የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪምና የሩስያው ፑቲን ተገናኙ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪምና የሩስያው ፑቲን ተገናኙ

የፎቶው ባለመብት, ALEXANDER ZEMLIANICHENKO

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሩስያ ምስራቃዊት ከተማ ቭላዲቮስቶክ አቅራቢያ በሚገኝ ረስኪ የተባለ ቦታ ነበር የተገናኙት።

ኪም እና ፑቲን የኮርያ ሰርጥን ከኒውክሌር ነጻ ስለማድርግ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት ውይይት መክሸፉን ተከትሎ፤ ኪም ከሩስያው ፕሬዘዳንት ድጋፍ ሊጠይቁ ይችላሉ።

ኪም ትላንት ሩስያ ሲገቡ የሀገሪቱ ባለስላጣኖች ሞቅ ያለ አቀባባል አድርገውላቸዋል።

በወታደራዊ ባንድ ሙዚቃ ዘና እንዲሉ ከተደረገ በኋላ ዘወትር ከመኪናቸው ጎን ለጎን በሚሮጡ ጠባቂዎቻቸው ታጅበው ተወስደዋል።

"ጉብኝቴ ውጤታማ እና ጠቃሚም ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ኪም ለሩስያ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የሰሜን ኮርያና የሩስያን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ስለ ኮርያ ሰርጥ ጉዳይ ለመወያየት እቅድ እንደያዙም ኪም ተናግረዋል።

የሩስያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የኮርያ ሰርጥ የኒውክሌር ጉዳይን በተመለከተ አሁን ላይ ውጤታማ ሊሆን የሚችል ዓለም አቀፍ ጥረት እምብዛም አለመኖሩን ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ተጀምሮ የቆመው የሰሜን ኮርያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩስያና አሜሪካ ውይይትን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።

ሰሜን ኮርያና ሩስያ ምን ይፈልጋሉ?

ተንታኞች እንደሚሉት፤ የኪም እና ዶናልድ ትራምፕ ውይይት ፍሬ ስላላፈራ ሰሜን ኮርያ እንደ ሩስያ ያሉ ወዳጆች ከጎኗ ማሰለፍ ግድ ይላታል።

ሰሜን ኮርያ በምጣኔ ሀብት ረገድም ብቸኛ አጋሯ አሜሪካ አንዳልሆነች ማሳየት ትፈልጋለች።

ሩስያ በበኩሏ በኮርያ ሰርጥ ጉዳይ ቀንደኛ ተዋናይ መሆን ትፈልጋለች። ፑቲን ከኪም ጋር ለመገናኘት በጉጉት ሲጠብቁ ነበርም ተብሏል።

እንደ አሜሪካና ቻይና ሁሉ ሩስያም የሰሜን ኮርያ ኒውክሌር ክምችት እንቅልፍ ይነሳታል።