የኢትዮጵያ ታሪክ መማሪያ መጻሕፍትን መከለስ ለምን አስፈለገ?

የታሪክ መማሪያ መጻሕፍት ለምን ይከለሳሉ? Image copyright DEA / C. SAPPA

የተመረጡ የፖለቲካ ትርክቶች ብቻ ጎልተውበታል በማለት ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት መጻሕፍትን ለመከለስ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፤ በመጨረሻ የብሔር ልሂቃን ባለመስማማታቸው ክለሳው ተቋረጧል የሚል ዘገባ ተሰምቶ ነበር።

ሆኖም ቢቢሲ ያናገራቸው የትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው ዘገባው ትክክል እንዳልሆነ፤ የታሪክ ትምህርት መጻሕፍት ላይ የተለየ ክለሳ እየተደረገ ሳይሆን እንደማንኛውም የመማሪያ መጻሕፍት እንደሚከለስ ተናግረዋል።

"በየጊዜው እየታረመ እየተስተካከለ ይሄዳል። የታሪክ ትምህርትም እንደሌሎች የትምህርት አይነቶች የማስተካከል ሥራ እየተሠራበት በመሃል ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ ነበር። የስርአተ ትምህርት አጠቃላይ ክለሳ የሚካሄድበት ወቅት በመድረሱ ሁሉንም ትምህርቶች እንደገና የምናይበት ጊዜ ላይ ደረስን። ስለዚህ የታሪክ ትምህርት ከሌሎች ትምህርቶች በተለየ መልኩ ሳይሆን እንደማንኛውም ትምህርት አንድ ላይ እንየው በማለት ስንሠራ የነበረውን ነገር አቆምን። ተቋረጠ፣ ተሰረዘ የሚባለው ነገር ተገቢ አይመስለኝም" ይላሉ አቶ እሸቱ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ተሰማ ተአ በበኩላቸው የታሪክ መጻሕፍቱን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ እንደነበር ይናገራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት መጻሕፍት ይዘት፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲሁም ትርክቱ አወዛጋቢነቱ እየጎላ መጥቷል።

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

በተለያዩ ታሪካዊ ሁነቶች ላይ ቅራኔዎች እየተንፀባረቁና በሕዝብ ዘንድ መለያየትን እያጎሉም መጥተዋል። ለዚህ በዋነኛነት የሚነሳው የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ ሚዛናዊነት ማጣት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

የታሪክ ትምህርት በጥልቀትና በብቃት ራሱ ታሪክ ምን እንደሆነ በትክክል የሚያስረዳ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ነገሥታትና የቤተ ክህነት ታሪክ ብቻ እንደሚጎላበት ፕሮፌሰር ተሰማ ያስረዳሉ።

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

የነገሥታቱንና የአሸናፊዎችን ታሪክ አጉልቶ የተሸናፊ ሕዝቦች ወገን የማይወከሉብት መሆኑ ትልቅ ችግር እንደሆነ ይገልፃሉ።

"ተሸናፊዎችም ታሪክ አላቸው፤ ታሪክ መስመር ያለው፣ በሁለት እግሩ የሚቆም፣ እውነትነትን የተመረኮዘና ሚዛናዊ ሆኖ የሚሄድ ነው" ይላሉ።

ለፕሮፌሰር ተሰማ የነገሥታት ታሪክ ሙሉ በሙሉ ትክክል መሆን ያለመሆኑ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፤ ዋናው ችግር የሕዝብን አስተዋፅኦ ያለማንፀባረቅና የመጨፍለቅ ትርክት እንደሆነ ይናገራሉ።

"ለአሸናፊዎች ሀውልት ይቁም ሲባል ስለተሸናፊዎች ምንም አይነት ነገር አይደረግ መባሉ በታሪክ እይታ ልክ አይደለም" ይላሉ።

የታሪክ ትምህርት መጻሕፍት ትርክት ሚዛን ያጣ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ተሰማ፤ ለምሳሌ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለራሳቸው ሕዝብ ምንም ነገር የሌለበትና ስለሌሎች ሕዝቦች ትልቅነት ብቻ የሚነገርበት ትምህርትን የመማር ፍላጎት እንደማይኖራቸው ያስረዳሉ።

ታሪክ በራሱ አከራካሪ እንደመሆኑ መጠን የአተራረኩ ዘዴም ሕዝቦች ራሳቸውንም ሆነ አስተዋፅኦቸውን በማያዩበት ወቅት የሚፈጠሩ ክፍተቶች እንዳሉና በአሁኑ ወቅት ለተፈጠሩ የብሔር መስተጋብር ችግሮች አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይናገራሉ።

በተለይም በአንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ላይ ብዙዎቹ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌሉ ተደርጎ መጻፉ አደገኛ እንደሆነም ይናገራሉ።

እናት አልባዎቹ መንደሮች

"ታሪክ መስታወት ነው፤ የዛሬውን ሁኔታ ለመገንዘብ እንዲሁም ወደፊት የሚመጣውን ለመቀየስ ታሪክ አስፈላጊ ነው" በማለት አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። =

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ለመቀየርና የተለያዩ ሕዝቦችን ማንነት ለማካተትና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አካታች የሆነ ታሪክን ለመጻፍ ጅምሮች የነበሩ ቢሆንም እስካሁን የተሳካ ውጤት ላይ አለመደረሱን ያመለክታሉ።

በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተሠሩ የመመረቂያ ፅሁፎች እንደሚያሳዩት፤ ይህንን ሚዛናዊነት የጎደለው ትርክትን ማስተካከያ የጠቆሙ የተለያዩ ፅሁፎች እንደተፃፉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ተሰማ፤ የእነዚህ ፅሁፎች ምክረ ሃሳቦች ተስተካክለው በትምህርት ስርአቱ እንዲካተቱ አስተያየት የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ በሃሳቡ የማይስማሙም አሉ ይላሉ።

ታሪክ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንደገና ይጻፍ ቢባልም፤ በተለይም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ታሪክ ተጣርሶ እንዳይጻፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

የቀደመ ታሪክ ላይ ማስተካከያ ይደረግ፤ ይጨመር ይቀነስ፤ ይህ ታሪክ ትክክል አይደለም ከተባለም መረጃ ማምጣራትና ማስረገጥ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች