የቦይንግ 737 ማክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የቦይንግ አብራሪዎች ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመጨረሻዋ ሰዓት አብራሪዎቹ ማድረግ የሚችሉት ምንም ነገር አልነበረም። በአብራሪዎቹ ክፍል ውስጥ የአደጋ ጊዜ ድምጽ ሲሰማ ዋና አብራሪውና ምክትሉ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ታግለዋል።

ልክ ወደ ምድር በፍጥነት ማስቆልቆል ሲጀምሩ ካፕቴን ያሬድ ጌታቸው በአየር ላይ ለመንሳፈፍ ሙከራ አደረገ። ነገር ግን ካፕቴን ያሬድ ይህንን በሚያደርግበት ሰዓት ኤምካስ የተባለውና አውሮፕላኑን በከፍተኛ ሁኔታ ወደላይ እንዳይወጣ ወይም ወደታች እንዳያሽቆለቁል ለመቆጣጠር ተብሎ የተሰራው ሥርዓት ይህንን ከማድረግ ገታው።

አውሮፕላኑም ወደታች ማሽቆልቆሉን ቀጠለ።

በዚህ ሁሉ ጭንቀት ካፕቴን ያሬድና ረዳቱ አህመድኑር ሞሃመድ መፍትሄ ለማግኘት መታገላቸውን አላቆሙም ነበር። በዚህ ጊዜ አውሮፕላኑ ሙሉ በሙሉ እራሱን በራሱ እያበረረ ነበር።

ካፕቴን ያሬድና ረዳቱ የበረራ ቁጥጥሩን በእነሱ እጅ ለማድረግ ከባድ አካላዊ ትግል ማድረግ ነበረባቸው። ሁለቱም የሚችሉትን ያህል ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀረ።

ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን ግን አውሮፕላኑ ለበረራ በተነሳ በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ በሰዓት 500 ሜትር እየተምዘገዘገ ወደ ምድር ተወረወረ።

149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሲከሰከስ የ35 ሃገራት ዜግነት ያላቸው ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ከእነዚህ መካከል 32 ኬንያዊያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 18 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮቶኮል ሻሀድ አብዲሻኩርን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞች ይገኙበታል።

ከአደጋው አምስት ወራት በፊት በኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ለማወቅ በተደረገው የምስለ በረራ ሙከራ ላይ እንደተደረሰበት አውሮፕላኑ ቁልቁል በአፍንጫው ባህር ላይ ሊከሰከስ መሆኑን ያወቁት ከ40 ሰከንዶች ያነሰ ጊዜ ሲቀራቸው መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን እ.ኤ.አ ኦክቶበር 26 ድረስ ብቻ ስድስት ያህል ችግሮች ገጥመውት ነበር። እነዚህ የገጠሙት ችግሮች በአየር ላይ እያለ ያለውን ፍጥነትና የከፍታ መረጃውን ያካትታሉ።

አውሮፕላኑ ከክንፎቹ እና በአየር ፍሰቱ መካከል ያለውን አቅጣጫ የሚለካውም ችግር ገጥሞት ነበር። አደጋው ከመድረሱ በፊት በነበረው በረራ አብራሪው አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት እንደነበር የሚያሳይ ምልክት ልኳል።

የኢንዶኔዢያ አውሮፕላን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ አፍንጫው የመደፈቅ ሁኔታ ሲገጥመው የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሚያሳው መሳሪያ በበረራው ጊዜ በሙሉ በርቶ ነበር።

በአደጋውም 198 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

የአውሮፕላኖቹን ወደ ላይ የመውጣትና የመውረድ ፍጥነት ንባብ እንደሚያመለክተው ሁለቱም አውሮፕላኖች ከፍና ዝቅ እያሉ እንደነበሩና አብራሪዎቹም ይህንን በመቆጣጠር አውሮፕላኖቹ ከፍ ብለው እንዲበሩ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ያሬድ ጌታቸው ችሎታን በተመለከተ አብራሪው ከ8 ሺህ ሰዓታት በላይ የማብረር ልምድ እንዳለው በመጥቀስ "የሚያስመሰግን ብቃት" እንዳለው መስክሮለታል።

