መአዛን በስለት ወግቶ ለሞት የዳረጋት ግለሰብ አሁንም ከፖሊስ እንዳመለጠ ነው

የመአዛ ካሳ የቀድሞ ፎቶና ሆስፒታል ከገባች በኋላ የተነሳ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, WUDE KASSA

የምስሉ መግለጫ,

የመአዛ ካሳ የቀድሞ ፎቶና ሆስፒታል ከገባች በኋላ የተነሳ ፎቶ

(በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መአዛ ሆስፒታል ሳለች ጉዳቷን የሚያሳይ ፎቶ አካተናል። ፎቶው ሊረብሽ ስለሚችል አንባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን።)

ጥር 2 ቀን 2011 ዓ. ም. በሥራ ባልደረባዋ በስለት ተወግታ፤ ከሁለት ወራት በኋላ መጋቢት 5 ህይወቷ ያለፈው የመአዛ ካሳ ገብረመድሀን ጉዳይ የበርካቶች መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል።

በተለይም መአዛ ላይ ጥቃት በማድረስ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው ግለሰብ ማምለጡን ተከትሎ ብዙዎች የሕግ አስፈጻሚ አካል ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግነኙነት ሀላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ተጠርጣሪው ያመለጠው እንዲጠብቀው ተመድቦ በነበረው ፖሊስ ቸልተኝነት ከሆነ ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረው እንደነበረ ይታወሳል።

ተጠርጣሪው በአንድ ፖሊስ አጃቢነት ለህክምና ከእስር ቤት ወጥቶ ካመለጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ተጠርጣሪውን እንዲጠብቅ ተመድቦ የነበረው ፖሊስ ለምርመራ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም፤ በዋስ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ተሰውሯል።

ለመሆኑ የመአዛ ቤተሰብ አሁን ምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? የተጠርጣሪው መጥፋት እና አጅቦት የነበረው ፖሊስ መሰወር ያጫረው ጥያቄስ?

(በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መአዛ ሆስፒታል ሳለች ጉዳቷን የሚያሳይ ፎቶ አካተናል። ፎቶው ሊረበሽ ስለሚችል አንባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን።)

ሀምሌ 2010

በ30 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው መአዛ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ውስጥ በፋይናንስ ሀላፊነት የተቀጠረችው ሀምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደነበረ ታላቅ እህቷ ውዴ ካሳ ትናገራለች።

እህቷ እንደምትናገረው፤ መአዛ ከተቀጠረች በኋላ ለተወሰኑ ሳምንታት ስልጠና ላይ ነበረች። ታህሳስ 2011 ላይ የጤና እክል ገጥሟት የነበረ ቢሆንም መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ሥራ በዝቷል ተብላ ጥር ላይ ከእረፍት ተመልሳ ግማሽ ቀን እንድትሠራ ተደረገ።

የውዴ ቤት ለመአዛ መሥሪያ ቤት ቅርብ ስለሆነ አልፎ አልፎ ምሳ አብረው ይበላሉ።

መአዛ ላይ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠረው የሥራ ባልደረባዋ ምሳ ሲበሉም ሆነ ሻይ ሲጠጡ አልፎ አልፎ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ውዴ ታስታውሳለች።

"አብረው ብዙ ጊዜ ባይሰሩም ስለሷ ያጠና ነበር። በአይነ ቁራኛ ይከታተላት ነበር። በአንድ ወቅት አሟት ስትተኛ ቤቷን አጠያይቆ ጠይቋት ነበር።'' የምትለው ውዴ፤ በመአዛና በግለሰቡ መካከል ከሥራ ባልረደባነት ያለፈ ግንኙነት እንደሌለ ገልጻ "በሱ ልብ ያለውን ግን አላውቅም" ትላለች።

ጥር 2011

መአዛ ጥቃቱ የደረሰባት ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።

መአዛ በሕይወት ሳለች ለፖሊስ የሰጠችውን ቃል አጣቅሳ ውዴ እንደምትለው፤ ግለሰቡ "ጥር 2 ሁሉም ነገር ያበቃል" ሲል ይዝት ነበር።

ውዴ እንደምትለው፤ በበዓል ማግስት የመሥሪያ ቤት ባልደረቦቿ ጋር የአውደ አመት ዳቦ እየበሉ የታሸገ ውሃ ይጠጡ ነበር። ከረፋዱ አምስት ሰአት አካባቢ የመአዛ ጓደኞች ከቢሮ ወጥተው እሷም እስከምትከተላቸው ይጠብቋት ነበር።

