አፍጋኒስታናዊቷ ጋዜጠኛና የፖለቲካ አማካሪ መገደል ቁጣ ቀሰቀሰ

ሚና ማንጋል Image copyright AfghanPresidential Inofrmation Coordination Center

የአፍጋኒስታን ፖለቲከኞችና የሴቶች መብት ተሟጋቾች የቴሌቪዥን ጋዜጠኛዋ በጠራራ ፀሐይ መገደል አስቆጥቷቸዋል፤ ተገቢውን ፍትህም እንድታገኝ እየጠየቁ ነው።

ሚና ማንጋል ወደ ፖለቲካው ከመምጣቷ በፊት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበረች ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ካቡል ውስጥ ከቅርብ ርቀት በተተኮሰባት ጥይት ነበር የተገደለችው።

የአፍጋን የመንግሥት ባለስልጣናት ገዳዮቿን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ቃል ገብተው ፖሊስ ምርመራውን እያደረገ መሆኑንና እስካሁን ከግድያው ጀርባ ማን እንዳለ አልታወቀም ብለዋል።

ቅዳሜ ዕለት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ለአፍጋን የሕዝብ እንደራሴ የባህል ጉዳዮች ኮሚሽን አማካሪ የነበረችው ማንጋል ወደ ስራ ገበታዋ እየሄደች በነበረችበት ተገድላለች ሲሉ ተናግረዋል።

"ምርጫው እንዲራዘም እንፈልጋለን" አቶ አንዷለም አራጌ

"ይህንን ሐውልት የኢትዮጵያ ሕዝብ አሠሩላቸው"

አውሮፕላን ያለ ፊት ጎማው ያሳረፈው አብራሪ

የአፍጋኒስታን ከፍተኛው ፍርድቤት፣ የሲቪል ሶሳይቲ ቡድኖች እና የፀረ ፆታዊ ጥቃት ኮሚሽኑ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ማንጋል በፌስ ቡክ ገጿ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማስፈራሪያ ዛቻዎች እየደረሷት መሆኑንና ለሕይወቷ እንደምትሰጋ ፅፋ እንደነበር የሴቶች መብት ተሟጋች የሆነችው ዋዝማ በቲውተር ገጿ ላይ አስፍራለች።

የፖሊስ ቃል አቀባዩ ለሮይተርስ "የዛቻው ዓይነት ግልፅ አይደለም፤ የቤተሰብ ግጭቶችንም ማየታችን አይቀርም" ብለዋል ።

ሞቷ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ አፍጋኒስታናውያን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሀገሪቱ ሴቶች ላይ ስለሚደርስ ጥቃት እየፃፉ ይገኛሉ።

አንዳንዶች ጥቃቱ በጠራራ ፀሐይ መፈፀሙን ሲፅፉ ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ በካቡል አንፃራዊ ደህንነትና ሠላም አለ በሚባልበት ሥፍራ መከሰቱን በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ በ2018 አፍጋኒስታንን ለጋዜጠኞች ፍፁም አደገኛ የሆነች ሃገር ሲል ፈርጇታል።