ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርበት የተከታተሉት የእራት ግብዣ

(ከግራ ወደ ቀኝ) ብሩክ አምዱ፣ ዊት ፅጌ፣ መሐሙድ አሕመድ፣ እና አብርሐም ወልዴ Image copyright Brook Amdu
አጭር የምስል መግለጫ (ከግራ ወደ ቀኝ) ብሩክ አምዱ፣ ዊት ፅጌ፣ መሐሙድ አሕመድ፣ እና አብርሐም ወልዴ

ከአጤ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ተዘግቶ የነበረው የአጤ ምንሊክ አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፍቶ እንግዶችን ያስተናገደው እሁድ ዕለት ነበር።

በዕለቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ሀሳብ ደግፈው 5 ሚሊየን ብር ለአንድ እራት የከፈሉና የተጋበዙ 300 እንግዶች በዚህ አዳራሽ ታድመዋል።

ከእንግዶቹ መካከል ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የባህር ማዶ ሰዎችም ነበሩ።

በዚህ በሚኒሊክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለተደረገው የእራት ግብዣውን መድረክ፣ ድምጽና መብራት ያዘጋጅው ብሩክ አምዱ ይባላል። 'ጁብሊ' የተባለ ተቋም አለው።

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ማዕድ የቀረቡት ምን ይላሉ?

"እራት ለመመገብ አይደለም የምንሄደው" በላይነህ ክንዴ

የ5 ሚሊዮን ብር እራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር

አዳራሹ፤ እሁድ ዕለት ከተደረገው 'ገበታ ለሸገር' የእራት ግብዣ በፊት ስድስት ቀናት የፈጀ መሰናዶ ተደርጎበታል የሚለው ብሩክ፤ ዶ/ር ዐብይ በየዕለቱ የሥራ ሂደቱን ይከታተሉ እንደነበር አጫውቶናል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየታቸውን እየሰጡ በመመሪያቸው መሠረትም ሁሉም ነገር እንደተሰናዳ ብሩክ ይገልፃል።

የግብር አዳራሹ እሁድ ዕለት ወደ 300 የሚጠጉ እንግዶችን ከማስተናገዱ በፊት የነበረው ሥራና ውጣ ውረድ ሲገልፅ "በጣም አድካሚ ነበር" ይላል።

አዳራሹን ከማሰናዳታቸው በፊት "ቤቱ በታሪክ ምን ይመስላል?" ብለው ራሳችውን ጠይቀው የነበረ ሲሆን ይህም ቀለማትን፣ የመብራት ዓይነትንና የድምፅ ሂደትን ለይቶ ለማወቅ እንደጠቀማቸው ያስረዳል።

የ 'ሞዛይክ' መስተዋት ቅቦቹ፣ የኮርኒሱን ምህዳሮችና እንጨቶቹ በአብዛኛው ቀይ ቀለም ጎልቶ የሚታይባቸው ስለሆኑ አብረው የሚሄዱ ቀለማት ተጠቅመዋል።

ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ታሪኩ ሳይሽፈን በዘመናዊ ማጌጫዎች ማስዋቡ አስፈላጊ ሆኖ ታይቶናል በማለት፤ ቀይ ፅጌሬዳ በብዛት መጠቀማችውን ያስረዳል።

Image copyright Brook Amdu
አጭር የምስል መግለጫ የአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ በቀይ አበባ ተውቦ

የእራት ዝግጅቱ ዓላማ አዲስ አበባን አረንጓዴ ማድረግ እንደመሆኑ፤ አዳራሹን በአረንጓዴ ቀለማት ከማስዋብ አልፈው አትክልቶችን በየቦታው አስቀምጠው ነፋሻማ አየር እንዲዘዋወር አድርገዋል። አዳራሹ ውስጥ በአረንጓዴ አፀድ በተከበበ ስፍራ የመቀመጥ ስሜትን ለመፍጠርም ወጥነው ነበር።

