ቦትስዋና ዝሆን ማደን ፈቀደች

ዝሆን Image copyright Getty Images

ቦትስዋና ዝሆንን ለማደን የሚከለከለውን እገዳ ማንሳቷን አስታውቃለች። ምክንያት ብላ ያቀረበችውም በሰዎችና በእንስሳቱ መካከል በተደጋጋሚ የተፈጠረውን ግጭት እና ዝሆኖቹ ሰብል ወደ ማውደም መሸጋገራቸውን ነው።

ዝሆኖችን ማደን የሚከለክለው ህግ የወጣው እ.ኤ.አ በ2014 ሲሆን ክልከላው ገበሬዎችንና ከዚህ በፊት በማደን ገቢ ያገኙ የነበሩ ግለሰቦችን እየጎዳ ነው ብለዋል።

በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ዝሆኖች የሚገኙት ቦትስዋና ሲሆን 130 ሺህ ያህል ዝሆኖች እንዳሏት ይገመታል።

ኬንያዊው ፀሀፊ ቢንያንቫንጋ ዋይናይና ሲታወስ

በጉጂ አስር ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

"የከተማ መስፋፋት የኢትዮጵያን ብዝሀ ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል" ዶ/ር መለሰ ማርዮ

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞክግዌትሲ ማሲሲ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር በቀድሞው ፕሬዝዳንት የተጣለውን እገዳ ለመመርመር ኮሚቴ ያዋቀሩት።

በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይም ኮሚቴው እገዳው እንዲነሳ የሚል ምክረ ሀሳብ ማቅረቡ ተሰምቶ ነበር።

"የዝሆኖቹ ቁጥር መጨመር፣ በዝሆኖቹና በሰው ልጆች መካከል የሚፈጠር ግጭት መበራከት፣ ዝሆኖቹ በሰውና በእንስሳት ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመር" ወደ እዚህ ውሳኔ እንደገፋቸው በመግለጫቸው ላይ የገለፁት የአካባቢ፣ የተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስትሩ ናቸው።

አክለውም "አደን ሲፈቀድ ሕግን በተከተለ እና ስርዓት ባለው መልኩ እንዲሆን እናደርጋለን" ብለዋል።

የክልከላው መነሳት እርምጃው ፖለቲካዊ ነው ብለው በማያምኑ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ዘንድ ብስጭትን ይፈጥራል።

ሀገሪቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የአካባቢ ጥበቃ ስም የሚያጠለሽ ሲሆን ለሀገሪቱ ከዳይመንድ ማዕድን ማውጣት ቀጥሎ ሁለተኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የቱሪዝም ሀብቷንም ይጎዳል ተብሏል።