የሱዳን መከላከያ አዛዥ የሸሪዓ ሕጉ የሀገሪቱ ሕግ ምንጭ መሆን አለበት አሉ

ሌተናንት ጄነራል ሸምሰዲን ካባሺ Image copyright AFP

ሱዳንን እያስተዳደረ የሚገኘው ወታደራዊ ምክር ቤት የሸሪዓ ሕግ ለሀገሪቱ አዳዲስ ሕጎች መነሻ እንዲሆን እንደሚፈልግ አስታወቀ።

የተቃውሞ ሰልፉን ይመሩ የነበሩ ቡድኖች የፕሬዝዳንት ኦማር አልበሺር ከስልጣን መውረድን ተከትሎ የሚፈልጓቸውን ዝርዝር ምክረ ሀሳቦች ለሽግግር መንግሥቱ አቅርበዋል።

ነገር ግን 10 አባላት ያሉት ወታደራዊ ምክር ቤት ስለምክረ ሀሳቡ "በርካታ የማንስማማባቸው ነጥቦች አሉ" በማለት ከነዚህም መካከል ተቃዋሚዎች የእስልምና ሀይማኖትን መሰረት ስላደረጉ ሕጎች ዝምታን መርጠዋል ብለዋል።

አልበሽር በማህበራዊ ሚዲያ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ ተቹ

በወታደሩና በተቃዋሚዎች መካከል እየተደገረ ያለው ንግግር በውጥረት የተሞላ ነው።

የተቃዋሚዎቹን ምክረ ሀሳብ ለወታደራዊ ምክር ቤቱ ያቀረቡት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመብት ተሟጋቾች በጋራ በመሆን ነው።

የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ሌተናንት ጄነራል ሸምሰዲን ካባሺ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ተቃዋሚዎቹ ባቀረቧቸው በርካታ ሀሳቦች ላይ ተስማምተዋል።

ለዘመናት በስልጣን ላይ ያሉት ስድስቱ መሪዎች

"ነገር ግን ምክረ ሀሳቡ የሀገሪቱ ሕግ ምንጮች ምን መሆን እንዳለባቸው አልጠቀሰም። የሸሪዓ ሕጉ እና ባህል የሀገሪቱ የሕግ ምንጭ መሆን አለባቸው" ብለዋል።

አክለውም "የኛ ፍላጎት ሸሪዓ፣ የሀገሪቱ ባህልና እምነት የሀገሪቱ ሕግ ምንጭ እንዲሆኑ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የሱዳን ሕገ መንግስት የሸሪዓ ሕግ ሀገሪቱ የምትመራበት መርህ መሆኑን ያስቀምጣል።

በአልበሺር የስልጣን ዘመን አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ሴቶችን ለማጥቃት ብቻ ይሠራበት ነበር።

ሌተናንት ጄነራል ካባሽ አክለውም በምክረ ሀሳቡ ላይ ሌሎች ነጥቦች ላይም መነጋገር እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

ተቃዋሚዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የካቢኔው ስልጣን እንዲሆን ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ወታደራዊ ምክር ቤቱ ግን ይህ የሚሰየመው የበላይ ጠባቂ ሃላፊነት እንዲሆን ይፈልጋል።

የሱዳን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ወታደሩ ያስቀመጠውን ሰዓት እላፊ ጣሱ

በምክረ ሀሳቡ ላይ የሽግግር ጊዜው ለአራት ዓመት እንዲሆን ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ወታደራዊ ምክር ቤቱ ግን ሁለት ዓመት በቂ ነው ሲል ይሞግታል።

አንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ የተካረረውን ፍጥጫ ለማርገብ በስድስት ወር ውስጥ ቅድመ ምርጫ የማካሄድ ሃሳብ አለ።

አንድ የተቃውሞ ቡድን ቃል አቀባይ የሆኑት አምጃድ ፋሪድ "የተሰጠንን መልስ እንየውና አቋማችንን እናሳውቃለን" ብለዋል።

ጠ/ሚ ዐብይ አልበሽርን የድንበር ግጭቱን አብረን እንፍታ አሉ

ከዚህ ቀደም አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሲቪሎች የሚበዙበት የሽግግር መንግሥትን አይቀበሉም። ይህም በርካታ ትችትና ነቀፌታን አምጥቶባቸዋል።

በሱዳን ካርቱም የሲቪል አስተዳደር ካልተመሰረተ አንንቀሳቀስም ያሉ ተቃዋሚዎች አሁንም በወታደሩ ዋና ፅህፈት ቤት ደጅ ይገኛሉ።

ተያያዥ ርዕሶች