"ሀኪሙ ትግሉን አቀጣጠለው እንጂ የሚታገለው ለታካሚው ነው" የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሬዚደንት ሐኪሞች

በትናንትናው ዕለት በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱ የሕክምና ባለሙያዎች

"አንድ አባት የአንጀት መታጠፍ ገጥሟቸው ወደሆስፒታላችን መጡ" ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩልቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ድህረ ምረቃ ተማሪው ዶ/ር ዮናስ አደመ።

የመጡት ከመሸ ነበር። ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ቀዶ ጥገና እንዲደረግላቸው ተወሰነ። ቀዶ ጥገናው እንዳይደረግ ግን ጄኔሬተሩ ተበላሽቷል። መብራት ቢኖርም ያለጄኔሬተር ቀዶ ጥገና ማድረግ አይቻልም። ዶክተሩ እንደሚሉት የደም ምርመራ ማድረግ አልቻሉም።

"የሚያክሙን ሙዚቃዎች እንዳሉ ሁሉ የሚያውኩንም አሉ" ዶ/ር መልካሙ

ኋላ ላይ ሀኪሞችና ነርሶች ገንዘብ አዋጥተው የደም ምርመራው ሌላ የግል ሆስፒታል ተሠራ።

ያም ሆኖ በሆስፒታሉ ቀዶ ጥገና ማድረግ ስላልተቻለ ወደ ሌላ የመንግሥት ሆስፒታል ተላኩ። ሆስፒታሉ ደግሞ ታካሚው የሚያስፈልጋቸው የፅኑ ሕሙማን ክፍል ስለሌለው ሊቀበላቸው አልቻለም።

ታካሚው ማግኘት ያለባቸውን ቀዶ ጥገና ሳያገኙ ሁለት ቀን ቆዩ። የአንጀት መታጠፍ ሲቆይ ወደ ጋንግሪን ይቀየራል የሚሉት ዶ/ር ዮናስ "ይህንን እያወቅን እኚህ አባት ማግኘት ያለባቸውን ሕክምና ሳያገኙ ቆዩ" ይላሉ።

ከሁለት ቀናት በኋላ የማዋለጃ ክፍል ጄኔሬተርን በብዙ ቢሮክራሲ አስፈቅደን ቀዶ ጥገናው ተሠራላቸው ይላሉ። ሆኖም ታካሚው ከስድስት ሰአት በኋላ ሕይወታቸው አለፈ።

የአንዳችን አባት ወይንም የቅርብ ጎረቤት የሚሆኑ አባት መትረፍ እየቻሉ በብልሹ የሕክምና ስርዓት ሳቢያ ሕይወታቸው እንዳለፈ ዶ/ር ዮናስ ይናገራሉ።

ዶ/ር ዮናስ አሁን ያለውን የሀኪሞች ተቃውሞ ሀኪሙ አቀጣጠለው እንጂ፤ "ሀኪሙ የሚታገለው ምንም ማድረግ ለማይችለው ታካሚ ነው" ሲሉ የሰሞኑን የሀኪሞችና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የሥራ ማቆም አድማና የሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ለካንሰር ተጋላጮች እነማን ናቸው?

"የተሻለ ሕክምና ማግኘት የማይችለው ሕዝብ የሚገባውን የጤና አገልግሎት እያገኘ እንዲኖር ነው ትግላችን። በብልሹ የህክምና አሰራሮችና መሟላት ያለባቸው ነገሮች ባለመሟላታቸው መትረፍ የሚችሉ በርካታ ሰዎች እየሞቱ ነው። መትረፍ የሚችሉ እጆች፣ መትረፍ የሚችሉ እግሮች እየተቆረጡ ነው። ይህ መሆን የለበትም" ይላሉ።

ጥያቄዎቻቸው ምንድን ናቸው?

በዋናነት የተነሱት ጥያቄዎች ሦስት ናቸው ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩልቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲ ተማሪ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ታምራት። አንደኛውና ዋነኛው የሕክምና አሰጣጥ ሂደት ነው።

"የሕክምና አገልግሎቱ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው። በሕክምና ተቋማት ውስጥ ትንንሽ ከሚባሉት ጎዝ፣ ጓንት፣ መርፌ ጀምሮ ትልልቅ እስከሆኑት ምርመራዎችና ለሕክምና የሚያስፈልጉ እቃዎች እጥረት የታካሚዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው" የሚሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ ይህ እንዲስተካከል ሲጠይቁ በቂ ምላሽ ስላላገኙ ወደሰላማዊ ሰልፍና የሥራ ማቆም አድማ መሄዳቸውን ያስረዳሉ።

