"ሥልጣን በአማራና በኦሮሞ መካከል የሚደረግ ቅርጫ መሆን የለበትም" ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አጭር የምስል መግለጫ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

ሰሞኑን የገቢዎች ሚኒስትር ለአንድ ብሔር ያደላ ሹመት ይሰጣል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቅሬታ ሲነሳበት ነበር።

የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ የተነሳውን ቅሬታ በሚመለከት ሲመልሱ፤ "ሠራተኞች በብሔር ላይ ቅሬታ አላነሱም" ይላሉ።

አንድ ሠራተኛ በችሎታው ተመዝኖ ለቦታው ብቁ ሲሆን ብቻ እንደሚመደብም ተናግረዋል።

"አመራሩን በተመለከተ አብዛኛው የጉሙሩክ ቅርንጫፎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያሉት" የሚሉት ወ/ሮ አዳነች፤ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሞጆ፣ አዳማ፣ ጅማና ሞያሌ የፌደራል ጉሙሩክ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች መኖራቸውን በማስታወስ፤ በነዚህ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የክልሉን ቋንቋና ባህል የሚያውቅ አመራር መመደቡን አረጋግጠዋል።

"ከመቶ ምናምን ፓርቲ ሴት የምናገኘው አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ሊሆን ይችላል" ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

አክለውም በፖለቲካ ወይም በሌሎች መስፈርቶች ይሰጡ የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎች እንደቀሩ አሳውቀው፤ ብቃት ዋነኛው መስፈርት መሆኑን አረጋግጠዋል። ሃገሪቷ ፌዴራላዊ አሠራር ስለምትከተል በክልል ያለንም አሠራር ልክ እንደዚያው ሕብረ ብሔራዊ አሠራርን የማንፀባረቅ ዓላማ እንዳላቸውም አብራርተዋል።

"ሥልጣን በአማራና በኦሮሞ መካከል የሚደረግ ቅርጫ መሆን የለበትም። የማንኛውም ብሔር ተወላጅ ለማንኛውም ሥራ ተወዳድሮ ብቃት ካለው ማግኘት ይችላል።"

በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚሠራም ለቢቢሲ ተናግረዋል። እንደ ምሳሌም ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር እና መቀሌን ጠቅሰው "በሁሉም ቅርንጫፎች ያሉት ኃላፊዎች ከባህሉም ከወጉም እንዲተዋወቁ አድርገናል" ብለውናል።

ቅሬታ አቅራቢዎች እንደ ምሳሌ የጠቀሷቸው ውስንና የተመረጡ ቅርንጫፎች በመሆናቸውም የመሥሪያ ቤቱን አሠራር እውነታ አያንፀባርቅም በማለት ሥራው በሂደት ላይ ቢሆንም የቅርንጫፎቹን አመራር ዝርዝር በፌስቡክ ገፃቸው ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

"በኦሮምያ ክልል ያሉት ቅርንጫፎች ውስጥ የሚሠሩት ሦስት ምክትል ኃላፊዎችም እንኳ ከሌላ ብሔር የተውጣጡ እንዲሆኑ ተደርጎ ነው መዋቀሩ የተሠራው" በማለት ሃሳባቸውን አብራርተዋል።

ሚኒስትሯ "በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ በእነዚህ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ምክትል ኃላፊዎች የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ስለዚህ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ስልጣን ላይ ኦሮሞ በዝቷል የሚለው ሐሰት ነው" በማለት ቅሬታውን ያጣጥላሉ።

"አመራር ስንመድብ የመጀመሪያው መስፈርታችን ብቃትና ችሎታ ነው" የሚሉት ወ/ሮ አዳነች፤ ሀገሪቷ በፌደራሊዝም ስርዓት የምትደዳር እንደመሆኗ የተመጣጠነ የብሔር ተዋፅኦ እንዲኖር እናደርጋለን ብለዋል።

በስህተት የተሰጣቸውን 1 ሚሊየን ብር የመለሱት መምህር

የገቢዎች ሚኒስትር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሰበሰበው ገቢ ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እንደሆነ ያስታወቁት ሚኒስትሯ፤ "ዘንድሮ የሰበሰብነው 145 ቢሊየን ብር ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት በ13 ቢሊየን ብር ይበልጣል" ብለዋል።

ይህንንም በመቶኛ ሲያስቀምጡት የዘጠኝ ነጥብ አምስት እድገት ማሳየቱን ይናገራሉ። አክለውም እንሠራለን ብለው ካቀዱት ጋር በማነጻጸር "አሁንም ጉድለቶች አሉ" ይላሉ ሚኒስትሯ።

"የሀገሪቱን ገቢ የማመንጨት አቅም ስናየው የሚያኮራ ሥራ ሠርተናል ብለን አናስብም። ነገር ግን የተሠራው ሥራ በቀላሉ ያሳካነው አይደለም። በመሥሪያ ቤቱ ትልልቅ የመዋቅር ማስተካከያዎችና ሪፎርሞች አድርገናል። ግብር ከፋዩ ዜጋ በፈቃደኝነት ተነሳስቶ መጥቶ እንዲከፍል ሁኔታዎችን አመቻችተናል። የሰው ኃይልን በማብቃት፤ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን እንዲሁም የግብር ከፋዮችን ለማነቃቃት የተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ስናካሂድ ነበር። ያገኘነው ስኬት የነዚህ ድምር ውጤት ነው።"

"በራሷ ገቢ የምትተማመንና መቆም የምትችል ሀገር ማየት እሻለሁ"ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የነበረው ብልሹ አሠራር የንግዱ ማህበረሰብ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥና ግብር በአግባቡ እንዳይከፍል አድርጎት ነበር የሚሉት ሚኒስትሯ፤ በተሠሩት የለውጥ ሥራዎች ይህንን ማስተካከል መቻላቸውን ይገልፃሉ።

"በዚህ አመት ለመሰብሰብ ያቀድነው 170 ቢሊየን ብር ነበር" ያሉት ወ/ሮ አዳነች፤ ሀገሪቱ ወደ ውጪ ከምትልካቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባቸው እቃዎች ታክስና ቀረጥ በሚፈለገው መጠን መሰብሰብ አለመቻሉን ገልጸዋል።

የውጪ ምንዛሬ እጥረትም ግባቸውን እንዳያሳኩ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀስ ተናገረዋል።

ዘረኝነት ለእናቶች ሞት ምክንያት እየሆነ ነው?

"ከሀገር ውስጥ የምንሰበሰበውን ገቢ ከ80 በመቶ በላይ አሳክተነዋል፤ ትልቁ ፈተና ከውጪ ከሚገቡ እቃዎች የምንሰበስበው ገቢ ነው።" በማለት የኮንትሮባንድ እቃዎች ግብይት እንዲሁም ሕገ ወጥ የውጪ ሀገራት ገንዘብ ዝውውር በሀገሪቱ ውስጥ ሕገ ወጥ ንግድ እየተስፋፋ እንደሆነ ያመላክታል ሲሉ ያስረዳሉ።

በየክልሎቹ የሚገኙ የኮንትሮባንድ እቃዎች ክትትል የሚደረግባቸው የፍተሻ ጣቢያዎችን መዋቅር በማጠናከር ችግሩን ለመቅረፍ ሙከራ እንደሚያደርጉም ተናገረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