ባለ ዲግሪዋ ቆሎ ሻጭ፤ የህወሐት የቀድሞ ታጋይ ብርሃ አፅብሃ

ባለዲግሪዋ የቀድሞ ታጋይ ብርሃ አፅበሃ በመቀሌ ከተማ የኦቾሎኒ ንግድ ላይ ተሰማርታለች

ታጋይ ብርሃ አፅብሃ የህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) የተቀላቀለችው በ1973 ዓ.ም፤ የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ነው ።

በወቅቱ ስልጠና በመውሰድም በጭላ፣ ሸራሮ እና በሌሎች የትግል ሜዳዎች ወላጆቻቸውን በትግል ወቅት ያጡ ህፃናትን አስተምራለች፤ 'እናት ሁኜ ተንከባክቤያቸዋለሁ' ትላለች።

ትግሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የምትናገረው ብርሃ ከደርግ መንግሥት ጋር በሚደረገው ፍልሚያ ውስጥ መቁሰልና መሞት እንዳለ ቢሆንም ታሞ የአልጋ ቁራኛ መሆንም እንዳለ የእራሷን ገጠመኝ በመጥቀስ ትናገራለች።

"ዓርኮኳይ በሚባል በረሃ ድንገት ዐይኔን ታወርኩኝ፤ ሆዴም ተነፋ፤ ዐይኖቼ ደም እያነቡ ታጋዮች ለሶስት ወራት በአልጋ ተሸክመውኝ ይንቀሳቀሱ ነበር። ያኔ ገደል ውስጥ ብገባ ብዬ የተመኘሁበት አጋጣሚ ነበር፤ በታጋዮች እንክብካቤ ግን ታክሜ ድኛለሁ"በማለት ያለፈውን ታስታውሳለች።

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ማዕድ የቀረቡት ምን ይላሉ?

"እምቦጭን ለማጥፋት የመጡት ጢንዚዛዎች አልጠፉም"

ከሽግግር መንግሥት በኋላ ከሰራዊቱ የተቀነሰችው ብርሃ ለወር በተሰፈረላት 270 ብር ያቋረጠችውን ትምህርቷን በመቀጠል 12ኛ ክፍልን አጠናቀቀች።

"ይከፈለኝ በነበረው ብር እንደ አባትም እናትም ሁኜ ሁለት ልጆቼን በማሳደግ፣ ራሴን በማስተማር በ2000 ዓ.ም በቋንቋ ዲፕሎማ፣ በ2005 ዓ.ም በማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪዬን አገኘሁ" ትላለች።

Image copyright BIRHA ATSIBEHA

በ270 ብር ከሁለት ልጆቿ ጋር ኑሮዋን ስትገፋ የነበረችው ብርሃ በተመረቀችበት የትምህርት ዘርፍም በአመቱ በትግራይ ገቢዎች ቢሮ በ4 ሺህ ብር ደመወዝ ተቀጠረች።

በዚህ ደሞዟ ኑሮዋ ጣፍጦ፣ ጥሩ ለብሳ ጥሩ ጎርሳ ስትኖር ሌሎች እንደርሷ በትግል በረሃ ብዙ ያሳለፉና በችግር እግር ቶርች የታሰሩ እህቶቿን መርዳት እንዳለባት ወሰነች።

" የምትራብ ታጋይ መኖር የለባትም" በሚል መንፈስ በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ የቀድሞ ታጋዮች ጋር በመሆን ችግር ውስጥ የወደቁትን ሴት ታጋዮች ለመርዳት 'የህወሐት የእድሜ ባለፀጋ ሴት ታጋዮች ማህበር' የሚል በጎ አድራጎት ማህበር አቋቋመች።

እናም ማህበሩ የካቲት 10/2008 ዓ.ም 300 የህወሐት ሴት ታጋዮች አባላትን ይዞ ከክልሉ ፍትህ ቢሮ እውቅና በማግኘት ተቋቋመ።

ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላም በወቅቱ የህወሐት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ከነበሩት አቶ እያሱ የድጋፍ ደብዳቤ ተሰጣቸው። እርሷ እንደምትለው ከህዝብ ያገኙትም ተቀባይነት ጥሩ ስለነበር በመጀመርያ የገቢ ማሰባሰብያ መድረካቸው ብቻ በአንድ ቀን 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚሰጣቸው ቃል ተገባላቸው።

የመጭው ዘመን አምስቱ ምርጥ ምግቦች

በመፈንቅለ መንግሥቱ ዙሪያ ያልተመለሱት አምስቱ ጥያቄዎች

ቃል የገቡት ደግሞ የክልሉ መንግሥት ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች እንደበሩ ታስታውሳለች።