አደጋው በደረሰበት ዕለትም አብራሪው ያሬድ ጌታቸው ችግር እንደገጠመውና ተመልሶ ለማረፍ ለበረራ ተቆጣጣሪዎች መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ እና ከአውሮፓ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን አጣሪ ባለሙያዎች በተሳተፉበት ምርመራ የመጀመሪያ ዙር ውጤት አውሮፕላኑ ለበራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመር ለመብረር በሚያስችለው ሁኔታ እንደነበር የገለጸ ሲሆን አብራሪዎቹም አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለውን ቅደም ተከተል ተግባራዊ ማደረጋቸውን አረጋግጧል።

በአውሮፓውያኑ 2015 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስመርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ተገኝተው ደስታቸውን ገልጸቀው ነበር።

በወቅቱም አውሮፕላኑ እጅግ የተራቀቀና ሁሉም አየር መንገዶች የሚፈልጉት ነበር። በዓለማችን ላይም ተወዳጁና ተፈላጊው አውሮፕላን ሆኖ ነበር።

የኢቲ በረራ ቁጥር 302 አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ቦይንግ በአደጋው ምክንያት ለጠፋው የሰው ህይወት ሃዘኑን በመግለጽ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንዳሳየው እንደ ከዚህ ቀደሙ ኤምካስ የተሰኘው ሶፍትዌር በተሳሳተ መረጃ 'አክቲቬትድ' (ሥራውን መጀሩን) ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

"አደጋን ሊያስከትል የሚችል ሁኔታን የመቅረፍ ሥራ የእኛ ነው። አውሮፕላኑ የእኛ ስሪት ነው። እንዴት እንደሚስተካከልም የምናውቀው እኛው ነን" በማለት ችግሩን እንደሚያስወግ ቃል ገብቶ ጥረት እያደረገ ነው።

ለኤምካስ ሶፍትዌር ማስተካከያ ከተደረገለት በኋላ 737 ማክስ አውሮፕላን ወደ በረራ ሲመለስ በበረራ ደህንነታቸው አስተማማኝ ከሆኑ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ ይሆናል በማለት የምርመራ ውጤቱን እንደሚቀበለውም አስታውቋል።

ቦይንግ አሰቃቂው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተከሰከሰበት ቦታ ላይ አዳዲስ መረጃዎች በመገኘቱ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹን በሙሉ ማገዱንም ገልጾ ነበር።

ኩባንያው እንዳሳወቀው ያሉትን 371 አውሮፕላኖች እስካሁን ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እንደገለፀው አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የተገኙ አዳዲስ መረጃዎችና የተጣሩ የሳተላይት ምስሎች አስተዳደሩ በጊዜያዊነት የእግድ ውሳኔውን እንዲያስተላልፍ አድርጎታል።

የአሜሪካ ፌደራል ኤቪዬሽን አስተዳደር ከብሔራዊ የትራንስፖርት ጥበቃ ቦርድ ጋር በመተባበር አደጋውን የሚመረምር ቡድን የላኩ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራው ዱካ ከላየን አየር መንገድ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተነግሯል።

በተጨማሪም የመከስከስ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የተገኙት መረጃዎች በላየን አየር መንገድ ከደረሰው ዕጣ ፈንታ ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸውም በተጨባጭ የሚያስረዱ መረጃዎች መኖራቸው የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ችግር እንዳለ ማሳያ ሆኗል።

የኢንዶኔዢያ አውሮፕላን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ አፍንጫው የመደፈቅ ሁኔታ ሲገጥመው የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሚያሳው መሳሪያ በበረራው ውስጥ በሙሉ በርቶ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ቦይንግ ኤምካስን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለአብራሪዎች መመሪያ ቢያወጣም፤ ነገር ግን በአውሮፕላኑ ወስጥ ያለው ሥርዓትን የሚቆጣጠረው ሶፍትዌር ላይ ያስፈልግ የነበረው ማሻሻያ ዘግይቶ ነበር ይፋ የተደረገው።

በተጨማሪም በበረራ ወቅት ችግር በሚያጋጥም ጊዜ አብራሪዎችን ሊያስጠነቅቅ ይችል የነበረው የማስጠንቀቂያ መብራትም አደጋው በደረሰባቸው ሁለቱ የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ አውሮፕላኖች ላይ አልተገጠመም ነበር።

