"ማህበሩ የማያልፈው ቀይ መስመር የስራ ማቆም አድማ ነው"-ዶ/ር ገመቺስ ማሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት

ዶ/ር ገመቺስ ማሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጤና ህክምና ባለሙያዎች ለመንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ በአግባቡ ሊመለስ ባለመቻሉ በስራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የስራ ማቆም አድማውን እንደማይደግፍ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የጤና ባለሙያዎቹ ያነሱት ጥያቄ የማህበሩም እንደሆነ የተናገሩት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ጥያቄዎቹን በተለያዩ መድረኮች እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፍ እስከ መውጣት ድረስ እንደሚወስዱት ቢናገሩም የስራ ማቆም አድማ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀዋል። "እንደ ማህበር የማናልፈው ቀይ መስመር የስራ ማቆም አድማ ነው" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄ ወቅታዊና በአመታት ሲንከባለሉ የመጡ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ገመቺስ በአካሄዱ ላይ ማህበሩ የተለየ መስመር እንደሚከተሉ ተናግረዋል።

"አንድነት ቢኖረንና እንደ ሀኪም ማህበር አንድ አይነት ጥያቄ ብናነሳ ደስ ይለናል፤ ከእኛ ጋር እንዳይገጥሙ ያደረጋቸው ለእኛ ያላቸው ጥርጣሬና አመለካከት ነው። ይህንን ምንም ልናደርገው አንችልም፤ እኛ በስራ ከሐኪሙ ጎን መቆማችንን ማሳመን መቻል አለብን እንጂ ዛሬ ከኛ ጋር ካልሆናችሁ አንልም።" ብለዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሰላማዊ ሰልፎች ጥያቄያቸውን ማቅረባቸው አይዘነጋም።

ካቀረቧቸውም ጥያቄዎች መካከልም የደመወዝ ዝቅተኛ መሆን፣የጤና መድን ዋስትና፣ የኢንተርን ሃኪሞች የስራ ድርሻ ግልፅ አለመሆን፣ ሀኪሞች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች፣ የሆስፒታሎች ምቹ አለመሆን፣ የህክምና ስርአቱ አወቃቀር፣ የጤና ቁሳቁሶች አቅርቦት ችግር ይገኙበታል።

“ኢትዮጵያ አዲስ የጥላቻ ንግግር ህግ አያስፈልጋትም” አቶ አብዱ አሊ ሂጂራ

በችግሮቻቸውና በመፍትሄዎቹ ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር ውይይት ቢያደርጉም ከመንግሥት በኩል ያገኙት ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

መንግሥት ጥያቄያቸውን ለመመለስ ዝግጁ አለመሆኑን ጠቅሰው እስኪመለስ ድረስም በስራ ገበታቸው እንደማይገኙም በተለያዩ መንገዶች እየገለፁ ነው።

አራት ሺ አባላት ያሉት ማህበር በበኩሉ ከመንግሥት በኩል ማሻሻያና ሊቀረፉ ይገባቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮችንም አትተዋል።

ከነዚህም ውስጥ የሀገሪቱ የጤና ፖሊሲ የሚጠይቀውን ሪፎርም መሰረት በማድረግ እንዲከለስ፣ ሀገሪቱ ለጤና የምትመድበውን በጀት እንድታሻሽል፣ የታካሚና የህክምና ባለሙያ ግንኙነት እና የታካሚ መብትና ግዴታን የሚገዛ የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ ደመወዝ እንዲሻሻል፣ የትርፍ ሰአት ክፍያዎች ወጥ በሆነ መንገድ እንዲተገበሩ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግራቸው እንዲቀረፍ የሚሉት ይገኙበታል።

የታሪክ መማሪያ መጻሕፍት ለምን ይከለሳሉ?

የህክምና ባለሙያዎቹ ጥያቄ የማህበሩ ጥያቄ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ገመቺስ በተለያዩ መድረኮችም እነዚህን ጥያቄዎች ለአመታት ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

"አርባ በመቶ መብራትና ውሃ የሌለውን ሆስፒታል ብላችሁ አትጥሩ፤ መድኃኒት በሌለበት አገር ውስጥ የተሟላ የጤና አገልግሎት አለን አትበሉ ስንል ቆይተናል" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ማህበሩ በአጠቃላይ በህክምና ስርአቱ ላይ መፍትሄን አቅጣጫን ለመሚመለከታቸው አካላት እንዳቀረቡ የሚናገሩት ዶ/ር ገመቺስ ከዚህም ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች ደመወዝ ሀገሪቱ በተራቆተችበት ሁኔታ ሳይሆን የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እርዳታን በመለገስ ክፍተቱን እንዲሞሉ የሚለው ይገኝበታል።

እንደ ምሳሌነትም አንድ ሀኪም ሲመረቅ የሚያገኘው ደመወዝ 4700 ብር መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ገመቺስ ይህ በከፍተኛ ሁኔታ ሊሻሻል እንደሚገባም በመግለጫቸው አፀንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎቹ ጥያቄ ለግላቸው ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ እንደሆነም ዶ/ር ገመቺስ ተናግረዋል።

"የተነሱት ጥያቄዎች ከሰላሳ አመት በፊትም ይሁን አሁን ወቅታዊ ናቸው፤ የዛን ጊዜም ቢሆን ስናገለግል የነበረው ህብረተሰቡን ነበር። ከአመታትም በፊት ቢሆን ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ነበር የጠየቅነው ዛሬም ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ነው የምንጠይቀው" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች