ወመዘክር፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን እስከዛሬ

ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ
አጭር የምስል መግለጫ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ

ወመዘክርን ንጉሡ ሲመሰርቱት

". . . በዚህ የሕዝብ መጻሕፍት ቤት የሚታተሙ መጻሕፍት፣ ያልታተሙ ጽሑፎችና ለታሪክ የሚጠቅሙ ነገሮች ሁሉ ተሰብስበው የሕዝባችን የአእምሮ ቅርስና የተስፋው ማነቃቂያ እንዲሆኑ ይጠበቃሉ፡፡ ዓላማችን በኢትዮጵያ የሚታተሙትን መሰብሰብ ብቻ አይደለም፡፡ በማናቸውም አገር የታተሙ ቢሆኑ የአገራችንን ጉዳይ የሚነኩትን መጻሕፍትና ጽሑፎች ሁሉ በተቻለ መጠን ለመሰብሰብ የምንደክምበት ነው. . .

. . . ማንበብ ወይም ምልክት ማድረግ ብቻ የበቃ አይደለም። የቅን ትምህርት ዋናው ምልክቱ የተነበበውን ከአእምሮ ጋራ ማዋሃድ ነው፡፡ ላይ ላዩን ከማንበብ የሚገኝ ዕውቀትና ከአንድ መጽሐፍ ውስጥ አንዳንድ ገጽ በመመልከት ብቻ ተገኝቶ የሚጠቀስ ቃል ሁሉ ለእውነተኛው የዕውቀት መሻሻል እጅግ የሚያሰጋና መሰናክል ይሆናል. . . "

ሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ. ም. ላይ የአሁኑ የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ያኔ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በሚል መጠርያ ሲመሰረት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ካደረጉት ንግግር የተቀነጨበ ነው።

"ሌቱም አይነጋልኝ" የተባለላት የውቤ በረሃ ትዝታዎች

ንጉሡ የግል ንብረታቸው የነበሩ መጻሕፍትን ለወመዘክር አበርክተው እንዳቋቋሙት የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ከመዛግብት ክፍሎች አንዱ

በቅድሚያ 138 ከዛም በተለያየ ጊዜ 600 መጻሕፍት ለግሰዋል።

ወመዘክር መዛግብት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ቅርሶች እንዲያሰባስብ ጭምር ታቅዶ ስለነበር የተለያዩ ነገሥታት አልባሳት፣ ከእንጨትና ከወርቅ የተሰሩ መገልገያዎችም ተሰባስበው ነበር።

እነዚህ ቅርሶች ዛሬ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ውስጥ ይገኛሉ።

ተቋሙ 1958 ዓ.ም. ላይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ሥራውን ማከናወን የቀጠለ ሲሆን፤ ከዛ በኋላም በተደጋጋሚ የመዋቅር ለውጦች ተደርጎበታል።

በ1968 ዓ. ም. የቀድሞው የባህልና ስፓርት ሚንስቴር ሥር እንደነበር ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ወመዘክር ኤጀንሲ የሆነው በ1998 ዓ. ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን አዋጅ ተከትሎ ነው።

የሠላም ተጓዧ ሉሲ (ድንቅነሽ) ምን ደረሰች?

በዚህ ዓመት 75ኛ የአልማዝ ኢዮቤልዮውን የሚያከብረው ወመዘክር፤ ባለፉት ሰባት አሰርታት ከጽሑፍ፣ ከድምፅና ከምስል ህትመቶች ሦስት ቅጂ ሰብስቧል።

የመጽሐፍ፣ የመጽሔት፣ የጋዜጣ፣ የሙዚቃ፣ የሀይማኖታዊ ዝማሬ፣ የቴአትር፣ የድራማ ቅጂዎች በማዕከሉ ይገኛሉ። የቃል ትውፊቶች በድምፅ ተቀርጸው እንዲሁም በጽሑፍ ሰፍረውም ይገኛሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸው የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ዝርዝር

ከሸክላ ሙዚቃ እስከ ሲዲ፤ ከብራና እስከ ጥራዝ መጻሕፍት ማግኘት ይቻላል። ለተመራማሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ክፍልና 24 ሰዓት የሚሠራ ቤተ መጻሕፍት የተቋሙ አካል ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ደራስያን ለመጽሐፋቸው የባለቤትነት እውቅና የሚያገኙበትና በዓለም አቀፍ የድረ ገጽ ገበያ ሥራቸውን ለመሸጥ የሚያስችላቸው የመጻሕፍትና የመጽሔት መለያ ቁጥር (ISBN) የሚሰጠውም ኤጀንሲው ነው።

ወመዘክር እንደ ተክለፃዲቅ መኩሪያና ከበደ ሚካኤል ያሉ አንጋፎች የመሩት ተቋም ነው።

የመይሳው ካሳ የልጅ ልጆች

ከኢትዯጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት ሊመለሱ ነው

እንደ ሀገር ግዛት ሚንስትር፣ አዲስ ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ፣ ፌደራል ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ካሉ ቀደምት ተቋሞች የተዛወሩ ስብስቦች ይገኙበታል።

ከታዋቂ ግለሰቦች ወደተቋሙ ከተዛወሩ የመዛግብት ስብስቦች መካከል፤ ዶክተር አምባሳደር ዘውዴ ገበብረሥላሴ ያሰባሰቧቸው 285 ፋይሎችና አለቃ ታዬ ገብረማርያም ያሰባሰቡት 48 አቃፊ መዛግብት ይጠቀሳሉ።

የወመዘክር ቤተ መጻሕፍት ለህጻናትና ለአይነ ስውራን ክፍል አለው። የኢትዮጵያ ጥናት ክፍል (17000 መጻሕፍት ያሉት)፣ የየእለቱ የጋዜጣና መጽሔት እትም ማንበብያ ክፍል እንዲሁም የማይክሮ ፊልም ክፍልም አለው።

የመጻሕፍት ውይይት፣ የመጻሕፍት ሽያጭ ያካሂዳሉ። ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ አታሚዎችና መጻሕፍት ሻጮች የሚሳተፉበት የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይም ይከናወናል።

የፈረሰው የደጃዝማች ዐምዴ አበራ ቤት ጠባቂ ምን ይላል?

የዘመናት ጉዞ

አፍሪካ ውስጥ ብሔራዊ መጻሕፍት በማቋቋም ግንባር ቀደሟ ግብጽ እንደሆነች ይነገራል። ኢትዮጵያም ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት በመመስረት ስመ ጥር ከሆኑ ሀገሮች አንዷ ነች።

ወመዘክር 75ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ ባወጣው መጽሔት ላይ እንደተመለከተው፤ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴ 1903 ዓ. ም. ላይ ለንደንን ጎብኝተው ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ፤ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ቤተ መዛግብት እንዲኖራት አሳስበው ነበር። ህልማቸው እውን የሆነው በ1936 ዓ. ም. ነበር።

አጭር የምስል መግለጫ በወመዘክር ጥንታዊ መዛግብት ይገኛሉ

ወመዘክር በመዋቅር ታቅፎ ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በ1968 ዓ. ም. ላይ የተላለፈ ውሳኔ ጉልህ ሚና መጫወቱን የታሪክ መጽሔቱ ያትታል።

በወቅቱ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ጥንታዊ መዝገቦቻቸውን ለወረቀት ፋብሪካ መሸጥ፤ ፍርድ ቤቶች ደግሞ ቦታ አጣበዋል ያሏቸውን አሮጌ መዛግብት ማቃጠል እንዲፈቀድላቸው ይጠይቃሉ።

"የወታደራዊ መንግሥቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት ማቋቋሚያ ሕግ ወጥቶ በሥራ ላይ እስኪውል ማንኛውም መዛግብትና ሰነዶች በነበሩበት ሁኔታ ተጠብቀው እንዲቆዩ ሰርኩላር አስተላለፉ።"

በማሳሰቢያው መሠረትም የባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገር ቅርስ የሆኑ መዛግብት በነበሩበት ሁኔታ ተጠብቀው መቆየት መቻላቸው በመጽሔቱ ተገልጿል።

ወመዘክር የታተሙ፣ በከፊል የታተሙና ያልታተሙ ጽሑፎች አሰባስቦ ከመጠበቅ ባሻገር ወደቀጣዩ ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነትም አለበት።

ባለፊት ዓመታት ግቡን ምን ያህል አሳክቷል? ስንል የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሽመልስ ታዩን ጠይቀናል።

ኃላፊው እንደሚሉት፤ ኤጀንሲው መሰብሰብ የሚገባውን ያህል መዛግብት አልሰበሰበም። ለዚህ በምክንያትነት የሚያስቀምጡት የጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ ባለቤት የሆኑ የሀይማኖት ተቋሞች መዛግብት ለተቋሙ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ነው።

"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንም ይሁን የእስልምና ጉዳየች፤ በመስጅድና በገዳም ያሉ መዛግብትን አይሰጡንም። ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበት ለነበረው የሥነ ጽሑፍ ሀብት በመቆርቆር 'ማን የኛን ያህል ሊጠብቃቸው ይችላል' ከሚል እምነት ማጣት የመነጨ ሊሆን ይችላል።"

የነዚህን መዛግብት ዋና ማግኘት ባይቻልም፤ ተቋሙ ዲጂታል ቅጂ ይወስዳል። መዛግብቱ ሰው ሰራሽ ወይም ተፈጥሯዊ አደጋ ቢደርስባቸው ቅጂውን መጠቀም ይቻላል።

