"አብጃታን ሀይቅ ለማለት ይከብዳል" የአብጃታ ሻላ ሀይቅ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ

ሀይቅ ላይ የሚታዩ አእዋፋት Image copyright Getty Images

አብጃታ ሀይቅ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ሊጠፋ እንደሚችል ይፋ የተደረገው በቅርቡ ነበር። ቀድሞ ስፋቱ 194 ኪሎ ሜትር የነበረው ሀይቅ ዛሬ 73 ኪሎ ሜትር ሆኗል። ጥልቀቱ ደግሞ ከ14 ሜትር ወደ 2.5 ሜትር ማሽቆልቆሉ ተገልጿል።

የአብጃታ ሻላ ሀይቅ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ባንኪ ሙደሞ እንደሚሉት፤ ሀይቁ ለመጥፋት የተቃረበው የተለያዩ ሰው ሰራሽ ተጽዕኖዎች ስር ስለወደቀ ነው።

ሀይቁን ከሚቀላቀሉ ገባር ወንዞች አንዱ ከዝዋይ ሀይቅ የሚሄደው ቡልቡላ ወንዝ ነው። ይህም ወንዝ ሰው ሰራሽ ጫና ውስጥ መውደቁ ወንዙን ሙሉ በሙሉ አድርቆታል።

የጣና ሐይቅን ሌሎችም አረሞች ያሰጉታል

"በዝዋይ አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ድርጅቶች የሚጠቀሙት የወንዙን ውሀ ነው። የሶዳ አሽ ድርጅት ከአቢጃታ ሀይቅ ውሀ በቱቦ እየሳበ ለፋብሪካው ሥራ ያውላል። ወደ 30 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በዓመት ይጠቀማሉ" ይላሉ አቶ ባንኪ።

ከዚህ በተጨማሪ በሀይቁ ዙሪያ የሚገኘው ደን ተመናምኗል። የአፈር መሸርሸር ሀይቁ በደለል እንዲሞላ አድርጓል። በደለሉ ምክንያት ሰዎችና የዱር እንስሳትም መንቀሳቀስ አልቻሉም።

ፓርኩ ውስጥ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን፤ የነዋሪዎቹ እንቅስቃሴ ለሀይቁ መድረቅ ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ያስረዳሉ።

የቀንድ ከብቶች መሰማራት ያስከተለው ገደብ የለሽ ግጦሽ እንዲሁም የደን ጭፍጨፋ የፓርኩንና የሀይቁንም ደህንነት አደጋ ውስጥ ጥለውታል።

አቶ ባንኪ "ሀይቁን ሀይቅ ለማለት ይከብዳል" ሲሉ አቢጃታ የሚገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ይናገራሉ።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ. . . ውሃ!

የሀይቁ መጠን ስለቀነሰ ሀይቁ ላይ የሚኖሩ አእዋፋት ቁጥር ተመናምኗል። ቡልቡላ ወንዝን የሚጠቀመው አካል ከድርጊቱ ተቆጥቦ ወንዙ በቀጥታ ወደ ሀይቁ መፍሰስ ካልጀመረ አብጃታ ተስፋ አለው ለማለት ይቸገራሉ።

Image copyright Taly Zion Barishansky

አብጃታ እንደማሳያ ተጠቀሰ እንጂ አብኞቹ የኢትዮጵያ ሀይቆች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እንደ ሀሮማያ ሀይቅ የጠፉ የውሀ ሀብቶችም አሉ።

"የአፍሪካ የውሀ ሀብት ማማ" እየተባለች የምትሞካሸው ኢትዮጵያ ሀይቆቿን መጠበቅ እንደተሳናት የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ይህ ሀይቅ ሊጠፋ ነው፤ ያ ሀይቅ ሊከስም ይህን ያህል ዓመት ቀርቶታል የሚሉ ዜናዎች መስማትም እየተለመደ መጥቷል።

ሀይቅ ለማለት የማያስደፍሩ "ሀይቆች"

አብጃታ ሻላ ሀይቅ ብሔራዊ ፓርክ ከተለያዩ አህጉሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኛ አእዋፋት መገኛ ነበር። ቱሪስቶች ከሚያዘወትሯቸው ፓርኮች አንዱ ሲሆን፤ እንደ ፍላሚንጎ ያለ ወፍን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት መኖሪያ ነው።

የአቢጃታ መጥፋት ብዝሀ ሕይወት ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ ባሻገር የቱሪስት ፍሰት ሲቀንስ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖም ይኖረዋል።

የተለያዩ የኢትዮጵያ ሀይቆች ህልውና ለምን አስጊ ሆነ? ስንል የብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት፤ እጽዋት ብዝሀ ህይወት ዳይሬክተር ዶ/ር ዴቢሳ ለሜሳን ጠይቀን ነበር።

ክፍል 1 ፡በፅኑ የታመመው የዓባይ ወንዝ

እሳቸው እንደሚሉት፤ እንደ አቢጃታ፣ ጨለለቃ፣ ዝዋይ ያሉ ሀይቆች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሱባቸው ምክንያቶች አንዱ በሀይቆቹ ዙርያ ግብርና መካሄዱ ነው። የእርሻ ሥራ እንደናይትሮጂን፣ ፎስፈረስ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ከመውሰዱ በመጨማሪ ደለልም ይፈጥራል።

