የዊኪሊክስ መስራች ጁልያን አሳንጅ ተጨማሪ 17 ክስ ቀረበበት

ጁልያን አሳንጅ Image copyright AFP

የአሜሪካ የፍትሕ ሚንስቴር፤ የዊኪሊክስ መስራች ጁልያን አሳንጅ ላይ 17 ተጨማሪ ክሶች አቅርቧል። አሁን በእስር ከሚገኝበት እንግሊዝ ወደ አሜሪካ እንደሚወሰድም ይጠበቃል።

አሜሪካ አሳንጅ ላይ ያቀረበችው ክስ በሕገ ወጥ መንገድ የመረጃ ምንጮችን ማውጣት ይገኝበታል። ክሱ የአሜሪካን ሕግ በመጣስ 2010 ላይ ሚስጥራዊ የሆኑ ወታደራዊና የዲፕሎማሲ መረጃዎችን ማሾለክንም ያካትታል።

ኢኳዶር የጁሊያን አሳንጅን እቃዎች ለአሜሪካ ማስረከብ ጀመረች

የፔንታጎንን መረጃ ለማግኘት ቸልሲ ማኒንግ ከተባለች የቀድሞ ሰላይ ጋር በመመሳጠር ባለፈው ወር ተከሶ እንደነበር ይታወሳል። እንግሊዝ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ በነበረበት ቀን ባለመቅረቡ የ50 ሳምንት እስር ተፈርዶበት ሚያዝያ ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።

አሳንጅ ከመታሰሩ በፊት ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ በጥገኝነት ይኖር የነበረ ሲሆን፤ ኢኳዶር ጥገኝቱትን ከነጠቀችው በኋላ ዘብጥያ መውረዱም ይታወሳል።

ስዊደን ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ መከሰሱን ተከትሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ በኢኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ ነበር። በወቅቱ የ47 ዓመቱ አሳንጅ ክሱን ማጣጣሉም ተዘግቦ ነበር።

የኤርትራ 28ኛ ዓመት ነፃነት ከየት ወደየት?

አሳንጅ ምንጮቹ ሚስጥራዊ መረጃ በማውጣት ለዊኪሊክስ እንዲሰጡ ያበረታታ እንደነበር በክሱ ተመልክቷል። የቀድሞዋ ሰላይ ቸልሲ ማኒንግ ሚስጥራዊ መረጃ እንድትሰርቅ ይደግፍ እንደነበርና የወታደራዊ ኮምፒውተር ይለፍ ቃልን ጥሶ ለመግባት እንደተስማማም ተገልጿል።

የቀድሞዋ ሰላይ ወታደራዊ መረጃ በማሾለክ የ35 ዓመት እስር ተፈርዶባት ነበር። ፍርዱን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ቢቀንሱላትም፤ ዊኪሊክስ ላይ ለመመስከር ፍቃደኛ ስላልሆነች በእስር ላይ ትገኛለች።

በአፍጋኒስታን፣ በቻይና፣ በኢራን፣ በኢራቅና በሌሎችም ሀገሮች የሚኖሩ ምንጮችን ይፋ በማድረግ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል የተከሰሰው አሳንጅ፤ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የዓመታት እስር ይጠብቀዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በሚያውቋቸው አንደበት

ዊኪሊክስ በበኩሉ፤ ክሱ ጋዜጠኞች ላይ የተቃጣና የመናገር ነጻነትን የሚጋፋ ነው ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

ተባባሪ አቃቤ ሐወግ ጆን ደርሜስ መሥሪያ ቤታቸው የጋዜጠኞችን መብት እንደማይገፍ ተናግረው "ደግሞም አሳንጅ ጋዜጠኛ አልነበረም" ብለዋል። ጋዜጠኞች በጦር ሜዳ ያሉ ምንጮችን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ማንነታቸውን ይፋ እንደማይደርጉም አክለዋል።