የ74 ዓመቱ ኮ/ል ካሳዬ አጭር የመፈንቅለ መንግሥት ማስታወሻ

መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የካቲት 12/1970 ዓ.ም ሞስኮ Image copyright TASS
አጭር የምስል መግለጫ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የካቲት 12/1970 ዓ.ም ሞስኮ

ኤርትራ የሚገኘው የ102ኛው አየር ወለድ ኢታማዦር ሹም ነበርኩ ያኔ።

ግንቦት 8 ቀን ነው፤ ማክሰኞ 'ለታ ድንገት ጄ/ል ደምሴ ቡልቶ ቢሮ በአስቸኳይ ትፈለጋለህ ተባልኩ። መኪናዬን አስነስቼ እሳቸው ቢሮ ሄድኩ። እኔ ስደርስ ብ/ጄ ካሳዬ ጨመዳ ውስጥ ነበሩ፤ እሳቸው ሲወጡ እኔ ገባሁ።

‹‹አቤት ጌታዬ!›› አልኳቸው። ‹‹አዲስ አበባ ትንሽ ግርግር አለ፤ ሁለት ብርጌድ ጦር ይዘህ ሄደህ በአስቸኳይ አረጋጋ›› አሉኝ። ጄ/ል ቁምላቸው ተጨማሪ ትዕዛዝ ይሰጥኻል ተባልኩ።

ጄ/ል ቁምላቸው ቢሮ ስደርስ፣ ‹‹መጣህ ካሳዬ! በል ተከተለኝ›› ብለው መኪናቸውን አስነሱ። ከኋላ ከኋላ ስከተላቸው፣ ስከተላቸው አሥመራ አየር ኃይል ደረስን። ፊት ለፊታችን ራሺያዎች ለመንግሥቱ በሽልማት የሰጧቸው አውሮፕላን ቆማለች። በዚህ አውሮፕላን አዲስ አበባ እንሄዳለን አሉኝ።

‹‹ልብስና ማስታወሻ አልያዝኩም እኮ፣ ጌታዬ›› ስላቸው፣ ‹‹…በል በሚቀጥለው አውሮፕላን ድረስብን›› ብለውኝ ገቡ። ቶሎ ቤት በርሬ ልብስና ማስታወሻ ይዤ ስመለስ አውሮፕላኗ ሳትነሳ ደረስኩ።

አውሮፕላኗ ውስጥ 70 የሚሆኑ ሰዎች ተሳፍረዋል። አየር ወለዶች ደግሞ በአራት አንቶኖቭ ተጭነው ተከትለውን ይመጣሉ።

አውሮፕላኗ ወደ ምጽዋ አቅጣጫ ያዘችና ከዚያ ወደ ቃሩራ ሄደች። ከዚያም ተመለሰችና ልክ መረብን ስንሻገር ይመስለኛል ጄ/ል ቁምላቸው ብድግ ብለው ተነሱና አንዲት ወረቀት ይዘው ማንበብ ጀመሩ። የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ የሚደርስበትን ችግርና መከራ አወሩና ሲያበቁ...መጨረሻ ላይ አስደነገጡን። እኔም በደንብ ትዝ የምትለኝ መጨረሻ ላይ የተናገሯት ነገር ናት…።

‹‹ኮ/ል መንግሥቱ ተገድለው ከሥልጣን ተወግደዋል!›› አሉ።

በጣም ነው የደነገጥኩት፤ እኔ ከአሥመራ ስነሳ የማውቀው ነገር አልነበረማ። በአውሮፕላኑ ላይ የነበርነው በአጠቃላይ 73 እንሆናለን። ያ ሁሉ ሰው ሲያጨበጭብ እኔ ግን ፈዝዤ፣ ደንዝዤ ቀረሁ። እንደመባነን ብዬ ነው ማጨብጨብ የጀመርኩት።

Image copyright William Campbell
አጭር የምስል መግለጫ ኢምፔሪያሊዝምን በመቃወም በአብዮት አደባባይ ሚያዚያ 23/1969 የተደረገ ሰልፍ፣

አዲስ አበባ የሚቀበለን አጣን

እኛ 11 ሰዓት ተኩል ላይ ኤርፖርት ደርሰን ስልክ ብንደውል፣ ብንደውል ማን ያንሳ። ሬዲዮ ብናደርግ ማን ያናግረን። መከላከያ ደወልን፤ ማንም ስልክ አያነሳም። ምድር ጦር ደወልን፤ ማንም የለም። ግንኙነቱ ሁሉ ተቋርጧል። ለካንስ እኛ ከመድረሳችን በፊት ነገሩ ሁሉ ተበለሻሽቷል።

ለምን በለኝ…፣ በ9፡30 አካባቢ ጄ/ል አበራም ሚኒስትሩን ጄ/ል ኃይለጊዮርጊስን ገድሎ አምልጧል። እኛ ይሄን ሁሉ አናውቅም። እኛ የምናውቀው ኮ/ል መንግሥቱ መገደላቸውን ነው።

በዚያ ሰዓት እኛ ይዘነው የመጣነውን ጦር የሚያስተባብር ሰው አልነበረም። እኛ ገና ሳንደርስ ነው ከልዩ ጥበቃ ብርጌድ ታንክ መጥቶ መከላከያን የከበበው። እንደነገርኩህ እኛ ይሄን አናውቅልህም። እኛ የምናውቀው መንግሥቱ መገደሉን ነው።

መንግሥቱ እና የኮሎኔል አጥናፉ ኑዛዜ

ብቻ ምናለፋህ…ተከታትሎ የመጣውን አየር ወለድ ግማሹ እዚያ ኤርፖርት ዙርያ ጥበቃ ማድረግ ጀመረ። ሌላው አቃቂ ቃሊቲ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ተመድቦ ከውጭም ከውስጥም ሰውም ሆነ ተሸከርካሪ እንዳይገባ እንዳይወጣ አደረገ።

የቀረነው ወደ ምድር ጦር አቪየሽን ግቢ ሄድን። ከጦላይ የመጣ 'ስፓርታ' ጦርም እዚያው ተቀላቀለን።

የግንቦት 8 አመሻሽ- በጎማ ቁጠባ አካባቢ

እየመሸ ሲሄድ ግራ ተጋባን። ጄ/ል ቁምላቸው ጠሩኝና «በቃ ወደ መከላከያ እንሂድ» አሉኝ። ምንም እንኳ ግንኙነታችን ቢቋረጥም አመጣጣችን እዚያ መከላከያ ሚኒስቴር ለሚገኙ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ከለላ መስጠት ስለነበር ነው ወደዚያው ያመራነው።

አንድ ሻለቃ ጦር ይዘን በምድር ጦር መሐንዲስ፣ በባልቻ ሆስፒታል ላይኛው በኩል፣ አድርገን በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አልፈን ጤና ጥበቃ ጋ ደረስን። አንድ ሻለቃ ጦር ይዘናል። እዚያው ጎማ ቁጠባ ጋ አስቀመጥናቸውና እኛ ለቅኝት ወደ መከላከያ ተጠጋን።

እንደነገርኩህ መሽቷል። እንዲያውም እኩለ ሌሊት አልፏል…። ግን ጨረቃዋ ድምቅ ብላ ወጥታ ነበር። የሚገርምህ ያን ምሽት ሁሉ ነገር ማየት ትችላለህ። በቃ ምን ልበልህ ልክ እንደ ፀሐይ ነበር የምታበራው።

ከላይ ከጎማ ቁጠባ መጥቼ ብሔራዊ ቲያትር አደባባዩ ጋ ለቅኝት ስቀርብልህ ከኢትዮጵያ ሆቴል በታች ትራፊክ መብራት አለ አይደል? ወደ ፍልዉሃ መሄጃ…? እዚያ አንድ ታንክ ቱሬቱን እያዘቀዘቀ ወደኔ ጂፕ እያስተካከለ ሲመጣ አየሁት። እኔ መትረየስ ጂፕ ላይ ነው የነበርኩት። ቶሎ ቀኝ ወደኋላ ተጠምዘዝ አልኩት ሾፌሩን።

እንደገና በላይ በኩል ዞረን ለማየት ስንል ከፒያሳ በኩል ሌላ አንድ ታንክ ቱሬንቱን ወደኛ እያስተካከለ ሊመታን ተዘጋጀ። ምናልባት አንድ ነገር ቢያጋጥም ለመተኮስ ነውኮ ወደኛ የሚያነጣጥረው። በቃ ተመልሼ ወደ ጎማ ቁጠባ ሄድኩ።

እኛ እስከዚህ ሰዓት ድረስ መከላከያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አናውቅም። መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉንም አልሰማንም። እነ ጄ/ል መርዕድም በሕይወት ያሉ ነው የመሰለን። መንግሥቱ ኃይለማርያም መወገዱን ብቻ ነው የምናውቀው።

ቢቢሲ፡ መሣሪያ ታጥቃችኋል?

