አሜሪካ፡ ታዳጊዋን ለ16 ዓመታት ያሰቃዩ ጥንዶች እስር ተፈረደባቸው

መሐመድ ቱሬ እና ባለቤቱ ዴኒስ ቱሬ
የምስሉ መግለጫ,

መሐመድ ቱሬ እና ባለቤቱ ዴኒስ ቱሬ

ለ16 ዓመታት የአንዲት ታዳጊን ጉልበት ይበዘብዙ የነበሩ ጥንዶች የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

መሐመድ ቱሬ እና ባለቤቱ ዴኒስ ቱሬ የተባሉት ጋያናውያን ጥንዶች ታዳጊዋን ከጋያና ወደ አሜሪካ የወሰዷት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2000 ነበር።

ቴክሳስ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጥንዶች ታዳጊዋን ለ16 ዓመታት ያለምንም ክፍያ አሠርተዋታል።

ወደአሜሪካ ስትወሰድ የአምስት ዓመት ልጅ የነበረችው ሴት፤ ቤት እንድታጸዳ፣ ምግብ እንድታበስልና ልጆች እንድትንከባከብ ትገደድ ነበር።

ጥንዶቹ ታዳጊዋን ይደበድቧት ነበር። ጸጉሯን ላጭተዋት፣ ቅጣት ብለው በቤታቸው አቅራቢያ በሚኝ ፓርክ ውስጥ ብቻዋን ያሳድሯትም ነበር። እንዳትማር ከመከልከላቸው ባለፈ ፖስፖርቷን ነጥቀዋትም ነበር።

2016 ላይ የጥንዶቹ የቀድሞ ጎረቤቶች ታዳጊዋ እንድታመልጥ ረድተዋታል። አቃቤ ሕግ የነበረችበትን ሁኔታ የገለጸው "ልጅነቷን ቀምተዋታል። ለዓመታት ጉልበቷን በዝብዘዋል። እሷ እየተሰቃየች እነሱ ሕይወታቸውን ያለችግር ገፍተዋል" በማለት ነበር።

ባልየው የጋያና የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት አህመድ ሶኩ ቱሬ ልጅ ሲሆን፤ ጥንዶቹ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ሊቀሙ ይችላሉ ተብሏል።

ፍርድ ቤት ጥንዶቹ 288,620 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ ወስኗል።

ባልና ሚስቱ፤ ስለኛ የተወራው ነገር "እጅግ ተጋኗል" በማለት አቤቱታ የማሰማት እቅድ አላቸው ተብሏል።