ናይጄሪያ፡ በረመዳን ምግብ የበሉ 80 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የረመዳን ምግብ Image copyright Getty Images

በናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት በረመዳን ጾም ወቅት በአደባባይ ምግብ የበሉ 80 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የግዛቲቱ እስላማዊ ሸሪያ ፖሊስ አስታውቀ።

ሂስባህ የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ የሸሪያ ፖሊሶች በግዛቲቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ቀናት ቁጥጥር ሲያደርጉ ነው ግለሰቦቹን የያዙት።

በፈረንጆቹ 2000 የሸሪያ ህግ እንደገና ተግባራዊ ከተደረገባቸው በርካታ የናይጄሪያ ግዛቶች መካከል አንዷ በሆነችው ካኖ ግዛት የሚኖሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጸሃይ ወጥታ እስትክጠልቅ ድረስ ምግብ በአፋቸው እንዳይዞር ህጉ ያዛል።

በፆም ወቅት ሰውነታችን ውስጥ ምን ይካሄዳል?

የቢላል አዛን የናፈቃቸው ሀበሾች

የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ያልሆኑ ሰዎች በቤታቸው እንደፈለጉት መመገብ የሚችሉ ሲሆን የእስልምና ተከታዮች ግን በጾም ወቅት በአደባባይ መመገብ አይችሉም።

በግዛቲቱ የሸሪያ ህጉም ከመንግሥታዊ ህጉ ጋር ጎን ለጎን በመሆን ይሰራል።

በካኖ ግዛት የሂስባህ ቃል አቀባይ የሆኑት አዳሙ ያህያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአደባባይ በመመገባቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉም ሙስሊሞች ሲሆኑ የሸሪያ ህጉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ያልሆኑት ላይ ተግባራዊ አይሆንም።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንዳንዶቹ ምግብ የበሉት የረመዳን ጨረቃን እራሳቸው ባለማየታቸው እንደሆነ ሲገልጹ፤ ሌሎቹ ደግሞ የጤና እክልን እንደ ምክንያትነት ቢያቀርቡም ባለስልጣናቱ ግን ተቀባይነት የሌለውና ምክንያት ነው ብለዋል።

ቴምር በረመዳን ለምን ይዘወተራል?

በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰማንያዎቹ ግለሰቦች ተግባሩን ሲፈጽሙ የመጀመሪያቸው በመሆኑ በከባድ ማስጠንቀቂያ መለቀቃቸውን ቃል አቀባዩ አክለዋል።

ከዚህ በኋላ በረመዳን ወቅት ከማፍጠሪያ ሰዓት ውጪ ምግብ ሲበሉ ቢገኙም ወደ ፍርቤት ተወስደው ለመዳኘት ቃል ገብተዋል።

የሂስባህ አባላቱም በረመዳን የጾም ቀናት ከተማዋን በማሰስ ተመሳሳይ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን እንደሚቀጥሉበትም ተገልጿል።

ተያያዥ ርዕሶች