እስልምናን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ፊት ፎቶ የተነሳችው ሙስሊም ሴት መነጋገሪያ ሆናለች

ሻይማ ኢስማኤል Image copyright Shaymaa Ismaa’eel
አጭር የምስል መግለጫ ሻይማ ኢስማኤል

የ24 ዓመቷ ሻይማ ኢስማኤል የምትኖረው አሜሪካ ነው።

የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮችን የሚያጥላሉ ሰልኞች ፊት ለፊት የተነሳችው ፎቶ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ አድርጓታል።

ሰልፈኞቹ ሙስሊሞችን የሚያንቋሽሹ ጽሁፎች አንግበው ነበር። ሻይማ ደግሞ በተቃራኒው ፈገግ ብላ በእጇ የድል ምልክት (V) እያሳየች ፎቶ ተነሳች።

የቻይና ሙስሊሞች ምድራዊ 'ጀሐነም' ሲጋለጥ

ፎቶው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከ200,000 በላይ ወዳጅ ወይም 'ላይክ' ያገኘ ሲሆን፤ ሻይማ "ፎቶውን የተነሳሁት ጥላቻቸውን በፍቅርና በፈገግታ ማሸነፍ ስለምፈልግ ነው" ብላለች።

ሻይማ የምትሠራው የአእምሮ ዝግመት ካለባቸው ህጻናት ጋር ነው። ዋሽንግተን ውስጥ የተካሄደ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ኮንፈረንስ እየተሳተፈች ነበር።

ለሦስት ቀናት የተሰናዳው መድረክ የሀይማኖቱ ተከታዮች እንዲገናኙ፣ እንዲወያዩ የተሰናዳ ዓመታዊ መርሀ ግብር እንደነበረ ትናገራለች።

"ኮንፈረንሱ ውስጥ ደስ የሚል ድባብ ነበር። ስንወጣ ግን እኛን የሚቃወሙ ሰልፈኞች አየን። በመጀመሪያው ቀን ሳንጠጋቸወ አለፍን።"

ሀይማኖቱን የሚያጥላላ ንግግር በድምጽ ማጉያ እያሰሙ ነበር። 'እስልምና የጥላቻ ሀይማኖት ነው'፤ 'የስብሰባው ተሳታፊዎች ጥላቻ እየተሰበኩ ነው' የሚል ጽሁፍ ይዘውም ነበር።

"መንግሥት የሚደግፈው የሙስሊሙን ሕብረተሠብ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ፀረ ሙስሊም ደብዳቤ በእንግሊዝ

ሻይማ በተቃራኒው "እኔም ድምጽ ማጉያ ኖሮኝ ኮንፈረንሱ ውስጥ የምናወራውን ባሰማቸው ብዬ አሰብኩ" ትላለች።

ሰልፈኞቹን ለሦስት ቀናት ካየች በኋላ በስተመጨረሻ እሷም አቋሟን ለመግለጽ ወሰነች።

"ነቢያችን ፈገግታ ቸርነት ነው ይላሉ። እኔም ሳቂታ ነኝ። ሰልፈኞቹ ፈገግ ብዬ እንዲያዩኝ ስለፈለግኩ ጓደኞቼ ስስቅ ፎቶ እንዲያነሱኝ ጠየቅኳቸው።"

ሻይማ እንደምትለው ፎቶው ላይ ያሉት ሰልፈኞች በድርጊቷ መበሳጨታቸውን አይታለች። በተቃራኒው ፎቶውን ያዩት ሌሎት ሰዎች ከጠበቀችው በላይ ድጋፍ ሰጥተዋታል።