እኔና ቁምላቸው ይዘነው የመጣነው ሠራዊት ሁለት አሞርካ አለው። አራት አፈሙዝ ያለው አሞርካ። እሱንም ቢሆን ያንኑ ምሽት ከልዩ ጥበቃ ብርጌድ የማረክነው ነው።

ቢቢሲ፡ ይቅርታ ግን ኮ/ል፣ አሞርካ ምንድነው?

አሞርካ የኮሪያ ባለሁለት አፈሙዝ፣ ሽልካ የመሰለ ሁለት አፈሙዝ ያለው ዙ 23 ጥይት የሚጎርስ ከባድ መሣሪያ ነው። ሁለት ነበሩ ከልዩ ጥበቃ ብርጌድ የመጡ። ምድር ጦር ሲገቡ ወታደሮቹን ማረፊያ ወስደን ማረክናቸውና ሾፌር መድበን፣ ተኳሾቹን ከአየር ወለድ ጨምረን ነው ወደ ጎማ ቁጠባ አካባቢ የሄድነው።

ከዚያ ከጄ/ል ቁምላቸው ጋር ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን ስልክ አግኝተን መደወል ጀመርን። መከላከያ ስልክ የሚያነሳ ሰው የለም። አር-ፒ-ጂ የለ፤ ታንኩን በምን እንምታው? በቃ ጧት መልሶ ማጥቃት እናደርጋለን ብለን ያን ሌሊት ከጎማ ቁጠባ ወደ ምድር ጦር ተመለስን።

የቀድሞዎቹ መሪዎች ኃይለማርያም ደሳለኝና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተገናኙ

እዛ ስንደርስ ጄ/ል ቁምላቸው መጣሁ ብለውኝ ሄዱ። ከዚያ ወዲያ ተያይተን አናውቅም።

Image copyright Mondadori Portfolio
አጭር የምስል መግለጫ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ፣ አዲስ አበባ፣ 1960ዎቹ

«ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያ እንባቸው መጣ»

የታሠርነው ቤተ መንግሥት ነበር። እዚያ ትልቅ አዳራሽ አለ፤ የንግሥት ዘውዲቱ ጠጅ መጥመቂያ የነበረ ነው። የአሥመራ ሞካሪዎችም በአሰቃቂ ሁኔታ የፊጢኝ ታስረው እየጮኹ ሲቀላቀሉን ትዝ ይለኛል። 112 እንሆን ነበር።

ታስረን እያለን ጓድ መንግሥቱ ሁለት ጊዜ ጎብኝተውናል።

የመጀመርያ ቀን የመጡት አብዮት አደባባይ ለሕዝብ ንግግር ያደረጉ ቀን ነው። ግንቦት 10 ይሁን 11 ብቻ ረሳሁት። ከአብዮት አደባባይ በቀጥታ እኛ ጋ መጡ። እኛ ደግሞ ያኔ ፖሊሶች ተመድበውልን ቃል እንሰጥ ነበር። ያን ቀን መጥተው ዝም ብለው አይተውን ሄዱ።

ከዚያ ደግሞ ሰኔ 11፣1981 ቀን ተመልሰው መጡ። ያኔ ወደ 118 መኮንኖች እንሆናለን በንግሥት ዘውዲቱ ጠጅ መጥመቂያ አዳራሹ ውስጥ የታሰርነው።

አዳራሹ አንድ በር ብቻ አለችው። ምንም ብርሃን የለውም። የምታየው አንዳች ነገር የለም። እርግጥ ጧትና ማታ ለአንድ ሰዓት ፀሐይ እንሞቃለን።

ሰኔ 11 ቀን ለሁለተኛው ጊዜ ሲመጡ ታዲያ ፀሐይ እየሞቅን ነበር። ተሰብሰቡ ተባለ። ግማሹ ጋቢ ለብሷል። ግማሹ ጭንቅላቱ ላይ ጠምጥሟል።

ከዚያች ዕለት ትዝ የሚለኝን ልንገርህ…? መንግሥቱ ዞር ዞር ብለው አዩን፤ ከዛ ወደ ጄ/ል አብዱላሂ ዞረው፣ ‹‹አብዱላሂ!» አሉ።

