ኡጋንዳ፡ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ገንዘብ ወይም ምግብ መለገስ ተከለከለ

የኡጋንዳ ገንዘብ የያዘ እጅ Image copyright Getty Images

በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ ለሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ገንዘብ ወይም ምግብ መስጠት የሚከለክል ሕግ ወጥቷል። ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች ደግሞ 11 ዶላር (300 ብር ገደማ) ይቀጣሉ።

ካምፓላ ውስጥ እድሜያቸው ከ7 እስከ 17 አመት የሆነ ወደ 15,000 የሚጠጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚኖሩ የአገሪቱ መንግሥት ያሳወቀ ሲሆን፤ የከተማዋ ከንቲባ ኤሪያስ ሊክዋጎ፤ ሕጉ ወሲባዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸውና እንዳይበዘበዙ ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

ኡጋንዳ ስደተኞችን ከእስራኤል ለመቀበል ስምምነት ማድረጓን አስተባበለች

ህፃናት ከመኖሪያ መንደራቸው ተሰርቀው ወደከተማ እየተወሰዱ እንዲለምኑና በጠባብ ክፍል እንዲኖሩ እንደሚገደዱ የቢቢሲዋ ዲር ጀኔ ዘገባ ይጠቁማል። መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ለጎዳና ተዳዳሪዎችና በወሲብ ንግድ ለተሰማሩ ግለሰቦች ቤት ማከራየት ከልክሏል።

ህፃናትን አስከትለው የሚለምኑት ጋርአኒ ካቱሬጌ የተባሉ የ60 ዓመት ሴት እንደሚናገሩት፤ ሰዎች ህፃናትን ሲያዩ ስለሚራሩ ገንዘብ ይሰጧቸዋል። ስለዚህም ከህፃናት ውጪ መለመን አይፈልጉም። "ቢያስሩንም ግድ የለንም" ሲሉ የሕጉ መውጣት ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸዋል።

ኡጋንዳ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ቀረጥ ልታስከፍል ነው

ከንቲባው ኤሪያስ ሊክዋጎ በበኩላቸው ሕጉ ልጆቻቸውን ተጠቅመው ገንዘብ የሚካብቱ ቤተሰቦችና ደላሎችን እንደሚያስቆም ይናገራሉ። በሕጉ መሰረት፤ ጎዳና ላይ የሚነግዱና የሚለምኑ ቤተሰቦች እንደሚታሰሩም ገልጸዋል።

"እየተጧጧፈ የመጣውን ልጆችን ከተለያዩ ከተሞች ወደካምፓላ የመውሰድ ንግድ ማስቆም እንፈልጋለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ተያያዥ ርዕሶች