ማንኛውም የጽሑፍ፣ የድምፅ ወይም የምስል ህትመት የሚያወጣ ግለሰብ አልያም ተቋም፤ ሦስት ቅጂ ለወመዘክር መስጠት ቢገባውም፤ ስንቶች ያደርጉታል? የሚለው አጠያያቂ ነው።

"እነሱም ያልሰጡን እኛም ያልሰበሰብናቸው አሉ" ይላሉ አቶ ሽመልስ።

ከግለሰቦች የአርባ ቀን መታሰቢያ ካርድ አንስቶ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር የተጻጻፈቻቸው ደብዳቤዎች በተቋሙ ይገኛሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ከተቋሙ ሠራተኞች ጥቂቱ

በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው መጽሐፈ ሄኖክ እና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለሞስኮው ንጉሥ ኒኮላስ ቄሳር የጻፉትን ደብዳቤ ጨምሮ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ)ያስመዘገበቻቸው 12 የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችም ለጎብኚዎች ክፍት ናቸው።

በቀጣይ ክታብ አልፋራይድ፣ ክታብ አልሙሳጣፊ፣ መጽሐፈ ድጓ እና ባህረ ሃሳብ በዓለም አቀፍ መዝገብ እንዲሰፍሩ ጥያቄ ቀርቧል።

በዓመታት መረጃ የማሰባሰብ ሂደት ክፈተት ከተፈጠረበት ወቅት አንዱ ዘመነ ደርግ እንደነበር አቶ ሽመልስ ይናገራሉ።

በወቅቱ የህትመት ቅጂ የማሰባሰብ ሥራ ያከናውኑ የነበረ ቢሆንም፤ መንግሥት አልፈልገውም ያለውን መረጃ ማከማቸት አይቻልም ነበር።

"የኔ መረጃ ከዛኛው ይበልጣል፤ የኔ ድርጅት ይበልጣል፤ ይባል ስለነበረ ሁሉንም አይነት ህትመት ማሰባሰብ አልተቻለም። መረጃ ማቃጠል፣ ማውደምና እንዳይገኙ ማድረግ የተበራከተው በዛ ዘመን ነው።"

ወመዘክር ውስጥ ለዓመታት በቴክኒክና ስልጠና ክፍል የሠሩት አቶ ተስፋዬ ካሱ በበኩላቸው "ትውልዱ አንባቢና የሚጽፍም ነበር። ነገር ግን በፖለቲካ አቋም መሰብሰብ የማንችላቸው መረጃዎች መኖራቸው ስብስቡን ጎድቶታል" ይላሉ።

በሌላ በኩል ወቅቱ ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ ብዙ የተደከመበት መሆኑን በበጎ ያነሳሉ። ወደ 70 የሚጠጉ ቤተ መጻሕፍት የነበሩበት ዘመን ከመሆኑ ባሻገር አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቤተ መጻሕፍት ሙያ ትምህረት ይሰጥ ነበር። ዛሬ ላይ ግን ይህ ነው የሚባል የስልጠና ተቋም ባለመኖሩ በወመዘክር ተነሳሽነት እንደ አቶ ተስፋዬ ያሉ ባለሙያዎች የአጭር ጊዜ ስልጠና ይሰጣሉ።

አቶ ሽመልስ የቀድሞውን ወመዘክርን ከዛሬ ጋር ሲያነጻጽሩ፤ ንጉሡ የራሳቸውን መጻሕፍት ለወመዘክር እንደሰጡት ቤተ መጻሕፍትን የመደገፍ ተግባሩ በሌሎች መሪዎችም መቀጠል ነበረበት ይላሉ።

"ስንቱ መሪ ነው ለዜጎች አስቦ ለቤተ መጻሕፍት መጽሐፍ የሚሰጠው? ትውልድን በእውቀት ለማነጽ የሚሞክር መሪስ ማነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ ተስፋዬ በተለያየ ዘመን የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች በወራሪዎች መዘረፋቸው፣ በሕገ ወጥ መንገድ እየተሰረቁ መውጣታቸው ትልቁን ክፍተት እንደፈጠረ ያስረዳሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ከወመዘክር የመጻሕፍት ስብስቦች መካከል

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎች እንግሊዝ ጣልያንና በሌሎችም ሀገሮች ይገኛሉ። በውጪ ዘራፊዎች ብቻ ሳይሆን በእርስ በእርስ ጦርነትም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

"የፈረንሳይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት አንዱ የስብስብ ክፍሉ የኢትዮጵያ ማኑስክሪፕት ነው። ከቤተ መንግሥት፣ ከትምህርትና ሥነ ጥብበ ሚኒስቴርና የአጥቢያ ኮኮብ ማኅበር ቤተ መጻሕፍት መዛግብት በጣልያኖች ተዘርፈዋል" ይላሉ በቁጭት።

