በኤርትራ የማህበራዊ ድረ ገጾች አገልግሎት ተቋረጠ

ዋትስአፕ በፌስቡክ የሚተዳደር መተግበሪያ ነው Image copyright Getty Images

በኤርትራ ውስጥ የማህበራዊ ድረ ገጽ የግንኙነት አገልግሎት መቋረጡን በሃገሪቱ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ አመለከቱ።

ከጥቂት ቀናት ወዲህ እንደ ፌስቡክና ሜሴንጀር ያሉ ማህበራዊ መድረኮችን መጠቀም እንዳልተቻለ የሃገሪቱ ዜጎች ተናግረዋል። ያገኘነው መረጃ እንሚያመለክተው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በፌስቡክና በሜሴንጀር መልዕክት መላክና መቀበል ይችሉ ነበር።

ጉዞ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ በፎቶ

እነዚህን የተዘጉ የማህበራዊ ግንኙነት መድረኮች ለመጠቀምም ሰዎች ቪፒኤን የተባሉትን እገዳውን ለማለፍ የሚያስችሉ መተግበሪያዎች እንደሚጠቀሙም ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኤርትራ በማህበራዊ የትስስር ድረ ገጾች ላይ ተጥሏል ስለተባለው እገዳ ምንነትና ምክንያቱን በተመለከተ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

አንዳንዶች እንደሚሉት ግን በአሁኑ ወቅት ኤርትራ የነጻነት በዓሏን ለማክበር እየተዘጋጀች በመሆኑ ከጸጥታ ጥበቃ ጋር የተያያዘ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ሌሎች ደግሞ በውጪ ሃገራት ያሉ የመንግሥት ተቃዋሚዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች በኩል የሚያስተላልፉትን መልዕክት ለመከላከል የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ይናገራሉ።

ቢቢሲ ከኤርትራ መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

አሥመራ፡ የአዛውንቶች ከተማ

የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ስርጭት መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው ዓመት ኤርትራ ወስጥ 71 ሺህ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሲኖሩ ይህም ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ ብዛት 1.3 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው።

ኤርትራ በዓለማችን ውስጥ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተደራሽነት ካለባቸው ሃገራት መካከል ትመደባለች።