ቻይናዊው ለውሾቹ ባወጣው ስም ምክንያት ዘብጥያ ወረደ

ቻይናዊው ውሻ ከአጨቃጫቂ ስሙ ጋር Image copyright Beijing News

በምስራቃዊ ቻይና የሚኖር ባን የተባለ ወጣት ለሚያሳድጋቸው ሁለት ውሾች ባወጣላቸው "ሕገ ወጥ" ስም ምክንያት ዘብጥያ ወረደ።

በቤይጂንግ የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ባን ውሾችን እያዳቀሉ በማርባት የሚታወቅ የ30 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ሰኞ እለት ሁለት የሚያሳድጋቸው ውሾችን ፎቶ አንስቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋራ በኋላ ስማቸውን 'ቼንጉዋን' እና 'ዤግዋን' እንዳላቸው ይገልጻል።

የውሾቹ ስም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነታረኪያ ሆነ። የማንዳሪን ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሚሉት፤ የውሾቹ ስም መንግሥት እና የመንግሥት ሠራተኛ ማለት ነው።

ቼንጉዋን በከተሞች አካባቢ ተቀጥረው የሚሠሩ እና ቀላል ወንጀሎችን ለመከላከል ላይ ታች የሚሉ ሲሆኑ፤ ዤግዋን ደግሞ መደበኛ ያልሆኑ እንደ በጎ ፈቃደኛ ያሉ የማኅበረሰብ ሠራተኞች ናቸው።

"ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም" የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

እናት አልባዎቹ መንደሮች

''ኢትዮጵያን ወደተሻለ ስፍራ ሊወስዳት የሚችል ሌላ መሪ የለም'' የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት

ጋዜጣው እንዳተተው፤ ወጣቱ ለውሾቹ ይህንን ስም ያሸከማቸው ለቀልድ ቢሆንም የአካባቢው አስተዳደር ከዚህ ስም ውስጥ የሚፈለቀቅ ደስታ ወይም ቀልድ አልታያቸውም፤ በይበልጥ ደግሞ ቼንጉዋን ከሚለው ስም።

የዪንግዡዎ ፖሊስ "ይህ የሕግ አስከባሪ አካላትን መዝለፍ" ነው በማለት በግለሰቡ ላይ ምርመራ የጀመሩት ወዲያውኑ ነው።

አክለውም የቻይናን ሕግ አንስተው፣ አንቀፅ ጠቅሰው ዘብጢያ ያወረዱት ሲሆን፤ 10 ቀናትም እዚያው ማሳለፍ አለበት ብለዋል።

አንድ የፖሊስ ኃላፊ እንዳሉት፤ የግለሰቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ፅሁፍ "ዜጎች ላይና የከተማዋ አስተዳደር ስሜት ላይ ጉዳት የሚያደርስ" ነው።

ባንም በድርጊቱ መፀፀቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ጋዜጣው እንደዘገበው "ሕጉ መኖሩን አላውቅም ነበር፤ ሕገ ወጥ መሆኑንም አላወቅኩም" ብሏል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ነገሩ የሳቅ ጅረት ሆኖላቸው ሲሳለቁ፤ አንዳንዶቹም የትኛው ሕግ እንደሚያስቀጣቸው አልያም እንደማያስቀጣቸው ሲከራከሩ ተስተውሏል።