ወባ ይከላከላል የተባለለት ክትባት ማላዊ ውስጥ ሙከራ ላይ ሊውል ነው

የፎቶው ባለመብት, D POLAND/PATH
በዓለም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለለት የወባ በሽታ ክትባት ማላዊ ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናት በሙከራ መልክ ሊሰጥ መሆኑ ተሰምቷል።
ክትባቱ የሰውነትን የመከላከል አቅም በማጎልበት የወባ ትንኝ የምታመጣውን የወባ ባክቴሪያ ያዳክማል ተብሏል።
ከዚህ በፊት በተደረገው ሙከራ መረዳት እንደተቻለው፤ ዕድሜያቸው ከ5-17 ወራት የሆኑ ሕፃናት ክትባቱን ወስደው ከበሽታው መጠበቅ ችለዋል።
ገዳዩን የወባ በሽታ ከምድረ-ገፅ ለማጥፋት የተደረገው ጥረት የተሳካ ቢመስልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሽታው ማንሰራራት አሳይቶ ነበር።
ዓለም ላይ በወባ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈ ግማሽ ሚሊየን ገደማ ሰዎች መካከል 90 በመቶው አፍሪቃ ውስጥ እንደሚገኙ፤ አብዛኞቹም ሕፃናት እንደሆኑ ጥናት ይጠቁማል።
ምንም እንኳ ማላዊ የወባ በሽታን ለመከላከል ሁሉንም ዓይነት መላ ብትጠቀምም ቀንደኛዋ የበሽታው ተጠቂ መሆኗ ግን አልቀረም። በግሪጎሪያን አቆጣጠር 2017 ላይ ብቻ 5 ሚሊዮን የማሊ ዜጎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል።
ማላዊን ጨምሮ ኬንያ እና ጋና አርቲኤስኤስ የተሰኘውን የወባ በሽታ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሞክሩ የተመረጡ ሃገራት ናቸው።
ሃገራቱ የተመረጡበት መሥፈርት ደግሞ ወባን ለማጥፋት በየቤቱ አጎበር እስከመዘርጋት ቢደርሱም በሽታው ሊቀንስ አለመቻሉ ነው።
ክትባቱ ለሦስት አሥርት ዓመታት ያህል አሉ በተባሉ ሳይንቲስቶች ሲብላላ የቆየ መሆኑም ተዘግቧል፤ እስካሁንም 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጭ እንደሆነበት ተነግሯል።
የክትባቱን ሂደት በበላይነት የሚቆጣጠረው የዓለም ጤና ድርጅት ነው። የክትባቱ የመከላከል አቅም 40 በመቶ ቢሆንም ከሌሎች መከላከያ መንገዶች ጋር በመሆን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ይላል ድርጅቱ።
ክትባቱ ለአንድ ሕፃን አራት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በየወሩ እንዲሁም የመጨረሻው ከ18 ወራት በኋላ ይወሰዳል።
እስከ 2023 ይቆያል የተባለለት ይህ የክትባት ሂደት ማላዊ ውስጥ ከተጀመረ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኬንያ እና ጋና ላይ የሚቀጥል ይሆናል።

• የቢጫ ወባ ካርድ በቦሌ ለሚወጡ ሁሉ ግዴታ ሊሆን ነው?
ሐሰተኛ ቢጫ ወባ ካርድን ለመከላከል የሚረዳ ዲጂታል ካርድ እየተዘጋጀ ነው።