ሁለተኛው ጥያቄ በቂ የህክምና ቁሳቁስና አለመኖሩ ነው።

"ሕንፃ ስላለ ብቻ ጥሩ ህክምና የለም። ውጤቱ ጥሩ የሚሆነው በህክምና መስጫ ውስጥ ቁሳቁስ ሲሟላ ነው። የሕክምና ባለሙያው ውጤታማ፣ ደስተኛና በሙሉ አቅሙ የሚሠራ መሆን አለበት" ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል።

ዶክተሩ እንደሚሉት፤ የሕክምና ባለሙያው የኢኮኖሚ አቅም እጅጉን የተዳከመ ስለሆነ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን አሟልቶ ሥራውን በተገቢው ሁኔታ መሥራት አልቻለም።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"ጥያቄያችን የደመወዝ ብቻ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የህክምና ስርዓቱ እንዲቀየር አብሮን ሊቆም ይገባል"

ሦስተኛው የሀኪሞቹ ጥያቄ የደህንነት ጉዳይ ነው። "በተለያዩ ቦታዎች የሕክምና ባለሙያዎች እየተመቱ ነው። ለባለሙያዎች ክብር አለመኖሩና ጥሩ የሆነ የሕግ ከለላ አለመኖሩም ሀኪሞችን ለተለያየ ችግር እያጋለጣቸው ነው" ይላሉ ሐኪሙ።

የባህር ዳር ሀኪሞችም ተመሳሳይ ጥያቄ በማንገብ ትላንት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር። በሰልፉ ላይ የነበሩት ዶ/ር አብርሀም ሞላ "ሰልፍ የወጣነው ለደመወዝ ጥያቄ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የህክምና ስርዓቱ እንዲቀየር አብሮን ሊቆም ይገባል" ይላሉ።

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ የሆነው የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ገደፋው ክንዱ በበኩሉ፤ "እስካሁን የተሰጠን ምላሽ አጥጋቢ ስላልሆነ የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደውል መሆኑን መንግሥትና ሕዝብ ይወቅልን" በማለት የሀኪሞቹን ምሬት ያስረዳል።

በፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪምና የሰልፉ የፕሬስ ኃላፊ ዶ/ር አብራራው ታደሰ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ባለሙያዎቹን ማነጋገራቸውን አድንቀው፤ ምላሽ የተሰጠበት መንገድ እንዳላስደሰታቸው ይናገራሉ።

ዶ/ር አብራራው የሃኪሞች ማኅበርም ለመንግሥት ያደላ በመሆኑ የሀኪሞችን ችግር ይፈታል ብለው አያምኑም።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ጥራት ያላቸው የህክምና ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም በተገቢው መልኩ እንዲከፈል፣ በዘርፉ የፖለቲከኞች ሚና እንዳይኖር እንዲሁም የህክምና ፖሊሲው እንዲሻሻል ጥያቄ ቀርቧል።

ለምን አሁን?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩልቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስና ስፔላይዜሽን ክፍል ተማሪ የሆኑት ዶ/ር ጀማል ማርቆስ እነዚህ ጥያቄዎች አሁን የተነሱት በአገሪቱ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች የጤናውን ዘርፍ ስላካተቱ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩልቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ተማሪው ዶ/ር አብርሀም ገነቱም ሀሳቡን ይጋራሉ።

ዶ/ር አብርሀም "በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ዜጎች ያሻቸውን መናገር የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዓመታት በሙያ ማኅበሩ በኩል ስናነሳቸው የነበሩ ጉዳዮች በቂ ምላሽ ባለማግኘታችውና ችግሮቹ እየተባባሱ በመምጣታቸው፤ እንዲሁም ሁሉም ሰው ሀሳቡን በደንብ መግለፅ ሲጀምር የሁላችንም አጀንዳ እየሆኑ ስለመጡ ነው" ይላሉ።

የጤና ዘርፉ ለውጥ እንደሚያስፈልገውና የኢትዮጵያ ሕዝብም ለዓመታት ከለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሹ ይናራሉ።

"ማህበሩ የማያልፈው ቀይ መስመር የስራ ማቆም አድማ ነው"-ዶ/ር ገመቺስ ማሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ፋኩልቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንጎልና ሕብለ ሰረሰር ቀዶ ሕክምና ክፍል ተማሪ ለሆኑት ዶ/ር አብዱላዚዝ አብደላ ተቃውሞው አሁን የተነሳው የመናገር ነፃነት ስላለ ብቻ አይደለም። በሕክምና ተቋማት የሚሰጥ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን እንደምክንያት ያስቀምጣሉ።