የመከላከያ ሚኒስትር አስተዳደር የነበሩት ጄ/ል አብዱላሂ፣ «አቤት ጌታዬ» አሉ፤

"አንተ የአዲስ አበባ ዙርያ ጦር ጥበቃ 6 ወር ደመወዝ እንዳልተከፈለው ታውቅ የለም እንዴ?" አሏቸው።

‹‹አዎን አውቃለሁ ጌታዬ›› ብለው መለሱ።

‹‹ይሄ በኔ ላይ ሴራ ለመጠንሰስ ያደረከው አይደለም?? አይደለም ወይ…?!››

ከዚያ ደግሞ ዞር ሲሉ ሰለሞን በጋሻውን አዩ። ጄ/ል ሰለሞን የአየር ኃይል ኢታማዦር ሹም ነበሩ።

"ሰለሞን! እናንተ በሂሊኮፕተር ሽርሽር ስትሄዱ እኔ ፈንጂ ውስጥ በእግሬ እዞር ነበር፤ ይሄን ታውቃለህ...?" አሉ።

በዚህን ጊዜ ጄ/ል ሰለሞን ጥያቄ ለመጠየቅ [መልስ ለመስጠት] እጃቸውን አወጡ። ልክ ከመናገራቸው በፊት ግን ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም እንባቸው ግጥም ሲል ታየኝ። ፊት ለፊታቸው ነበርኩ።

እንባቸው የመጣው…እልህ ይዟቸው ይመስለኛል። እንባ ሊቀድማቸው እንደሆነ ሲያውቁ 360 ዲግሪ ዞሩና ወጥተው ሄዱ። በኛ ፊት ሲያለቅሱ መታየት አልፈለጉ ይሆናል።

ከዚያ በኋላ ጓድ መንግሥቱን አይተናቸው አናውቅም።

Image copyright Francois LOCHON
አጭር የምስል መግለጫ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ንግግር ሲያደርጉ-ኀዳር 21፣ 1980 ዓ.ም

ሞት የሚጠባበቁ ታሳሪዎች ምን ይሉ ነበር?

አብረውኝ የታሠሩት ሁሉም መፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎች ናቸው። ከጄ/ል እስከ ሚሊሻ። እኔ እንዳውም ከኮ/ል በታች ላሉት 'ካቦ' ነበርኩ። ደርግ ተገለበጠ ሲባል እልል ብለህ መሬት ስመኻል ተብሎ የታሰረ ሚሊሻም አብሮን ነበር።

እነ ጄ/ል ኃይሉ ገ/ሚካኤል (የምድር ጦር አዛዥ)፣ ምክትሉ ሜ/ጄ/ል ዓለማየሁ ደስታ፣ የፖሊስ አዛዡ ሜ/ጄ ወርቁ ዘውዴ ሌሎችም ከአሥመራው አሰቃቂ ግድያ የተረፉት በሙሉ አብረውን አሉ።

ጄ/ል ፋንታ በላይ ግን ሦስተኛው ቀን መጡና ወዲያው ደግሞ ማዕከላዊ ሄዱ ተባለ።

እዚያ አዳራሽ ውስጥ ቁጭት ነበረ። ሰለሞን በጋሻውና ጄ/ል ተስፉ ለምሳሌ ይቆጩ ነበር። ብርጋዴር ጄኔራል ተስፉ ደስታ የአየር ኃይል የዘመቻ መኮንን ነበር። ብርጋዴር ጄኔራል ሰለሞን በጋሻው ደግሞ የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ነበር።

ከእኔ አጠገብ ነበር የሚተኙት። እሰማቸዋለሁ። ማታም ጠዋትም ‹‹ይሄ ሰውዬ አይለቀንም፤ ምናለ በለኝ ይገድለናል›› ይሉኝ ነበር። ያው የፈሩት አልቀረም።

ሁለቱም የሚቆጩበት አንድ ነጥብ ምን ነበር መሰለህ? ያኔ ኮ/ል መንግሥቱ [ወደ ምሥራቅ ጀርመን] ለጉብኝት በሚሄዱበት ጊዜ አውሮፕላኑ ሲነሳ ቀይ ባሕር ላይ እንዲመታ ተብሎ ነበር የተዘጋጀው። እና እነሱ ያ አለመደረጉ [ይቆጫቸው ይመስለኛል]።

ቢቢሲ፡ ኮ/ል አሁን በ74 ዓመትዎ ሲያስቡት መፈንቅለ መንግሥቱ ተሳክቶ በሆነ ብለው ይቆጫሉ?