ከሁለቱ አደጋው ከደረሰባቸው አውሮፕላኖች የተገኙ የበረራ መረጃዎችም ተመሳሳይነት እንዳላቸው መርማሪዎች አመልክተዋል።

የአውሮፕላኖቹን ወደ ላይ የመውጣትና የመውረድ የፍጥነት ንባብ እንደሚያመለክተው ሁለቱም አውሮፕላኖች ከፍና ዝቅ እያሉ እንደነበሩና አብራሪዎቹም ይህንን በመቆጣጠር አውሮፕላኖቹ ከፍ ብለው እንዲበሩ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ የአቪዬሽንት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት (ኤፍኤኤ) የቦይንግ ምርቶችን ደረጃና ጥራት በመቆጣጠርና በማጽደቅ ሂደት ላይ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለቦይንግ አሳልፎ መስጠቱ ዓለምን አስደንግጧል።

ባለሥልጣኑ ባሳለፍነው ሳምንት ለሲያትል ታይምስ የምርመራ ዘገባ በሰጠው ቃል፤ ባጋጠመኝ የፋይናንስ አቅም መመናመን የአውሮፕላኑ አምራች እራሱ የአዳዲስ አውሮፕላኖችን ብቃት በከፊል እንዲያረጋግጥ አድርጊያለሁ ሲልም አምኗል።

ለዚህም ነው ይህ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ያላቸው ሃገራት በአውሮፕላኑ ላይ ያለው ችግር ተጣርቶ መፍትሄን እስኪያገኝ ድረስ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ የተገደዱት።

የአውሮፕላኑ አምራች የሆነችው አሜሪካም ለአውሮፕላኑ አገልግሎት ላይ መዋል የተሰጠውን ፍቃድ በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ አዛለች።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገኛኛ ብዙኃን የኢትዮጵያው አየር መንገድ አብራሪ ይህን አውሮፕላን ለማብረር የሚያስፈልግን ተጨማሪ ስልጠና እንዳልወሰደ በመጥቀስ ያቀረቡት ዘገባ ከተለያዩ ወገኖች ቁጣንና ተቃውሞን አስከትሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አብራሪዎች አውሮፕላን አምራቹ ባወጠው እና በአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተቀባይነት ባለው መንገድ ተገቢውን ስልጠና መውሰዳቸውን አረጋግጧል።

ቦይንግ 737 ማክስ ሶፍትዌር ላይ እያደረገ የነበረውን ማሻሻያ መጨረሱንና ማሻሻያ ባደረገባቸው አውሮፕላኖች 207 በረራዎች ማድረጉን አሳውቋል።

አብራሪዎች አውሮፕላኑን ስለሚቆጣጠሩበት መንገድ ለፌደራል አቪዬሽን አድሚንስትሬሽን (ኤፍኤኤ) መረጃ እንደሚሰጥም ተገልጿል። የኤፍኤኤ ባለሙያዎች ቦይንግ ማሻሻያው እንዲጸድቅለት መረጃውን በሚቀጥለው ሳምንት ለኤፍኤኤ እንደሚያስረክብም ይጠብቃሉ።

ማሻሻያውም አብራሪዎች አውሮፕላኑን ከአደጋ ለመከላከል ይጠቀሙት የነበረውን አንድ መንገድ ወደ ሁለት አማራጭ አሳድጎታል። ቀደም ብሎም የአደጋ ጠቋሚ መልዕክት ይደርሳል ተብሏል።

ለፌደራል አቪዬሽን አድሚንስትሬሽን (ኤፍኤኤ) ተወካይ ሃላፊ ዳንኤል ኤልዊል እንደገለጹት ቦይንግ በሚቀጥለው ሳምንት ማሻሻያውን እስከሚያቀርብ ድረስ ምንም አይነት ውሳኔ አይሰጥም።

737 ማክስ አውሮፕላኖችም በአሜሪካ አየር ክልል ውስጥ በድጋሚ መብረር የሚጀምሩት እጅግ ጠንካራና የተራቀቀ የሙከራ ፈተናዎችን ማለፍ ሲችሉ እንደሆነ ተገልጿል።

አብዛኞቹ 737 ማክስ አውሮፕላን ያላቸው አየር መንገዶች የምስለ በረራ መለማመጃ የሌላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ለስልጠናው የሚያገለግለው ይህ ዘመናዊ መሣሪያ ባለቤት ነው።