መአዛ መሥሪያ ቤቷ ውስጥ ወንበሯ ላይ ተቀምጣ ሳለች የሆነውን ውዴ ትናገራለች።

"ስሟን ጠርቶ ዞር ስትል ቀኝ ጡቷ ስር በቢላ ወጋት። ጨጓራዋ ተቀደደ። ቢላውን አማስሎ ሲያወጣው አንጀቷ ተበጣጠሰ። እንደምንም አምልጣ ወደ ኮሪደር ስትሄድ ተከትሎ በተደጋጋሚ ይወጋት ነበር። ሰዎች እየተጯጯሁ ለማስቆም ይሞክሩ ነበር። ኋላ ላይ አስጥለዋት ወደ አለርት ሆስፒታል ወሰዷት።"

የመአዛ ደም ኦ-ኔገቲቭ (o-) ስለሆነ ደም ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ምሽት 1 ሰአት ድረስ ቀዶ ጥገና ማድረግም አልተቻለም ነበር።

ሀኪሞች ለመአዛ ቤተሰቦች እንደነገሯቸው ጨጓራዋ ውስጥ የነበረው አሲድ ወደ ሰውነቷ ፈሶ ነበር። ከሳምንት በኋላ ወተት ስትጠጣ ስለወጣ ጥር 8 ሁለተኛ ቀዶ ጥገና ተደረገላት።

"አንጀቷ ስለተጎዳ የመትረፍ እድል የላትም ቢባልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየች ነበር። ለሁለት ወር ከ15 ቀን ሆስፒታል ተኝታለች።"

የፎቶው ባለመብት, WUDE KASSA

የምስሉ መግለጫ,

መአዛ ከጥቃቱ በኋላ ሆስፒታል ሳለች የተነሳ ፎቶ

ተጠርጣሪው ጥቃቱን ባደረሰበት ዕለት ማለትም ጥር 2 ጎተራ ወረዳ 7 ፖሊስ መምሪያ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደረገ። በወቅቱ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ፖሊስ ምርመራውን አለመጨረሱን እንደተናገረ ውዴ ትገልጻለች።

የካቲት 2011

ውዴና የተቀረው ቤተሰብ የመአዛን ሕይወት ለመታደግ በሚያደርጉት ሩጫ ተይዘው የነበረ ቢሆንም የካቲት 4 ፍርድ ቤት ሄደው ስለጉዳዩ ጠይቀዋል።

"ስንሄድ ችሎት አልተሰየመም ተብለን ነበር። የሚከሰሰው ነፍስ በማጥፋት ሙከራ ወይስ በአካል ማጉደል ወንጀል የሚለው አልተለየም ነበር።"

በዚህ ወቅት ግለሰቡ ህክምና እንደሚፈልግ ለፍርድ ቤት አሳውቆ ፍርድ ቤት ፈቀደለት።

ከአንድ ጠባቂ ፖሊስ ጋር ወደ ሆስፒታል ሄዶ ሳለ እንደጠፋ የተገለጸውም በዚህ ጊዜ ነበር። ሆኖም ማምለጡ ለመአዛ ቤተሰቦች አለመነገሩን ውዴ ትናገራለች።

መአዛ ሆስፒታል ሳለች የግለሰቡ ቤተሰቦች መአዛ የምትገኘበት ሆስፒታል ድረስ በመሄድ ለማግባባት ጥረት ያደርጉ እንደነበር ውዴ ትናገራለች። የተጠርጣሪው ቤተሰቦችም ውዴን ከተጠርጣሪው ጋር በስልክ በማገናኘት "አሁን ተሽሏታል ብለሽ መስክሪልኝ፤ እሷን እኛ እናሳክምልሻለን" ማለቱን ውዴ ትናገራለች ታክላለች።

ጥቃቱ ሳያንስ ለማግባባት በተደገረው ጥረት እጅግ የተበሳጨችው ውዴ ቤተሰቦቹ ወደ ሆስፒታል መምጣታቸው ስጋት ውስጥ ከትቷት እንደነበርም ትገልጻለች።

መጋቢት 2011

መአዛ የጤናዋ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ፣ ሰዎች ለመጠየቅ ሲደውሉላትም "ቤት መጥታችሁ ታዩኛላችሁ" ትል እንደነበረ እህቷ ትናገራለች።

ውዴ እንደምትለው፤ መአዛ ከተኛችበት ክፍል በዊልቸር ይዘዋት ይወጡ ነበር። ሀኪሞችም ለውጥ ማሳየቷን አረጋግጠውላቸው ነበር። ሆኖም ከመሞቷ ከጥቂት ቀናት በፊት መሸበር፣ መጮህ ጀመረች።

"እማዬ እያለች ትጮሀ ነበር። ጥቃቱን ያደረሰባት ሰው እንደታሰረ ብታውቅም 'ይታሰር' ትል ነበር። ትፈራ ነበር። ትጨነቅ ነበር። ብቻዋን መሆን አትፈልግም ነበር።" በማለት ውዴ የእህቷ ህይወት ከማለፉ በፊት የነበራተን ሁኔታ ታስረዳለች።

