የትናንቱ ኢፍጣር እና የአዲሱ መጅሊስ እርምጃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት የኢፍጣር ሥነ ሥርዐት በሚሊኒየም አዳራሽ ከሕዝበ ሙስሊሙ ጋር ታድመዋል Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

ትናንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና ሌሎችም የመንግሥት ባለስልጣኖች በተገኙበት የኢፍጣር ሥነ ሥርዐት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዶ ነበር።

በርካታ ሙስሊሞች የተገኙበት የኢፍጣር ሥነ ሥርዐት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖም አምሽቷል። ሥነ ሥርዓቱ በሕዝበ ሙስሊሙ መካከል አንድነት የታየበት ነበር የሚል አስተያየት የሰነዘሩም ነበሩ።

ጉዳዩን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ መጅሊስ ከመቋቋሙ ጋር ያያዙትም ነበሩ። ሕዝበ ሙስሊሙ ለበርካታ ዓመታት ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች በአዲሱ መጅሊስ እንደሚመለሱ አመላካች ስለመሆኑም ተነግሯል።

"መንግሥት የሚደግፈው የሙስሊሙን ሕብረተሠብ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የአዲሱ መጅሊስ መቋቋም ምክንያት የነበረው የሙስሊም ማኅበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባልና የአዲሱ መጅሊስ አማካሪ የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የትላንቱን ኢፍጣር "ታሪካዊ" ሲሉ ይገልጹታል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድነት ማፍጠራቸውም አስደስቷቸዋል።

"ሕዝበ ሙስሊሙ ረመዳን በመጣ ቁጥር ስቃይ ያሳልፍ ነበር። ይህ ረመዳን ግን ሰላም የወረደበትና ሕዝበ ሙስሊሙ ለጥያቄዎቹ በአግባቡ መልስ ያገኘበት ነው" ብለዋል።

የትናንቱን ኢፍጣር ከተካፈሉት አንዱ የሆነው ሀጂ አቡበከር አለሙ፤ ቀደም ባለው ጊዜ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጋር ተቃቅሮ፣ ለእስርም ይዳረግ እንደነበር አስታውሶ ነገሮች በመለወጡ ደስተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ምሽቱን "ተዐምራዊ" ሲልም ይገልጸዋል።

በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ስብሰባ ምን ውሳኔዎች ተላለፉ?

ተስፋ የተጣለበትን አዲስ መጅሊስ በማቋቋም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች የተመሰገኑበት ምሽት እንደነበር ኡስታዝ ካሚል ያወሳሉ።

ለመሆኑ አዲሱ መጅሊስ ከተቋቋመ ወዲህ ምን ተሠራ? ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ነው?

የሀጅ ጉዞ

አዲሱ መጅሊስ መሻሻል ያደርግባቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል የሀጅ ጉዞ በዋነኛነት ይጠቀሳል። የሀጅ ጉዞ ዋጋ መናርና ተጓዦች የሚደርስባቸው እንግልትም በርካቶችን አማሯል።

ኡስታዝ ካሚል እንደሚሉት፤ የዘንድሮው የሀጅ ጉዞ ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንዲሆን ያላሳለሰ ጥረት እያደረጉ ነው። ከጉዞው መነሻ እስከመድረሻ ያለውን ችግር አጥንቶ መፍትሄ የሚያበጅ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በጉዞው የሚገጥመውን ችግር የሚፈትሽ የልዑካን ቡድን ወደሳዑዲ መላኩንም ያክላሉ።

ጥናቱ ሲጠናቀቅ አንድ ተጓዥ የሚያስፈልገው ትክክለኛ ወጪ ተተምኖ ጉዞው ያለውጣ ውረድ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

"ማኅበረሰባችን ከአየር መንገድ ከተነሳ ጀምሮ ሀጂ አድርጎ እስከሚመለስ የነበሩ እንቅፋቶችን እናጸዳለን። መካ ከደረሱ በኋላ በቤት ኪራይ፣ በምግብና በመጓጓዣ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በተወሰነ ደረጃ ሕዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንደሚያገኝ ተስፋ እናደርጋለን።"

ባለፈው ዓመት የሀጅ ጉዞ በርካታ ውጣ ውረድ ከገጠማቸው አንዱ የሆነው ሀጂ አቡበከር እንደሚለው፤ የዘንድሮው ሀጅ ጉዞ እየተቃረበ በመምጣቱ፤ በአጭር ጊዜ የጉዞውን ችግሮች በአጠቃላይ ለመፍታት ይከብዳል።

"የተጋነነ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልገምትም። ከዚህ በፊት የነበረው ሥራ አስፈጻሚ የዘንድሮውን ሀጅ ለማስፈጸም ተፈራርሞ ስለመጨረሱም መረጃ አለኝ" ይላል።

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እንግልት በመካ

Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ?