አቶ ሽመልስ ባለፈው ዓመት ከሀገር ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ሊወጡ የነበሩ 100 የብራና መጻሕፍት በጉምሩክ ተይዘው ለወመዘክር መሰጠታቸውን አስታውሰው፤ "ይህ በጣም ያሳዝናል። ትውልዱ ማንነቱን፣ ታሪኩን እየሸጠና አሳልፎ እየሰጠ ነው። ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድ ማሰብ ይገባ ነበር" ይላሉ።

ባለሙያ ማጣትና ሌሎችም ተግዳሮቶች

ዋነኛ ትኩረቱን በቤተ መጻሕፍትና በቤተ መዛግብት ሙያ ላይ አድርጎ ስልጠና የሚሰጥ ተቋም አለመኖሩ በዘርፉ ክፍተት እንደፈጠረ አቶ ሽመልስና አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ።

አቶ ሽመልስ "በመዛግብት አስተዳደርና በሪከርድ ሥራ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠናም ስለሌለ መዛግብቶች እየተጎዱ ነው፤ በባለሙያ መያዝ ሲገባቸው ልምዱና እውቀቱ በሌላቸው ሰዎች እጅ ይገኛሉ" ይላሉ።

ኤጀንሲው ይህንን ክፍተት ለመሙላት ማስተማሪያ አዘጋጅቶ የቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ስልጠና ይሰጣል።

አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ ቤተ መጻሕፍት መስፋፋት እንዳለባቸው ሁሉ ባለሙያዎችም መበራከት አለባቸው።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የኤጀንሲው መዋቅር ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ያስረዳሉ። ተቋሙ ራሱን ችሎ በሚንስትር ደረጃ ቢዋቀር የተሻለ ነው ይላሉ።

አሁን ከክልሎች ጋር በጋራ የመሥራት ስልጣን በአዋጅ ስለሌለው መገደቡን ይናገራሉ። አዋጁ እንዲሻሻል ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን አለመፅደቁን ያክላሉ።

"ራሱን ችሎ የቆመና ተጠሪነቱ ቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን ጉዳዮቹን ቶሎ ያሰፈጽማል።"

በሌላ በኩል ሀገር በቀል እውቀት ዘመን ተሻግሮ በዚህኛው ትውልድ እምብዛም ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ብዙዎች ይስማሙበታል።

"የንባብ ባህል እንዲዳብር እንፈልጋለን። በእውቀት የበለጸገና በምክንያት የሚያምን ማኅበረሰብ ያስፈልገናል። ትውልዱ ጥንታዊ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ፍልስፍናና ሀብቶቹን እንዲያውቅ እንሻለን" ሲሉ ኃላፊው ይናገራሉ።

በወመዘክር ያሉትን የሥነ ሕዋ ምርምር፣ የመድሀኒት ቅመማና ሌሎችም ሀገር በቀል እውቀት የያዙ መዛግብትን ትውልዱ እንዲጠቀምባቸው አቶ ሽመልስ ያሳስባሉ።

ጥንታዊ የብራና መጸሕፍትን ምስጢር መመርመር ይቻል ዘንድ የግዕዝና የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠት እንደጀመሩም ያስረዳሉ።

በዲጂታል ቅጂ ከዘመኑ ጋር መራመድ

ዓለም ወደ ዲጂታል መረጃ ክምችት እየተሸጋገረ እንደመሆኑ፤ ሰዎች ከየትም ቦታ ሆነው በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በኮምፒውተር መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ ይመርጣሉ።

ተቋሙም ጥንታዊ መዛግብትን ዲጂታል ቅጂ በማዘጋጀት ይታወቃል። ቀደምት የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ከንክኪ መጠበቅ ስላለባቸው ግለሰቦች በቅጂዎቹ ይጠቀማሉ።

አቶ ሽመልስ "ጥናትና ምርምር የሚያደርግ ሰው የግድ ጣና ገዳማት፣ ድሬ ሼህ ሁሴን መሄድ አያስፈልገውም። ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የተከማቸውን መጠቀም ይችላል" ይላሉ።

እምቦጭ የጣና ቂርቆስ መነኮሳትን ከገዳሙ እያስለቀቀ ነው

ዲጂታል ስነዳ ከኢትዮጵያ አልፎ ከተቀረው ዓለም ጋር ለመተሳሳርም አንድ መንገድ ነው።

ኤጀንሲው 200ሺህ የሚጠጉ የመረጃ ሀብቶች ያሉት ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ዲጂታይዝ የተደረጉት 2537 ይሆናሉ። ከነዚህ መካከል 1173 ማኑስክሪፕት፣ 256 መዛግብት ይገኙበታል።

በማይክሮፊልም የተያዙ 11ሺህ መረጃዎችም ይገኛሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