ሞና ሊሳ ዲፕ ፌክ በተሰኘ ቴክኖሎጂ "ነፍስ ዘራች"

ሞና ሊሳ እንዴት እንደተሠራች የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል Image copyright Samsung

የሊዮናርዶ ዳ ቬንቺ ዝነኛ የጥበብ ሥራ የሆነችው 'ሞና ሊሳ' በግጥም፣ በዘፈን፣ በልብ-ወለድ ወይንም በአጭር ወግ ውስጥ ነፍስ ዘርታ አብረናት የልቦለዱን ዓለም ብንገማሸርበት አይደንቅም።

የ 'አርተፊሻል ኢንተለጀንስ' የጥናት ባለሙያዎች የወደድነው አይኗን፣ ያደነቅነው አንገቷንና አፏን በተንቀሳቃሽ ምስል ማሳየት ችለዋል።

እንዴት? ካሉ፤ አንዲት ነጠላ ምስሏን ወስደው በቤተ ሙከራ ውስጥ ነው ማንቀሳቀስ ቻሉ መልሳችን።

"ሀኪሙ ትግሉን አቀጣጠለው እንጂ የሚታገለው ለታካሚው ነው"

ብዝኀ ሕይወት ምንድን ነው? ለምንስ ግድ ይሰጠናል?

ቴክኖሎጂው 'ዲፕ ፌክ' ይሰኛል። ይህ ቴክኖሎጂ የአንድ ነገር ድግምግሞሽን ተጠቅሞ ነው ሥራውን የሚከውነው። የግኝቱ ባለቤት ሞስኮ የሚገኘው የሳምሰንግ ቤተ ሙከራ ነው ።

ነገሩ ብዙዎችን አላስፈነጠዘም። ፊታቸውን ቅጭም አድርገው፤ "ይህ 'ዲፕ ፌክ' ያላችሁት ቴክኖሎጂ ላልተገባ ተግባር የመዋል እድሉ የትየለሌ ነው" ሲሉ የተቃወሙ አሉ።

ይህንን የምርምር ሥራ ይበል የሚያሰኝ ብለው ያጨበጨቡ፣ የወደፊቱ የቴክኖሎጂ እመርታ ቀድሞ ያሳየ ብለው ያደነቁም አልጠፉም።

ይህ የሳምሰንግ ቴክኖሎጂ ግን የ7ሺህ ስመ ጥር ሰዎችን ምስሎች ከዩቲዩብ ሰብስቧል። ከዚያም ከምስሉ ላይ የፊት ቅርፅንና እንቅስቃሴን ወስዶ 'እፍ' በማለት ሕይወት ይዘራባቸዋል።

Image copyright Samsung

እንደውም ይግረማችሁ በማለት የሳልቫዶር ዳሊን፣ የአልበርት አንስታይንን፣ የፌይዶር ዶስቶቭስኪ እና የማርሊን ሞንሮ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለቅቋል።

እ.ኤ.አ በ2017 በቴልአቪቭ ዩኒቨርስቲ ተመሳሳይ የምርምር ሥራ ይፋ ተደርጎ ነበር።

ታዋቂው ኬንያዊ ደራሲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ያኔ ምስላቸው ተወስዶ በሌሉበት፣ ባልዋሉበት እንደዋሉ ተደርገው የቀረቡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ነበሩ።

የዚህ ፈጠራ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሱፓሶርን ሱዋይናኮርን በወቅቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ቴክኖሎጂው ላልተገባ ድርጊት ሊውል ይችላል ነገር ግን በጎ ጎንም አለው።

የምንወደውን ሰው በሞት ስንነጠቅ፣ ፊታችንን ነጭተን፣ ከል ለብሰን ከል መስለን ከምንቀመጥ፣ ምስላቸውን ሕያው እንዲሆን በማድረግ መፅናናት እንችላለን ይላሉ።

ባለሙያዎች ግን የፖለቲከኞች ምስል በዚህ ቴክኖሎጂ ተቀነባብሮ፤ ሀሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት ወይም የአንድን አገር ሕዝብ ግራ ለማጋባት ሊውል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

ይህ 'ዲፕ ፌክ' ቴክኖሎጂ ዝነኛ ሰዎችን ባልዋሉበት አስውሎ የወሲብ ፊልሞች ላይ ሊያሳትፋቸው ይችላል ያሉም አልታጡም።

የ 'አርተፊሻል ኢንተለጀንስ' ቴክኖሎጂ አማካሪ የሆኑት ዴቭ ኮፕሊን፤ በዚህ 'ዲፕ ፌክ' ቴክኖሎጂ ላይ እንኳንም በጊዜ መወያየት ጀመርን ይላሉ።

"በጊዜ ውይይት መጀመራችን መልካም ነው፤ እውነት የሚመስሉ ሀሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በቀላሉ መሥራት እንደሚቻል ማህበረሰቡ ማወቅ አለበት" ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