ኡስታዝ ካሚል፤ አዲሱ መጅሊስ ለሕዝበ ሙስሊሙ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥና ከቀድሞው መጅሊስ በተቃራኒው ከመንግሥት ተጽዕኖ የተላቀቀ ነው ይላሉ።

ሆኖም የመጅሊሱን መቋቋም እውን ያደረገው ኮሚቴ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መዋቀሩ እንዲሁም በአዲሱ መጅሊስ ምስረታ ጠቅላይ ሚንስትሩ መገኘታቸው መንግሥት ዛሬም በጉዳዩ እጁን እያስገባ ነው? የሚል ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም።

ኡስታዝ ካሚል፤ ቀድሞ መንግሥት 'መጅሊስ ልምረጥላችሁ' ይል እንደነበረና አሁን እውነታው መቀየሩን ይናገራሉ።

"እኛ መንግሥትን እዚህ ቦታ ተገኝልን ብለን እየጠራን ነው። ከዚህ በፊት መንግሥት ሲያጠቃው የነበረውን ሕዝብ እንደዜጋ እየተመለከትክ ስለመሆኑ ዋስትና ስጠው ብለናል" ይላሉ።

በመንግሥትና በሀይማኖት ተቋሞች መካከል መኖር ካለበት ግንኙነት ያፈነገጠ ትስስር እንደሌለም ይገልጻሉ።

ሕዝበ ሙስሊሙ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወጥቶ በመረጠው አመራር እየተዳደረ መሆኑን የሚናገሩት ኡስታዝ ካሚል፤ "መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከጣልቃ ገብነት መውጣቱን ማወጅ ችሏል። እስካሁን ከነበረው ጎጂ ጣልቃ ገብነት ወጥተናል። የአሁኑ እሱ ራሱ ሲያበላሽ የነበረውን ነገር እንዲያስተካክል የማድረግ ጉዳይ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

አዲሱ መጅሊስ በተቋቋመበት ወቅት ያነጋገርናት ሙኒራ አብደልመናን የኡስታዝ ካሚልን ሀሳብ ትጋራለች።

"ቀድሞ መጅሊሱን ይመሩ የነበሩት የመንግሥት ካድሬዎች ነበሩ። [በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውይይት ላይ የመንግሥት ባለስልጣኖች የተገኙት] መንግሥት ያስቀመጣቸውን ሰዎች ራሱ ማንሳት ስለነበረበት ነው። ይህ ቋሚ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን እስካሁን የነበረው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መወገዱ ምልክት እንደሆነ አስባለሁ" ትላለች።

መንግሥት ከመጅሊሱ እጁን ያውጣ የሚለው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በሀይማኖት አስተምሮት የላቁ ሰዎች ወደአመራር መምጣታቸውን ሁለቱም ይስማሙበታል።

ለወደፊትስ?

አዲሱ መጅሊስ አሁን ላሉ በርካታ ችግሮች መፍትሄ ሰጪ እንደሆነ ተስፋ ተጥሎበታል። የሀጅ ጉዞን ማስተካከልና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ መውጣት ዋነኛ ጥያቄዎች ቢሆኑም ሌሎችም ምላሽ የሚያሻቸው ጉዳዮች አሉ።

ሀጂ አቡበከር መንግሥት በመጅሊሱና በእስልምና ጉዳዯች ጠቅላይ ምክር ቤት ውስጥ ያደርግ የነበረው ጣልቃ ገብነት መወገዱ መልካም እንደሆነ ጠቅሶ፤ የሚስተዋለው ለውጥ በፌደራል መንግሥት የሚገደብ ሳይሆን ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል የሚያዳርስ መሆን እንደሚገባው ይጠቁማል።

ኡስታዝ ካሚል በበኩላቸው፤ አዲሱ መጅሊስ በዋነኛነት የኡለማ ምክር ቤትና ሕጋዊ ቦርድን ወደክልሎች የመውሰድ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ገልጸው፤ ለውጡ በመላው አገሪቱ እንዲዳረስ እንደሚረዳ ያስረዳሉ።

ሕዝቡ እንደዜጋ ደህንነት ተሰምቶት ይወክለኛል የሚል ተቋም ማግኘቱን እንደስኬት ይጠቅሳሉ። "ትላንት 'የመንግሥት መጅሊስ' ይል የነበረ ሕዝብ፤ ዛሬ መጅሊሳችን ማለቱ ትልቅ ለውጥ ነው" ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለዓመታት ይቃወሟቸው የነበሩ ብልሹ አሠራሮች መንስኤ የነበረው ተቋም ሙሉ በሙሉ መለወጡን እንደትልቅ እርምጃ የምታየው ሙኒራ፤ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚሠራ ሀገር አቀፍ ተቋም መመስረቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ትላለች።

ቅድሚያ እንዲሰጠው ስለምትፈልገው ጉዳይ ስትናገርም "መጅሊሱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙሰኛ አሠራር ማጽዳት ያስፈልጋል" ትላለች። ከሀጅ ጉዞና ከሱቅ ኪራይ ገቢ ቢገኝም መስጅዶች እንደመብራትና ውሀ ያለ መሰረታዊ ነገር ለማሟላት ማኅበረሰቡን መለመናቸውን እንደማሳያ ትጠቅሳለች።

እነዚህና ሌሎችም ችግሮች በጊዜ ሂደት እንደሚፈቱ ሙኒራ፣ ሀጅ አቡበከርና በርካቶች ተስፋ ያደርጋሉ።