እኔ ምንም እንደዛ አላስብም። ምክንያቱም እኔ ያለውን ሁኔታ ሳየው መንግሥቱም አጠፋ ብዬ በሱ የምፈርደው ነገር የለም። ምንም አላደረገም። ለኢትዮጵያ ጥሩ ነገር ነው የሠራው። እስር ቤት ሳለንም እነሱ ፊት እከራከር ነበር። የደርግ ደጋፊም ነበርኩ። መንግሥቱ ምን አደረገ?

መቼም አገሪቱ ውጊያ ላይ ብትሆንም፣ ጦርነት ቢበዛም፣ እሱም የኢትዮጵያን አንድነት ነው ይዞ የተነሳው። አገር እንዳይቆረስ ነው የታገለው። እኛ መኮንኖቹ ያጠፋነው ጥፋት ነው ለዚህ የዳረገን። አብዛኛውን ውጊያ ቦታ ላይ ለመሸነፍም የበቃነው ከአመራር ስህትት ነው። መረጃ ሾልኮ እየወጣ ነው። ችግሩ ከኛ ነበር እንጂ ከመንግሥቱ አልነበረም።

Image copyright William Campbell
አጭር የምስል መግለጫ ሚያዚያ 23/1969 ዓ.ም ወታደሮች መስቀል አደባባይ ላይ በተካሄደ ሰልፍ ኢምፔሪያሊዝምን እያወገዙ

ከሞት መንጋጋ ስለመትረፍ

እስር ቤት ሆነን እነ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ አሥመራ ላይ የደረሰባቸውን ስንሰማ አዘንን፤ እኛ ጋ ታስረው የመጡ መኮንኖች ናቸው የነገሩን። ያው በዚያ መንገድ መሞታቸው አግባብ አልነበረም። በሕግ ነበር መቀጣት የነበረባቸው።

ሁላችንም በቡድን በቡድን ተከፋፍለን ቤተ መንግሥት ውስጥ የተቋቋመ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ነበር የምንቀርበው።

እነሱ ሰኔ 12፣1982 ለውሳኔ ተቀጠሩ።

ሰኔ 11 ብርጋዴር ጄነራል ተስፉ ደስታ (የአየር ኃይል ዘመቻ ኃላፊ) ይናገር የነበረው ትዝ ይለኛል። ‹‹ዛሬ የመጨረሻችን ነው። ካሳዬ [ምናለ በለኝ] እኛ አንመለስም›› ይል ነበር።

ተሰነባብተን ነው የተለያየነው። እነሱም አንመለስም ይገድለናል ብለው ነው ተሰናብተውን የወጡት። ግንቦት 11 ቀን ነው። አብረን ነው ያደርነው። እነሱ ወደ ችሎተ ሄዱ፤ ምናልባት ይመጣሉ ብለን ስንጠብቅ ቀሩ።

ሞትን ቁጭ ብሎ መጠበቅ ምን ይመስላል?

እነሱ በተገደሉ በዓመቱ ግንቦት 23 ለውሳኔ ተቀጠርን። ከእኛ በፊት ግንቦት 15፣1983 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለውሳኔ የሚቀርቡ ጓደኞቻችን ነበሩ።

ያው እነሱ ሳይመለሱ ሲቀሩ እኛም ተመሳሳይ ነገር እንደሚመጣ ነው የምንጠብቀው፤ በእውነቱ እንወጣለን እንድናለን ብለን የምንለው ነገር አልነበረም። ያው የሞት ፍርድ ይፈረድብናል ብለን ነበር እንጠብቅ የነበረው።

በመሀሉ ግንቦት 13፣ መንግሥቱ ከአገር ወጡ ተባለና በተአምር ተረፍን። ይኸው በሕይወት አለን...

የስንብት ጥያቄዎች ለኮ/ል ካሳዬ ታደሰ

ቢቢሲ፡- ጄ/ል መርዕድ ንጉሤ እንዴት ራሳቸውን እንዳጠፉ ያውቃሉ?

ኮ/ል ካሳዬ፡- አላውቅም

ቢቢሲ፡- ጄ/ል አመሃ ደስታ ራሳቸውን እንዴት እንዳጠፉ ያውቃሉ?

ኮ/ል ካሳዬ፡- አላውቅም

ቢቢሲ፡- ጄ/ል አበራ አበበን በሕይወት መያዝ እየተቻለ ለምን የተገደሉ ይመስልዎታል?

ኮ/ል ካሳዬ፡- ጄ/ል አበራን እኔ ሳውቃቸው እጅ የሚሰጡ ሰው አይደሉም። ተታኩሰው ነው የሚሞቱት።

ተያያዥ ርዕሶች