ታጣፊው የሳምሰንግ ስልክ የ'ስክሪን' መሰበር ወቀሳ ቀረበበት

ታጣፊው የሳምሰንግ ስልክ

የሳምሰንግ አዲሱን ታጣፊ ስልክ ቀድመው የሸመቱ ግለሰቦች 'ስክሪኑ' እየተሰበረብን ነው በማለታቸው ምክንያት፤ ኩባንያው የስልኩን ምርቃት ጊዜ አዘግይቶታል።

'ጋላክሲ ፎልድ' የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ይህ ምርት እክል ስላጋጣመው ይቅርታ የጠየቀው ኩባንያው «ትንሽ ጊዜ ስጡኝና ስልኩን ላበጃጀው» ሲል ተደምጧል።

1980 ዶላር (61 ሺህ ብር ገደማ) ዋጋ የተለጠፈበት 'ጋላክሲ ፎልድ' ምርቃት በቅርቡ መሆኑ አይቀርም ብሏል ኩባንያው።

ኩባንያው የችግሩ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ስልኩ እንዲታጠፍ የሚረዳው ማጠፊያ ነውና እሱን እናስተካክል ዘንድ ጥቂት ሳምንታት ስጡን ብሏል።

የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ ኩባንያ ሳምሰንግ አዲሱን ምርቱን ሎንዶን፣ ሆንግ ኮንግ እና ሻንጋይ በመሳሰሉ ከተሞች አስመርቃለሁና በጉጉት ጠብቁኝ ብሎ ነበር።

አንዳንድ ሸማቾች ስልኩ ላይ ያለው 'ስክሪን ከቨር' ስልኩን ከአደጋ እንዲከላከል የተቀመጠ መስሏቸው የስልኩን 'ስክሪን' መገንጠላቸው ደግሞ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

ሁዋዌ ኣነደ ዣዎሚ የተሰኙት የቻይና ስልክ አምራቾችም 'ታጣፊ ስልክ ካልሠራን ሞተን እንገኛለን' ማለታቸው ተሰምቷል።