የኤርትራ መንግሥት ለ13 ዓመታት የቁም እስር የፈረደባቸው ፓትርያርክ ማን ናቸው?

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሦስተኛ ጳጳስ የሆኑት አቡነ እንጦንዮስ

የፎቶው ባለመብት, TEWAHDO.ORG/SCREENSHOT

የምስሉ መግለጫ,

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሦስተኛ ጳጳስ የሆኑት አቡነ እንጦንዮስ

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሦስተኛ ፓትርያርክ የሆኑት አቡነ እንጦንዮስ፤ ከ13 ዓመታት በኋላ ድምጻቸው ተሰምቷል።

አቡነ እንጦንዮስ በኤርትራ መንግሥት ግፊት ከኃላፊነታቸው ተነስተው የቁም እስረኛ ከሆኑ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ፓትርያርኩ ስላሉበት ሁኔታ የተለያዩ ሀሳቦች ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም፤ ከ13 ዓመታት በኋላ ቤታቸው ውስጥ እንደተቀረጸ በተነገረ ተንቀሳቃሽ ምስል ድምጻቸው ተሰምቷል።

በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ ፓትርያርኩ መጀመሪያ ላይ ከመንግሥት ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት ሲያብራሩ፤ አቶ ዮፍታሔ ዲሞጥሮስ የተባሉ ከመንግሥት የተላኩ ሰው ቤተክርስትያኒቱን እመራለሁ ብለው እንደመጡ፤ እሳቸው ግን ቤተክርስቲያኗ ዲያቆን ወይም ቄስ ባልሆነ ሰው መመራት እንዳማትችል ገልጸው መቃወማችውን ያብራራሉ። ሆኖም አቶ ዮፍታሔ፤ ሃሳባቸውን እንዳልተቀበሉ በአጽንኦት ያስረዳሉ።

አቡነ እንጦንዮስ ይህንን ሃሳብ ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ባቀረቡበት ጊዜም የሲኖዶሱ አባላት ''መንግሥት ከወሰነ እኛ ምን ማድረግ እንችላለን?'' ብለው እንደመለሱላቸው ያስረዳሉ።

ኋላ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ በስድስት ወንጀሎች እንደከሰሳቸው የሚናገሩት አቡነ እንጦንዮስ፤ ''ሕግ በመጣስ እኔን ሳያናግሩ ራሳቸው ከሳሽና ፈራጅ በመሆን ከፓትርያርክነት አውርደው ተራ መነኩሴ እንድሆን አደረጉኝ'' ሲሉ ሁኔታውን ያብራራሉ።

የቁም እሥረኛ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች እና አንድ ካህን ወደታሠሩበት ቤት በመሄድ፤ መስቀል፣ መጻሕፍቶቻቸውን እና አልባሳታቸውን በመኪና ጭነው እንደወሰዱባቸው ይገልፃሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ንብረቶቹ በጊዜው 'ከሕግ ውጭ' የተሾሙት ፓትርያርክ እንደሚገለገሉበት የተነገራቸው ቢሆንም አሁን የት እንዳሉ አያውቁም።

ከሲኖዶሱ እንደታረቁና ስህተታቸውን እንዳመኑ የሚወራው ወሬ ልክ እንዳልሆነ አቡነ እንጦንዮስ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ያብራራሉ።

በመጨረሻም አቡነ እንጦንዮስ፤ ቤተክርስቲያኗ ያለ መሪ እንደቀረች በምሬት ገልፀው ሕገ ቤተክርስትያን እንዲመለስ ከታሠሩበት ቀን ጀምሮ እየጸለዩ እንደሆነ ይናገራሉ።

በሰሜን አሜሪካ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንና የማዕከላዊ ምስራቅ አውሮፓ ሃገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ጸኃፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ቄስ ገብረሚካኤል ዮሐንስ፤ ፓትርያርኩ ተናገሩት ተብሎ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ባለፈው መጋቢት የተቀረጸ እና ትክክለኛ እንደሆነ አረጋግጠውልናል።

«በተጨማሪም ባለፉት 13 ዓመታት ቤተክርስትያኗ ከጸጥታ ኃይሎች እና ፖሊስ ያጋጠማት የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ጫና የሚያረጋግጡ ብዙ ሰነዶች እጃቸን ላይ አለ» ይላሉ ቄስ ገብረሚካኤል።

ቤተክርስትያኗ ለሁለት ሺህ ዓመታት የቆየ ሕግ እንዳላት እና አቡነ እንጦንዮስ ጥፋት ፈጽመው ከሆነ በቤተክርስትያን ሕግ መዳኘት እንደነበረባቸው ገልፀው፤ ፓትርያርኩ ተወግዘዋል የሚባል ከሆነ ግን ቤተክርስትያኗ ለሁለት ልትከፈል እንደምትችል ያስጠነቅቃሉ።

ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምላሽ ለማግኘት ብንፈልግም በህማማት ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ ዝግ በመሆኑ አልተሳካም።

አቡነ እንጦንዮስ ሕምብርቲ የተባለች ከአስመራ ከተማ ወጣ ብላ ያለች ቦታ እንደተወለዱ መዛግብት ያስረዳሉ።

በፈረንጆቹ 2004 ላይ ነበር የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ በመሆን የተሾሙት። መንበሩን ከያዙ ከሁለት ዓመታት በኋላ የኤርትራ መንግሥት ቄሶች ማሠሩን በመቃወማቸው ለቁም እሥር እንደበቁ ይነገራል።

ሐምሌ 2017 ላይ በከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ታጅበው አስመራ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ንግግር እንዲያሰሙ ግን አልተፈቀደላቸውም።

አቡኑ አሁን ላይ ያሉበት አድራሻ በውል የማይታወቅ ሲሆን መንግሥት ሕክምና የማግኘት መብታቸውን ገፏል እየተባለም ይታማል።