ይህን ሀሳባቸውን የሚያጠናክሩት በትምሀርት ክፍላቸውን የደረሰውን አጋጣሚ በማስታወስ ነው።

"በአንጎል ቀዶ ጥገና ትምህርት ክፍል ውስጥ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁና አሁን አራተኛ ዓመት ሆኜ ነገሮች እየቀነሱ መጥተዋል። ይባስ ብሎ ከሁለት ሳምንት በፊት የ15 ዓመት ታዳጊ ሞተብን" ይላሉ።

የ15 ዓመቱ ታዳጊ ሊያጠና ወደጎረቤት እየሄደ ሳለ በሞተር ተገጭቶ ነበር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሄደው።

"እኛ ጋር ሲደርስ ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ነበርን። ሁለት የሚሠራ ቀዶ ጥገና ክፍል ነበረን። የነበረን እቃ ውስን ነበር። የነበረንን እቃ ለሁለቱ አካፍለን መሥራት ጀመርን። ሁለተኛውን ቀዶ ጥገና ክፍለ ውስጥ እየሠራን ሳለ ይህ ልጅ በድንገተኛ ክፍል በኩል መምጣቱ ተነገረን። ሲቲ ስካን ታይቶ ውጤቱ ሲመጣ ጭንቅላቱ ውስጥ ከላይኛው ሽፋን በላይ የተጠራቀመ ደም አለ። ይህ ልጅ በአስቸኳይ ቀዶ ጥገና ማግኘት አለበት። ኦፕሬሽን ክፍል ውስት ግን እቃ የለም" በማለት የተጠቀሙበትን እቃ አጥበው ወደ ስቴሬላይዜሽን ክፍል ለመላክ እንኳ ውሃ አለመኖሩን በምሬት ያስረዳሉ።

ጥቁር አንበሳ ውስጥ ረብዑና አርብና ውሀ የለም የሚሉት ሀኪሙ፤ "የሚሻለው አርብና እሮብ ውሃ የለም ብሎ መቀመጥ ነው ወይስ ታንከር ማስገባት ነው?" በማለት በቁጭት ይናገራሉ።

የክፍሉ ችግር ግን ይህ ብቻ አይደለም። ከሁለት ሳምንት በፊት ቀዶ ጥገናዎች እየተሰረዙ ነበር። ምክንያቱም ቀዶ ጥገና ክፍል የሚለበሰው (ድሬፕ) አለመኖሩ ነበር።

የልብስ ንፅህና መስጫው ተበላሽቷል መባሉን ያስታውሳሉ። የሕክምና ተቋሙን ችግር ለማስተካከል ፈቃደኝነት መጥፋቱንም ያክላሉ።

የአሜሪካው ፅንስ ማቋረጥ ሕግ ሆሊውድን አስቆጣ

"እኛ ሕብለ ሰረሰር ሕክምና እንማር ነበር። ነገር ግን አንድ መሣሪያ የለም ተብሎ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሲጠየቅ ቢቆይም ባለመገዛቱ እኛም ሳንማር፣ ታካሚውን ወደግል ተቋም በመላክ ለተጨማሪ ወጪ እየዳረግነው ነው" ይላሉ።

አንድ የሕብለ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ለመሥራት አምስት ወር እንደሚወስድባቸውና ታካሚዎች ወደግል ተቋማት ሲያቀኑ ደግሞ 120 ሺህ ብር ድረስ እንደሚከፍሉ ያስረዳሉ። "ይህን የቱ አቅመ ደካማ ነው የሚችለው?" ይላሉ ቁጭታቸው ፊታቸው ላይ እየተነበበ።

የሥራ ማቆም አድማን እንደ መፍትሔ?

ዶ/ር ዳንኤል "ሙሉ በሙሉ አድማ አልመታንም" በማለት የድንገተኛ ክፍል፣ የጽኑ ሕሙማን ክፍልና የወሊድ አገልግሎት ክፍል ሀኪሞች የሥራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ ያስረዳሉ።

"የሕዝቡ ስጋት የነበረው የሕሙማን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል። በእነርሱ አድማ ምክንያት የሚሞት ሰው ይኖራል የሚል ነው። ነገር ግን እነዚህ የጠቀስኳቸው ክፍሎች እና የሰው ልጅ ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚባልባቸው ክፍሎች የሚሠሩና ጥያቄያችንን የሚደግፉ ሐኪሞች ሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው ሲያገለግሉ ነበር።"

የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች

የጡት ካንሰር የያዛት የጡት ካንሰር ሀኪም

መንግሥት ይህንን ጥያቄ ያነሱ ሐኪሞችን ማመስገን አለበት የሚሉት ሐኪሙ፤ የብሔርና የሐይማኖት ጥያቄዎች በብዛት በሚነሱበት ዘመን አገርን የሚጠቅም ጥያቄ ሲነሳ ጥያቄውን ማክበር ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ

እንደዶክተሩ ገለጻ፤ ከመንግሥትም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት ፈቃደኝነቱ ቢኖር መፍትሔ ይገን ነበር። "ነገር ግን አሁን እየታየ ያለው ማስፈራራትና ተመልሰዋል የተባሉ ጥቂት ጥያቄዎችን መላልሶ ማውራት ነው" ይላሉ።

ዶ/ር ዮናስ ሀኪሞች የሚያደርጉት ትግል ግቡን እንደሚመታ ያምናሉ።

"ባለኝ መረጃ መሰረት ዓለም ላይ ከሀምሳ በላይ አገራት ውስጥ ሐኪሞች እኛ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች አንስተው አድማ መትተው ያውቃሉ። እነዚህ አድማዎች በአጠቃላይ ሙሉ በሙሉ ግባቸውን የመቱ ናቸው። የእኛም ትግል የፈጀውን ጊዜ ይፈጃል እንጂ ግቡን መምታቱ አይቀርም።"

አሁን በጥቂት ሆስፒታሎች የሚስተዋለው ጥያቄና ሰልፍ ወደ ሌሎች ሆስፒታሎችና በተለያዩ ሆስፒታሎች ወደሚሰሩ ሀኪሞች ተሸጋግሮ አገር አቀፍ አድማ እንዳይሆን ይሰጋሉ።

"ይህ ባይሆን ምኞታችን ነው። ከዛ በፊት ጥያቄያችንን ሰምተው ምላሽ ቢሰጡን ደስ ይለናል። አድማችንና ትግላችን በአገሪቱን የጤና ስርአት ለውጥ ያመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ይላሉ።

አክለውም "ጥያቄውን መጠየቅ የነበረበት ሕዝቡ ነበር ብለን እናምናለን" ይላሉ።

ቀጣይ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ዮናስ፤ መንግሥት ሁለት አይነት አማራጭ አለው ይላሉ።

"እኛ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አጀንዳ የለንም። የአገራችን የጤና ስርአት እንዲሻሻል እንፈልጋለን። ስለዚህ ከኛ ጋር ተወያይተው ችግሮች የሚሻሻሉበትን የጊዜ ሰሌዳ ቢያስቀምጡ፣ ከአገሪቷ አቅም በላይ ናቸው የሚባሉትን ችግሮችን ለይተውም ቁርጠኛነታቸውን ቢያሳዩን እኛም ወደሥራችን እንመለሳለን" ይላሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ውይይትና የተሰጣቸው መልስ አጥጋቢ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ጀማል፤ ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው እርምጃ እንዲወሰድ ይጠይቃሉ።

ዶ/ር ዮሐንስ በበኩላቸው፤ መንግሥት ተቃውሟቸውን ያሰሙትን ሀኪሞች ማባረርና ማሰር ሌላው "አማራጭ" አድርጎ እንደሚወስድ ያነሳሉ። ይህንን የሚሉት ሰሞኑን ከጥቁር አንበሳ አስተዳደሮች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን በማጣቀስ ነው።

"ይህ ከሆነ ግን ጥሩ ነገሮች አይፈጠሩም" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ዶ/ር ዳንኤል ሀኪሞች የአድማ ፍላጎት እንደሌላቸውና ሙያቸውን እንደሚወዱ ይናገራሉ።

"ጠዋት ገብቶ ስምንት ሰዓት የሚወጣ ሀኪም የለም። ሰላሳ ስድስት ሰዓት ሰርቶ የሚወጣ ሀኪም ነው ያለው። የኛ ጥያቄ ሀያና ሰላሳ አመት ሲጠየቅ የኖረ ነው። ይህ ችግር በኛ እድሜ ካልተፈታ፣ ሀኪሙ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ የሚደበደብ ከሆነ ችግሩ አይፈታም" ይላሉ።

ጤና የራቀው የፈለገ ህይወት ሆስፒታል

ችግሩን ፈጥረዋል ብለው የሚያስቧቸው ሰዎች "የመፍትሔው አካል ይሆናሉ" ተብለው ሲደራጁ ጥያቄያቸው እንደማይፈታ ይናገራሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩን አነጋግረን 'ከሳቸው በታች ያሉ ሰዎች መፍትሔ ይሰጣችኋል' ሲባል ተስፋ አስቆራጭ ነው" ይላሉ።