ጦስ ያመጣው የአዲስአበባ ጉዞ

በመቀሌ ከተማ ከተካሄደው የገቢ ማሰባሰብያ እና እርዳታ መድረክ በኋላ የማህበሩ መሪዎች እና ደጋፊዎች ሁለተኛ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ለማዘጋጀት ወደ አዲስአበባ አመሩ። አዲስ አበባ ግን የጠበቁት ነገር እንዳልጠበቁት ሆነ።

ብርሃ አፅብሃ እንደምትለው የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኩ አዲስአበባ በሚገኘው የህወሐት ፅህፈት ቤት እንዳይካሄድ እገዳ ገጠመው። በኋላም ወደ ህወሐት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ቢሮ ቢሄዱም አንጀት ጠብ የሚል መልስ ሳያገኙ ጓዛቸውን ሸካክፈው መቀሌ ተመለሱ።

መቀሌ እንደተመለሱ ወደ ህወሐት ዋና ፅህፈት ቤት በመሄድ 'ለምን ተከለከልን?' ብለው መጠየቃቸውን ያስታውሳሉ።

ያገኙት መልስ ግን አጭር ነው "ፕሮጀክቱ እናንተ የምትሰሩት አይደለም፤ ዘግተነዋል" የሚል።

በወቅቱ በፅህፈትቤቱ ሲሰሩ የነበሩት የአሁኑ የማእከላዊ ዞን አስተዳደር አቶ እያሱ ተስፋይ ግን 'እኛ ማህበሩ እንዲጠነክር ደብዳቤ በመፃፍ አገዝናቸው እንጂ አልከለከልናቸውም፤ የሚሉትን ነገር ውሸት ነው' በማለት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ታጋይ ብርሃ እንደምትለው "ፓርቲው ሊሰራው የሚገባውን ነገር እኛ በመስራታችን ልታመሰግኑንና ልታበረታቱን በተገባ ነበር" ስንላቸው በማህበሩ ስራ አስከያጆች እና በፓርቲው አመራሮች መካከል ውዝግብ ተፈጠረ ትላለች።

የዛሬ 30 ዓመት... የኮ/ል መንግሥቱ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

አለመግባባት እየተካረረ ባለበት ወቅት "ብርሃ የዓረና ፓርቲ አባል ናት" የሚል ወሬ በመወራቱ በማህበሩ አባላት መካከል ክፍፍል ፈጠረ።

"የዓረና አባል ባሉኝ ግዜ ደነገጥኩኝ ፤ ባልሆንኩትን ነገር ስሜን ስላጠለሹት አለቀስኩኝ" ትላለች።

በማህበሩ ውስጥና ውጪ ያለው አለመግባባት የተለያዩ ጉዳዮችን እየመዘዘ ቀጠለ።

"አስቀድመውም በማህበሩ አላማ የተቀመጠው በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሴት ታጋዮችን መርዳት" የሚለውን ሃሳብ አልተቀበሉትም የምትለው ብርሃ " 'ለምን የህወሐት ታጋይ ሴቶች አላችሁ፤ ስም ቀይሩ' " በሚልም መጋጨታቸውን ታስታውሳለች።

ቀስ በቀስም የማህበሩን ገንዘብ አጥፍታለች በማለትና የማህበሩ አባላቱን በማሳደም ከማህበሩ እንዳስወጧት ትናገራለች።

500 ሺ ብሩ ወዴት ገባ?

በመጀመርያ በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መድረካቸው ከተገኘው 1.5 ሚሊየን ብር 500 ሺ ብሩ ከትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ቢሮ ቃል የተገባ ነበር።

"ይሁን እንጂ በህወሐት ፅህፈት ቤት ያሉ ሰዎች ለእኛ በመከልከል በድብቅ ወደ ካዝናቸው እንዲገባ አደረጉ" በማለት ከክልል መንግስት ቢሮ ወደ ህወሐት ፅህፈት ቤት እንዲገባ የተፃፈውን ደብዳቤ እንደማስረጃነት ታቀርባለች።

ታጋይ ብርሃ ሁኔታውን እንዳወቀች ደብዳቤውን የፃፈውን ግለሰብ ሄዳ ያነጋገረቸው ሲሆን "በአለቆቼ ታዝዤ ነው" እንዳላት ትናገራለች።

"ሰነዶቹ እጄ ውስጥ እንዳሉ ሲያውቁ አሰሩኝ፣ ከስራዬ አባረሩኝ" በማለት የደረሰባትን ትናገራለች።

የነበራትን ትጥቅ ለመንግሥት ብታስረክብም 'ትጥቅሽን አስረክቢ' በሚል መታሰሯን፤ 200 ሺ ብር ሰርቃ ወደ ውጪ ልትጠፋ ነው በማለትም በውሸት መከሰሷን፤ ፍርድቤት ግን በ10 ሺ ብር ዋስ እንድፈታ እንዳደረገ ታስረዳለች።

ፍርድቤቱ ጉዳዩን አጣርቶ ነፃ ቢላትም ጉዳዩን ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በመውሰድ በሙስና ተከሰሰች። በኋላ ላይም ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ነፃ ነሽ ብሎ አሰናበታት።

