ጫት የአእምሮ ጤናን እንደሚጎዳ ጥናት አመለከተ

ጫት

ጫት ለተለያዩ የአእምሮ ጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ አጥኚዎች እንደደረሱበት ባለፈው ሳምንት ኬንያ ውስጥ ለህትመት የበቃ የሳይንሳዊ ምርምር መጽሄት አስታወቀ።

"ጥናቱ በተደረገባቸው ጫት የሚጠቅሙ ሰዎች የአእምሮ ጤና ችግር ምልክቶች ከፍ ብሎ ታይቷል" ሲል ባለፈው ማክሰኞ የታተመው ቢኤምሲ ሳይኪያትሪ የምርምር መጽሄት አስፍሯል።

"ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም" የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

ሪፖርቱ እንደሚለው፤ ጫት መቃም ካልተለመዱ ክስተቶችና ከቅዠት ጋር በከፍተኛ ደረጃ የሚያያዝ ሲሆን እነዚህም የአእምሮ ጤና ችግር ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው።

ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት ከኬንያ መንግሥት ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ በሁለት አካባቢዎች ላይ በሚገኙ 831 ሰዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ላይ ተመስርተው ያገኙትን ውጤት ነው።

ከ831 የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 306ቱ ወይም 37 በመቶው ጫት ቃሚዎች ሲሆኑ ከግማሽ በላዩ ወንዶች ናቸው።

"ጫትን ማገድ ፈፅሞ የሚቻል አይደለም" ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድ

እድሜያቸው ከ10 - 17 ያሉ ታዳጊ ልጆችም ጫት እንደሚቅሙ በጥናቱ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም በአእምሮ ጤና ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል።

አጥኚዎቹ ይህ የታዳጊዎች ጫትን የመጠቀም ልማድ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተው፤ በለጋ እድሜ እንዲህ አይነት ሱስ አስያዥ ነገሮችን መጠቀም ከዕፅ ጋር ተያያዥነት ባላቸው በሽታዎች የመጠቃት እድልን ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህ ጥናት ላይ የተሳተፉ ሰዎች አልኮልና ሲጋራን ይጠቀሙ እንደሆነ የተጣራ ሲሆን፤ ጥናቱ እንዳመለከተው ከጫት መቃም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የአእምሮ ጤና ችግሮች አመላካች ምልክቶች ከአልኮልና ከሲጋራ አንጻር ከሚከሰቱ ችግሮች ጋር ተያያዥነት የላቸውም።

ጫትን መቆጣጠር ወይስ ማገድ?

ቀደም ሲል በጫት ላይ በተደረገ ጥናት አወንታዊ ውጤቶች እንዳሉት የተገለጸ ቢሆንም፤ አዲስ ይፋ በተደረገው ጥናት መሰረት ግን ጫት በወሲባዊ ግንኙነት፣ በምግብ ፍላጎት እንዲሆም ከውፍረት አንጻር ስለሚኖረው ውጤት አንዳች የተጠቀሰ ነገር የለም።

ጫትን በተመለከተ ይፋ በተደረገው ጥናት ላይ ከተሳተፉት ተመራማሪዎች በተጨማሪ ከሦስት የተለያዩ የኬንያ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ አጥኚዎችም ተሳትፈውበታል።