገራለች።

ዶክተሯ 'ሬድዮቴራፒ' (የጨረር ህክምና) ካደረገች በኋላ የክንዷ እንቅስቃሴ ተገደበ። ቀዶ ጥገና ማድረግም አልቻለችም።

ህመሙ አካል ላይ የሚያደረሰውን ጉዳት እንጂ ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖው እስከሚደርስባት ድረስ አታውቅም ነበር።

"የጡት ካንሰር ላለበትን ሰው መንገር እንጂ በበሽታው መያዝ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም ነበር።"

ሀኪሟ ከቀዶ ጥገና በኋላ ትከሻዋን እንደቀድሞው ማዘዝ አልቻለችም

የፎቶው ባለመብት, Liz O'Riordan

የምስሉ መግለጫ,

ሀኪሟ ከቀዶ ጥገና በኋላ ትከሻዋን እንደቀድሞው ማዘዝ አልቻለችም

"የራሴን ህመም ደጋግሞ ማስታወስ ነው የሆነብኝ"

ካንሰር እንደያዛት ካወቀች በኋላ የቀዶ ጥገና አማካሪ ከሆነ ባለቤቷ ጋር ተመካክራ የትዊተር ገጿ ላይ ስለመታመሟ ጻፈች።

ትዊተር ላይ 1,500 ተከታዮች ያሏት ሲሆን፤ እንደሷው የጡት ካንሰር ያለባቸው ሴቶች ማኀበራዊ ሚድያ ላይ ድጋፍ ይቸሯት ጀመረ።

እንደሷው ሀኪም ሆነው የጡት ካንሰር ከያዛቸው ሴቶች ጋር የተገናኘችውም በማኀበራዊ ሚዲያ ነበር። የዋትስአፕ ቡድን ፈጥረው ተሞክሯቸውን ይጋራሉ።

የጡት ካንሰር ከያዛት በኋላ ህመሙ ያለባቸውን ሰዎች በተሻለ ሁኔታ መርዳት እንደምትችል ገምታ ነበር። ሆኖም እንዳሰበችው ቀላል ሆኖ አላገኘችውም ።

"ለእያንዳንዷ ሴት የጡት ካንሰር እንዳለባት መንገር ከባድ ነው። የራሴን ህመም ደጋግሞ ማስታወስ ነው የሆነብኝ" ትላለች ዶ/ር ሊዝ።

ቀዶ ጥገና ከተደረገላት በኋላ ታካሚዎቿ ላይ ቀዶ ጥገና ማድረግ ተቸግራ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Liz O'Riordan

የምስሉ መግለጫ,

ቀዶ ጥገና ከተደረገላት በኋላ ታካሚዎቿ ላይ ቀዶ ጥገና ማድረግ ተቸግራ ነበር

"እኔና እሷ አንድ ነን"

ትሠራበት በነበረው ሆስፒታል አንድ በሷ ዕድሜ ያለችና እንደሷው አይነት የጡት ካንሰር ያለባት ሴት ህክምና ትከታተል ነበር።

ሰለታማሚዋ ከሌሎች ሀኪሞች ጋር እየተነጋገረች ሳለ "ያለችበት ሁኔታ እጅግ የከፋ ነው" ሲባል ልክ ስለሷ እንደሚወራ እንደተሰማት ትናገራለች፤ "እኔና እሷ አንድ ነን" ስትልም የተሰማትን ስብራት ትገልጻለች።

ዶ/ር ሊዝ ሰዎች ካንሰር ከያዛቸው በኋላ ወደሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ትመክራለች። በርካታ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ካንሰር ከያዛቸው በኋላ ወደሥራ የሚመለሱበትን መንገድ እንደማያመቻቹም ትናገራለች።

አሁን የጡት ካንሰር ላለባቸው ሴቶች እገዛ ማድረግ በምትችልባቸው ማህበሮች ውስጥ ትሳተፋለች፤ ታማክራለችም።

"አማካሪ ሆኜ በዓመት ቢያንስ ከ70 እስከ 100 ሴቶች እረዳለሁ። በመጽሐፌ ደግሞ መቶ ሺዎችን አግዛለሁ" ትላለች ዶክተሯ።