ሀይቅን ጨምሮ ሌሎችም የውሀ አካላት ሲጠፉ አሳ፣ የተለያዩ እጽዋትና አዕዋፍትም ይመናመናሉ።

"ውሀማ አካላትን ከግምት ያላስገቡ ኢንቨስትመንቶች አንድ የችግሩ መንስኤ ናቸው። ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን እንደ አቢጃታ ያሉት ሀይቆች በዚህ ተጎጂ ናቸው። አቢጃታ ሻላ አካባቢ የሶዳ አሽና የአበባ ፋብሪካዎች አሉ" ይላሉ።

የፋብሪካዎች ተረፈ ምርት በአግባቡ አለመወገዱ ወደ ውሀ አካል ከሚለቀቀው ኬሚካል ጋር ተደማምሮ የውሀ አካላት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

ዶ/ር ዴቢሳ እንደ ማሳያ በሚጠቅሱት ጨለለቃ ሀይቅ አካባቢ የጀልባ መዝናኛ ነበር። አሁን ግን ግብርና በመስፋፋቱ የውሀ ሀብቱ እየጠፋ ሰለሆነ ወደ አካባቢው ለመዝናናት መሄድ አይታሰብም።

"ተፈጥሮ ላይ ሊደርስ ስለሚችለው ተጽዕኖ ተገቢው ጥናት ሳይደረግ የሚሠሩ መንገዶችና ድልድዮች እንስሳትና እጽዋት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ" ይላሉ ዳይሬክተሩ።

ምን ተጽዕኖ አሳደረ?

የውሀ አካላት መጥፋት ተፈጥሯዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሀይቅና ሌሎችም የውሀ አካላት መጥፋታቸው ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ ነው።

አብዛኛው የመሬት ክፍል ውሀ እንደመሆኑ፤ የውሀ አካል ሲጠፋ ለእንስሳትና እጽዋት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ህልውናም ስጋት ይሆናል።

አሁን እያገገመ እንደሆነ የሚነገርለት ሀሮማያ በጠፋበት ወቅት ያነጋገርናቸው የሀሮማያ አካባቢ ነዋሪዎች የሀይቁ መጥፋት በእለት ከእለት ህይወታቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ገልጸውልን ነበር።

ወንዶች የማያወሯቸው አምስት አሳሳቢ ነገሮች

በድሪ የሱፍ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ አሳ ማስገር እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት መቸገራቸውን ነግረውን ነበር። በውሀ እጥረት ምክንያት የቀንድ ከብቶቻቸውን እንዳጡ፤ አካባቢውን ለመጎብኘት ከጅቡቲ እና ሌሎችም አካባቢዎች ይሄዱ የነበሩ ቱሪስቶች ፍሰት መቋረጡንም ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚመረተው ሀረር ቢራና የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ሀሮማያ ሀይቅን መጠቀማቸው ሀይቁ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረውም ነበር።

እንክብካቤና ጥበቃ ካልተደረገለት ሊጠፋ ተቃርቧል የተባለው አቢጃታ ሀይቅም ተመሳሳይ ስጋት አለበት። ይህም ተፈጥሮውን ተከትⶀ የሚመጣውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማጣት ነው።

ዶ/ር ዴቢሳ የውሀ አካላት የማኅበረሰቡ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወናወኑባቸው መሆናቸውን የሚናገሩት እንደ እሬቻና ጨንበላላ ያሉ ሥርዓቶችን በማጣቀስ ነው።

የሀይቆች ጉዳይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያም ነው።

ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ዴቢሳ እንደሚሉት፤ ሀይቆችን ጨምሮ የውሀ ሀብቶች የሚጠበቁበት ግልጽ መርህ ያስፈልጋል።

"አሁን እንደ ፖሊሲ ያለው እንደመስኖና ኢነርጂ፣ ግብርና፣ ደን ልማት ባሉ ዘርፎች ነው። ራሱን የቻለ የውሀ ክፍልን የሚያስጠቅ ሕግ ያስፈልጋል" ይላሉ። የውሀ ሀብት ጥበቃ በተለያዩ ዘርፎች ተበታትኖ የሚሠራ ሳይሆን በአንድ ተቋምና በወጥ መርህ የሚመራ መሆን እንዳለበት ያስረጋጣሉ።

አሁን ላይ የውሀ ሀብት ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ተረቆ እስከሚጸድቅ እየተጠበቀ ይገኛል።

በአንድ አካባቢ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሲካሄድ ከጀርባው ባሉ ተቋማት መካካል መናበብ ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ። ኃይል ሲመነጭ ውሀ የሚጠፋ ከሆነ፤ መንገድ ሲሠራ ዛፍ የሚቆረጥ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ እያመዘነ ይሄዳልና።

እናት አልባዎቹ መንደሮች

ዶ/ር ዴቤሳ ሀይቆች ከተጋረጠባቸው አደጋ መውጣት የሚችሉት ሀገር አቀፍ ፖሊሲ ሲጸድቅና ተቋሞች ሲናበቡ ነው ሲሉ፤ አቶ ባንኪ በበኩላቸው ማኅበረሰቡ የተፈጥሮ ሀብቱን መንከባከብ እንዳለበት ይናገራሉ።

እሳቸው የሚያስተዳድሩት የአቢጃታ ሻላ ፓርክ አቅራቢያ ያለው ማኅበረሰብ ደን እንዳይጨፈጭፍና ከብቶች እንዳያሰማራ እንዲሁም ወጣቶች አካባቢውን እንዲያለሙ የጀመሯቸው እንቅስቃሴዎች ፍሬያማ ካልሆኑም አቢጃታን ዳግም አናየው ይሆናል።