የማስዋብ ሥራውን ሲያጠናቅቁ በአዳራሹ ውስጥ ወደሚኖረው የድምፅ ማስተላለፊያ ሥርዓት ወይም 'አኩስቲክ' ሥራ ተሸጋገሩ።

እዚህ ላይ ትንሽ ችግር እንደገጠማቸው ያጫወተን ብሩክ፤ "'ፊልተሪንግ' እና 'ባላንሱን' የሚያመጣልንን መሣርያ በማናውቀው መንገድ ነው የተጠቅምነው። የነበሩት ባህላዊ ሙዚቃ መሣርያዎች ስለነበሩ በኤሌክቴሮኒክ ሲስተም ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ ነበረብን" በማለት የግብዣው ዕለት የአብርሃም ወልዴ ባህላዊ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ቡድን ላቀረበው ትርዒት ያደረገውን አስተዋፅኦ ያስረዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአብርሃም ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የተሠራውን ካዩ በኋላ ቅር አላቸው።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረኩን አልወደዱትም ነበር። በትክክል ሳንግባባ ቀርተን ነው መሰለኝ። ስለዚህ አፍርሰን እንደ አዲስ መገንባት ነበረብን"

መድረኩን በድጋሚ መሥራት ለምን አስፈለገ? ስንለው፤ ዋናው ትኩረት ሙዚቃው ላይ ሳይሆን እንግዶቹ ላይ ስለነበረ በቅድሚያ በተዘጋጀውና ፕሮጀክቱን በሚያሳው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ለማተኮር ተፈልጎ እንደነበረ ያስረዳል።

Image copyright Brook Amdu
አጭር የምስል መግለጫ በ"ገበታ ለሸገር" የእራት ግብዣ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው የድምፅ መሳሪያዎች በከፊል

ፎቶ ለሚነሱ እንግዶች ታስቦ የአዳራሹ ዋና መግቢያ ላይ ብሩህ መብራቶች ተተክለው ነበር።

በየጠረጴዛው ላይ ከተቀመጡት ትንንሽ ሻማዎች በተጭማሪ፤ ከአዳራሹ መግቢያ አንስቶ እንግዶች የሚራመዱበት መንገድ በሻማ እንዲያሸበርቅ ተደርጎ ነበር። ከሻማው ጎዳና በኋላ የአዳራሹን ነባር 'ሻንድልዬር' የሚያጎሉ ቀለል ያሉ መብራቶችን እንደተጠቀሙም ብሩክ አጫውቶናል።

የአዳራሹ ድምጽና መብራቱ የእንግዶቹ ትኩረት ፕሮጀክቱ ወደሚተላለፍበት ሸራ እንዲሆን ታስቦ ነው የተሠራው።

Image copyright Brook Amdu
አጭር የምስል መግለጫ የአጤ ምኒሊክ የግብር አዳራሽ በከፊል

የመሰናዶው ዝግጅት ድርጅት ባለቤት የሆነችው ዮዐዳን ያዘጋጀቻችው ወንበሮች አዳራሹን ልዩ አድርገውት ነበር። ወንበሮቹ ወደውስጥ የሚያሳዩ በመሆናቸው መብራት ሲያርፍባቸው በማንፀባረቅ የአዳራሹን ውበት አጉልተውታል።

ብሩክ ቅድመ ዝግጅቱን ሲጨርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ጎበዝ፤ ተስፋ አለህ" ሲሉት የተለየ ስሜት እንደተሰማው አካፍሎናል።

እሁድ ከሰአት በቀደሙት ነገሥታት ዘመን ይደረግ እንደነበረው እንግዶች ወደግብር አዳራሹ ሲገቡ ነጋሪት እየተጎሰመና እምቢልታ እየተነፋ፣ ጋባዡ ዶ/ር ዐቢይም በደጅ ሆነው እንግዶቻቸውን ሲቀበሉ ሲመለከት፤ ልፋቱን በማስታወስና ነገሮች ሁሉ እንደታሰቡት በመሄዳቸው በሥራው ኮርቷል።

Image copyright Brook Amdu
አጭር የምስል መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ብሩክ አምዱ በአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ፊት ለፊት

"የዝግጅቱ መጠናቀቂያ ላይ "ኢትዮጵያ ሃገሬ" የሚለው ዘፈን ሲደመጥ እነመሐሙድ አሕሙድ፣ አለማየሁ እሽቴ እና ሌሎችም ድምጻውያን ከመቀመጫቸው ተነስተው አብረው ሲዘፍኑ ሳይ በጣም የተለየ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር።"

ከሁሉም በላይ ብሩክን ያስገረመው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማንኛውም ሰው እንግዶችን ከበር ተቀብለው፣ ሰላምታ እየሰጡ ማስገባታቸውና ዝግጅቱ ካለቀ በኋላም ልብሳቸውን ቀይረው ወደአዳራሹ በመሄድ እቃዎቹን ሲያነሳሱና ሲያፀዱ የነበሩት ግለሰቦች ማየታቸው ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