ህወሀት እና ህግደፍ ይታረቁ ይሆን?

አብርሃም ገብረሊባኖስ እና ሃብቶም ገብረሊባኖስ Image copyright CELEBRITY EVENTS
አጭር የምስል መግለጫ አብርሃም ገብረሊባኖስ እና ሃብቶም ገብረሊባኖስ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያካሄዱትን አውዳሚ ጦርነት ተከትሎ፤ ምንም የሰላም ጭላንጭል በሌለበት በራቸውን ለ20 ዓመታት ዘግተው ቆይተዋል።

ብዙ ሰላም የማውረድ ጥረቶች ባልተሳኩባቸው ሁለት አስርት ዓመታት፤ የሁለቱን አገራት ሕዝቦችና ምሁራን አሰባስቦ በመንግሥታቱ ላይ ተጽእኖ በመፍጠር ሰላም ማውረድ ይቻላል ብለው ያመኑ ወንድማማቾች 'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' የተሰኘ ተቋም መሰረቱ።

ወንድማማቾቹ አብርሃም ገብረሊባኖስ እና ሃብቶም ገብረሊባኖስ ላለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ህወሀትንና ህግደፍን ለማስታረቅ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ገልጸዋል።

"አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው"- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መሳካቱ የሚናገረው አብርሃም ገብረሊባኖስ፤ ''ሕዝቦች በአንድነት ሆነው መንግሥታቱ ወደእርቅ የሚመጡበትን መንገድ ሊፈልጉና ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ'' ይላል።

'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' የተባለው ተቋማቸው በተለያዩ ጊዜያት 'መዝሙር' እና 'ሰላም' የተሰኙ የምክክር መድረኮች አዘጋጅቷል።

''እንቅስቃሴው ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በያሉበት ሆነው ተጽእኖ መፍጠር ጀመሩ'' የሚለው አብርሃም፤ 'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' በሁለቱ አገራት ዙርያ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ እየቻሉ መድረክ ላላገኙ ምሁራን መድረክ እንደፈጠ ያስረዳል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች እንዲቀራረቡ እንዲሁም ተጽእኖ እንዲፈጥሩ መሠራቱንም ያክላል።

''የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት እንዲወስን እኛና ሁለቱ ሕዝቦች ግፊት አድርገዋል። እንደ ፕሬዝደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያሉ ትልልቅ ሰዎች ተጽእኖ ማሳደራቸውም አይረሳም። ኤምባሲዎችም ግፊት ሲያደርጉ ነበር። መንግሥታቱም ይህን ያውቁት ነበር።''

ኢትዮጵያና ኤርትራ የመጨረሻውን የሠላም ስምምነት ፈረሙ

የሁለቱን አገራት ድንበር መከፈት ተከትሎ፤ 'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' በመቐለ ከተማ ያካሄደውና የሁለቱም አገራት አርቲስቶች የተሳተፉበት የሙዚቃ ዝግጅት፤ ጥልቅ የመነፋፈቅና የወንድማማችነት ስሜት የተንጸባረቀበት ነበር።

ህወትንና ህግደፍን ማስታረቅ ለምን አስፈለገ?

'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' በምሁራን ታግዞ፣ በሁለቱም አገራት ጥናት እንዳካሄደ የሚገልጸው አብርሃም ገብረሊባኖስ፤ '' አሁን የተገኘው ሰላም ቀጣይና አስተማማኝ እንዲሆን ምን መሠራት አለበት? ብለን ጥናት ለማካሄድ ሞከርን፤ የሁለቱ ፓርቲዎች መኮራረፍ ረዥም ርቀት እንደማይወስደንና መታረቃቸው ለሰላሙ አስፈላጊ እንደሆነም ተረዳን'' ይላል።

ተቋሙ ባካሄደው ጥናት፤ ህወሀትና ህግደፍ ማን ናቸው? የማያግባባቸው ነገር ምንድንነው? በመሀከላቸው የውጭ ጣልቃ ገብነት ነበረ? ሁለቱን ፓርቲዎች ለማስታረቅ የሚስችል ሁኔታ አለ? ግዜው ይፈቅዳል? ከሁለቱ ፓርቲዎች እርቅ የኤርትራ እና የትግራይ ሕዝቦች ምን ይጠቀማሉ? የሚሉና ሌሎችም ጉዳዮች በጥልቀት እንደተዳሰሱ አብርሃም ይገልጻል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ፡ አዲስ ዓመትን በቡሬና በዛላምበሳ

"ከጥናቱ ያገኘነው ሃሳብ የሁለቱ ድርጅቶች መቃቃር አሁንም ቢሆን በሕዝቦች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ነው። ተግባብተው መሥራት ባለመቻላቸው፤ ምስራቅ አፍሪካም መረጋጋት ኣልቻለም። ተቀናቃኝ እንጂ ለሰላምና ለልማት አብረው የሚሠሩ አይደሉም" ይላል አብርሃም።

ጥናቱን ሲጨርሱ የሁለቱ አገራት ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን ህወሀት እና ህግደፍ መታረቅ አለባቸው ወደሚል ድምዳሜ እንደደረሱ ይገልፃል።

የአሁኑ የ 'ሰለብሪቲ ኤቨንትስ' ዓላማ ህወሀትና ሕዝባዊ ግንባር ችሮቻቸውን የሚፈቱበት መድረክ መፍጠር ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ሰላሙ አስተማማኝ እንደሚሆን ያምናሉ።

ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተነሳ

"ይህም የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ያለሃሳብ እንዲያርሱ፣ እንዲሸምቱ፣ እንዲነግዱ፣ እንዲጋቡ ያደርጋል" የሚለው አብርሃም፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ብዙ ስጋቶች ያዘለ እንደሆነ ይናገራል።

ህወትና ዝባዊ ግንባር ሊታረቁ ይችላሉን?

ከኢትዮጵያ የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን ጥሪ መቀበላቸውን ባሳወቁበት ወቅት፤ የህወሀትን ስም አንስተው "ጌም ኦቨር" (ጨዋታው አከተመ እንደማለት) ሲሉ ተደምጠዋል።

ወደኢትዮጵያ በመጡበት ወቅትም ቀድሞ ሲመላለሱበት የነበረውን የትግራይን ምድር አለመርገጣቸው፤ ብዙዎች "ሰውየው ገና እንደተቀየሙ ነው" እንዲሉ አስገድዷቸዋል።

በአንፃሩ አቶ አባይ ፀሃዬን የመሰሉ ከፍተኛ የህወሀት ሰዎች "እኛ ቂሙን ትተነዋል፤ እሳቸውም [ፕሬዚደንት ኢሳይያስ] ቢተዉት ምናለ?" ብለው ተናግረው ነበር።

"ዋናው ሕዝቡ እነዚህ ድርጅቶች እንዲታረቁ መፈለጉ ነው። መሪዎቹ ላይ ጫና በመፍጠር ወደውይይት እንዲመጡ ማድረግ ሁለተኛው ነው" የሚለው አብርሃም፤ ሕዝቡ ሁለቱ ድርጅቶች እንዲታረቁ እንደሚፈልገግ ባደረጉት ጥናት አንዳረጋገጡ ይናገራል።

ወደሁለቱ መንግሥታት ደብዳቤ ልከው አወንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ገልጾ፤ "እምቢ ያለን የለም፤ እስከአሁን እየተባበሩን ነው" በማለት ተስፋ እንዳለ ይገልጻል።