በአሁኑ ሰአት 'የህወሐት የእድሜ ባለፀጋ ሴት ታጋዮች ማህበር ስራ አስኪያጅ' የሆኑት ወይዘሮ ዘውዱ ገብሩ ግን የኮሚሽኑ ውሳኔ ልክ እንዳልነበረ እና እንደማያምኑበት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

"ማህበራችን ውሳኔውን አይቀበለውም፤ ኮሚሽኑ ያቀረብነው ክስ አይቶቷል የሚል እምነት የለንም። ማህበር ነው የሚበልጠው ወይስ ወይዘሮ ብርሃ? ወደ ኮሚሽኑ ቅሬታ አስገብተን ነበር" ይላሉ።

ትራምፕ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፅእኖ እያሳደሩ ነው?

በአሁኑ ሰአት በአዲስ አመራር እየተመራ ያለው ማህበሩ ለመጀመርያ ግዜ ከተካሄደው የገቢ ማሰባሰብያ መድረክ በስተቀር ሌላ መድረክ አላዘጋጀም። ለምን የማህበሩ እንቅስቃሴ እንደተቀዛቀዘም ወይዘሮ ዘውዱ ሲናገሩ "በአሁኑ ግዜ በፓርቲውና በክልሉ የሚያሳስብ ሁኔታ ስለተፈጠረ ቀስ ብለን እናየዋለን" ሲሉ ይመልሳሉ።

በዚህ ጉዳይ ስማቸው የተነሳውን እና አሁን ማእከላዊ ዞን አስተዳደር የሆኑት አቶ እያሱ ተስፋይ "ማህበሩ ነፃ ስለሆነ በተነሱ ቅሬታዎች ላይ የማውቀው ጉዳይ የለም፤ ሁሉም ውሸት ነው። እኛ በአቅማችን ስንመክር እና ስናግዛቸው ነበር። የህወሐት ፅህፈት ቤትም ሆነ እኔ በማህበሩ ጉዳይ ውስጥ ገብተን ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ አንልም" ብለውናል።

ከትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ቢሮ ለማህበሩ እንዲሰጥ ቃል ስለተገባና በድብቅ ወደ ህወሐት ፅህፈት ቤት ካዝና ገባ ስለተባለው ግማሽ ሚሊየን ብር ተጠይቀው ሲመልሱም

"በህግ መሰረት ገንዘብ ከመንግስት ወደ ፓርቲ አይገባም፤ ከገባም ስህተት ነው። የህወሐት የፋይናንስ ሰዎች መጠየቅ ይችላሉ። በአጠቃላይ እየተባለ ያለው ነገር ስም ማጥፋት ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ ግን ከትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ቢሮ ለማህበሩ እንዲሰጥ ቃል የተገባው ግማሽ ሚልየን ብር ወደ ህወሐት ፅህፈት ቤት ካዝና እንዲመለስ የተፃፈ ደብዳቤ ተመልክቷል።

በማህበሩ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት ራሷን ከማህበሩ አባልነት ያገለለችው ለተርፍኤል ተስፋይ በበኩሏ "የማህበሩ መቋቋም ለመንግሥት እና ለፓርቲው የሚያግዝ ነበር። ይሁን እንጂ ጣልቃ እየገቡ ማህበሩን ስላዳከሙት፤ ከአባልነት ራሴን አግልያለሁ" በማለት "ብርሃ አፅበሃ ያጋጠማት ችግርም "በህወሐት አመራር ላይ ያለው ብልሹ አሰራር የሚያሳይ ነው" ትላለች።

የአመት እረፍት ወስዳ ለማህበሩ ስትታትር የነበረችው ታጋይ ብርሃ በመቀጠልም እረፍቷን በማስረዘም ያለ ደመወዝ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ሲታዘጋጅ ነበር። በዚህ መሀልም በማታውቀው ሁኔታ ከመስሪያ ቤቷ ትግራይ ገቢዎች ቢሮ ደብዳቤ ሳይደርሳት ሌላ ሰው እንደተቀጠረ አወቀች።

"ህጋዊ ቢሆን ምክንያቱን ያሳውቁኝ ነበር፤ መልቀቂያም ይሰጡኝ ነበር፤ ይህ ሁሉ አልሆነም" ትላለች።

ብርሃ አፅበሃ ሁሉም መንገዶቿ ሲዘጉባት በመቀሌ ጎዳናዎች ላይ ቆሎ በመሸጥ ኑሮዋን እየገፋች ነው። "በገንዘብ እጦት ልጄ የሁለተኛ አመት የኮሌጅ ትምህርቷን አቋርጣለች" በማለት የችግሯን ግዝፈት ታስረዳለች።

ቢቢሲ የህወሐት ፅህፈት ቤት ኃላፊን በተደጋጋሚ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።