ሀኪሞች ከጥቃት በኋላ (ፖስት ትራውማ) የሚፈጠር መረበሽ ነው እንዳሉ ውዴ ታስረዳለች። ሆኖም ከፍተኛ ማገገም አሳይታ የነበረችው እህቷ የተፈጠረባት ጭንቀትና ያገኘችው የህክምና ማብራሪያ አብሮ የሚሄድ ሆኖ አላገኘችውም።

መአዛ ያረፈችው መጋቢት 15 ቀን ጠዋት ላይ ነበር። መጋቢት 16 ከተቀበረች በኋላ ግለሰቡ ከፖሊስ ቁጥጥር ማምለጡን ቤተሰቡ መስማቱን ውዴ ትናገራለች።

"ለሽፋን 'አፍቅሬያታለሁ' ማለቱን ሰምተናል። ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። እጁ ላይ ካቴና ያለ ሰው ያመልጣል ብለን አልጠረጠርንም። አሁን ለራሳችንም ሕይወት ሰግተናል። ማንን ማመን እንዳለብን፣ የት መሄድ እንዳለብን አናውቅም። አሮጊት እና ህጻናት ይዘን ግራ ተጋብተናል። ምስቅልቅላችን ወጥቷል።"

ለፓሊስ ስልክ እየደወሉ "ተይዟል ወይ?" ብሎ ከመጠየቅ ባለፈ ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ውዴ በሀዘን ተውጣ ትገልጻለች።

ከሚያዝያ 2011 ወዲህ

መአዛ የሁለት ልጆች እናት ነበረች። ሁለት ልጆችም ታሳድግ ነበር።

የመጀመሪያ ልጇ 7 ዓመቷ ሲሆን ሁለተኛ ልጇ ደግሞ ሦስት ዓመት ሞልቶታል።

"ልጇ ጠዋት የእናቷ ፎቶ ስር ሻማ አብርታ 'ለእናቴን እየጸለይኩ ነው' ትላለች። ጥቁር ለብሳ 'የእናቴን ሀዘን ልወጣ ትላለች'። መአዛ የተቀበረችበት ቤተክርስቲያን እየሄደች ብዙ ጊዜ የሰፈር ሰዎች መልሰዋታል። ትንሹ ልጇ ሆስፒታል ያለች ስለሚመስለው 'መአዛ ጋር አንሂድ' ይላል።"

ውዴ ይህን የምትናገረው እንባ እየተናነቃት ነው። መአዛ እናታቸውን ጧሪ፣ ቤተሰቡን ሰብሳቢ እንደነበረችም ትናገራለች።

መአዛ የፊታችን ክረምት ላይ ከሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ትመረቅ ነበር።

ፍትህ ወዴት አለሽ?

መአዛ ህክምና ላይ ሳለችና ከሞተች በኋላም ቤተሰቡን በማገዝና ጉዳዩ ትኩረት እንዲቸረው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመጻፍ ሲተባበሩ ከነበሩ በጎ ፍቃደኞች አንዷ ኤደን ጸጋዬ ናት።

የተጠርጣሪው ማምለጥ እንዳለ ሆኖ የፖሊሱ መሰወር እና የመአዛ ቤተሰብ ጉዳዩን እንዳያውቅ መደረጉ ተደማምሮ "በሴቶች ላይ ጥቃት ሲደርስ ህግ አስፈጻሚ አካልን ማመን ይቻላልን?" የሚል ጥያቄ እንድታነሳ አድርጓታል።

ጥቃት አድርሶ የተያዘ ሰው የሚያዝበት መንገድ ብቻ ሳይሆን አንዲት ሴጥ ጥቃት ደርሶባት ወይም ስጋት አድሮባት ለፖሊስ ለመጠቆም ወደ ሕግ ቦታ ስትሄድ ያለው አቀባበል ሴቶች በስርዓቱ ያላቸው እምነት አንዲሸረሸር ያደርጋል ትላለች።

"ምርመራ ሲደረግ የተጠቃችን ሴት መልሶ ማጥቃት የሚመስል ንግግር ይደረጋል። ከዛም ባላይ በነፍስ ግድያ የተጠረጠረ ግለሰብ ማምለጡ እንደ ቀላል ነገር ሲታይ እምነት ያሳጣል። አጥቂዎች የሚገባቸውን እያገኙ አይደለም" ትላለች ኤደን።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሰር ለማዋል አስፈላጊውን መረጃ ያሰባሰቡ ሲሆን፤ የደረሱበትን ደረጃ በቅርብ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፖሊስ ከሴቶች ጥቃት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ስለሚይዝበት መንገድ ስለሚነሳው ቅሬታ ኮማንደሩ ሲመልሱ፤

"አንድ ፖለስ ማምለጡ ሁሉም ፖሊስ ላይ እምነት ሊያሳጣ አይገባም። በተፈጸመው ነገር ሁላችንም አዝነናል። ከአንድ ጠንቃቃ ፖሊስ የሚጠበቅ አይደለም። በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ጥብቅ እርምጃ እንወስዳለን።"